የፌደራል የሥነምግባር እና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከሙስና ቅድመ መከላከል ሥራዎች ጋር በተያያዘ ሲቀበላቸው ከነበሩ ጥቆማዎች ውስጥ 34ቱ ከኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ውጭ በመሆናቸውና የወንጀል ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ሆነው በመገኘታቸው ለአዲስ አበባና ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ መላኩን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የሚቀርቡለትን የተለያዩ የሙስና ጥቆማዎችን እየተቀበለ አስፈላጊውን መረጃ በማጠናቀር የቅድመ መከላከል ሥራ እየሠራ ይገኛል። የወንጀል ድርጊት ሆነው የተገኙ ጥቆማዎችን ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 22(3) መሰረት ጉዳዩን የመመርመር ሥልጣን ላለው አካል ይልካል።
በዚህም መሠረት ከግንቦት እስከ ሐምሌ ወር 2013 ባለው ጊዜ ለኮሚሽኑ ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ 34ቱ ወንጀል ነክ ጥቆማዎች ሆነው በመገኘታቸውና ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልጋቸው በመታመኑ ለአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል መላካቸው ታውቋል።
ለምርመራ የተላኩት የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች በአብዛኛው በተለያዩ ቼኮች በግለሰብ ስም ገንዘብ መውሰድ፤የመንግሥት ቤትን ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞር ማድረግ፤ በመንግሥት ይዞታ ላይ ካርታ እንዲሰጥ ማድረግ፤ ለዋጋ ማረጋጊያ የመጣን የፍጆታ ዕቃ ለሕብረተሰቡ ሳይደርስ መሸጥ፤ በተቋም ገንዘብ ለግለሰብ አክሲዮን መግዛት፤ ያልተገባ ስጦታ መቀበል፤ የመንግሥትን እና የሕዝብን ገንዘብ ማጉደል፤ ከውጭ የተላከን ንብረት ባለቤት ላልሆነ ሰው መስጠት፤ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የመንግሥት ገንዘብን ለመመዝበር ጥረት ማድረግ እና ሕግን ባልተከተለ መልኩ የጨረታ ሒደት ቅድሚያ ክፍያ መክፈል፤ የሚሉት በዋናነት የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች መሆናቸውን የቀረቡት ጥቆማዎች ያመለክታሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013


