ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች

0
2341

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሴቶች በአገራችን ብሎም በዓለማችን ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር እምቅ ኃይል አላቸው። በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸው እየጨመረ መምጣት ከጀመረ ሰነባብቷል።
ያለ ሴቶች ተሳትፎ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለውጥ ለማምጣት መጣር በጊዜ ላይ እንደመቀለድ ሊሆን ይችላል። እንደ ምክንያት የሚወሰደውም ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚኖራቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ነው።

ሴቶችን በማስተማር ሆነ አሰልጥኖ በተለያዩ የትምህርት፣ ሥራ እና ፖለቲካ መሰል ጉዳዮች ላይ ማብቃት መቻል ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ሚና አለው።
ከዚህ ቀደም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በይበልጥም በኢትዮጵያ ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራ ከመሥራትና በልጅነት ዕደሜ ወደትዳር ዓለም ገብቶ ልጅ ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እና ውሳኔ መስጠት አይችሉም ነበር። የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተቀምጠው ሲመሩ መመልከት እንዲሁም በማንኛውም ጉዳዮች ላይ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ሲያሰሙ መስማት እጅግ ከባድ ነበር።

በማኅበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ሴቶች አቅም እና ችሎታቸውን ሳያወጡ እና ሳይጠቀሙበት ለዘመናት እንዲቆዩ ያደረጋቸውን አስተሳሰብ በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በፈጠሩት ተጽዕኖ የተነሳ ነበር ተብሎ እንዲቀር አድርገዋል ለማለት ያስደፍራል።
ከማኅበረሰቡ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች የተሳሳተውን አመለካከት ሠብሮ ለመውጣት የከፈሉት ዋጋ ግን ቀላል የሚባል አይደለም። ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ከወንዶች እኩል በተለያዩ አገራዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እየሠሩ እና ሐሳባቸውን በነፃነት እየገለፁ፣ እንዲሁም በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተቀምጠው ውሳኔ እየሰጡ ይገኛሉ።

ሴቶች በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረጉም ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ፣ የኢትዮጲያ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ ብርቱካን ሚደቅሳ ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በአምስት ዓመቷ የአይን ብርሃንዋን ያጣችው እና ትምህርቷን ተከታትላ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ኹለት ዲግሪ በማግኘት በብዙኃኑ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለችው የትነበርሽ ንጉሴ እና ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች ሎዛ አበራ በጥቂቱ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ተብለው መጠቀስ ይችላሉ።

ሴቶች የራሳቸውን ዕምቅ አቅም በመገንዘብ በተሰማሩበት የሥራና የትምህርት ዘርፎች ላይ ጠንክረው በመሥራት ቀደሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከትን በመቀየር ሴቶችን ለተሻለ አቅም እና መነሳሳት እየፈጠሩ ይገኛሉ። ሴቶች በአገር ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተጽዕኖ ፈጥረው የተሻለ ለውጥ እያመጡ ስለሚገኙ ማንኛውም አካል ሴቶችን መደገፍ ይጠበቅበታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here