ሦስት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ስንዴ ለማቅረብ ጥያቄ ቀረበ

0
557

አፕላስ ኢምፖርተር የተባለ መቀመጫውን ውጭ ያደረገ ድርጅት በመንግሥት አገሪቷ ገበያን ለማረጋጋት የታሰበውን አራት መቶ ሺሕ ኩንታል ስንዴ በሦስት ቢሊየን ብር ለማቅረብ ተጫረተ።

በግዢና ንብረት አገልግሎት ኤጀንሲ ባለፈው ሐሙስ፣ ጥር 23 በተከፈተው ጨረታ ላይ ለመሳተፍ 31 ድርጅቶች ፍላጎት ቢያሳዩም የተወዳደሩት ስምንት ድርጅቶች ናቸው። በዕለቱ ጨረታው ሲከፈት የቴክኒክና የፋይናንስ ሰነዶች የተነበቡ ሲሆን አሸናፊው ድርጅት ከ15 ግምገማ በኋላ የሚለይ ይሆናል የተባለ ሲሆን አሸናፊው ድርጅት ያሸነፈበትን ስንዴ ለንግድ ሚኒስቴር የሚያስረክበው ኤል ሲ ከተከፈተ ከ30 ቀን በኋላ ይሆናል፡፡

ከተጫራቾች መካከል አንዱ የሆነው አፕላስ፤ አንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በአማካይ በ276 ነጥብ 5 ዶላር ለማቅረብ ተጫርቷል። ይህ በዓለም ዐቀፉ ግሬን ካውንስል ከወጣው ዋጋ ሲነፃፀር የ30 ዶላር ጭማሪ ያለው ሲሆን ቡንጂ ኤስ ኤ፣ አምሮፓ፣ ኢንትሬድ፣ ፎኒክስና ፕሮሚሲንግ የተባሉ ድርጅቶች በተወዳደሩበት ጨረታ የተካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ኮርፖሬሽን በአገሪቷ የስንዴ ገበያን ለማረጋጋት በማለም ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው።

ለብዙ ዓመታት ስንዴ በማቅረብ የሚታወቀው ፕሮሚስንግ አንድ ቶን ስንዴ በ314 ዶላር ለማቅረብ የተጫረተ ሲሆን ከቡንጂ በመቀጠል ትንሹን ዋጋ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም ተጫርቶ ያልተሳካለት የስዊዘርላንዱ ቡንጂ በበኩሉ በአማካይ 306 ዶላር ለማቅረብ ተጫርቷል።

በግዢ ሒደት ያለው ስንዴው ለዳቦ ቤቶች እና ለፋብሪካዎች የሚከፋፈል መሆኑ የታወቀ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች የታየው የዋጋ ለውጥ ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ስንዴ ለመግዛት የምታወጣ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ግማሽ ቢሊየን ዶላር አውጥታለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here