በ2013 አመት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር(Cup of Excellence)ላይ ቀርቦ ማሸነፍ የቻለው ቡና በ14 ሺሕ 533 ብር በኪሎ መሸጡ ተገለጸ።
የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር አሸናፊ የሆነው ቡና በበይነ መረብ በተደረገው ጨረታ ላይ ቀርቦ በ330 የአሜሪካን ዶላር ወይም በ14 ሺሕ 533 ብር በኪሎ ሊሸጥ ችሏል። ቡናውን ሳዛ ኮፊ ኦፍ ቶኪዮ የተሰኘ ድርጅት መግዛቱም ተጨምሮ ተገልጿል።
ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የነበሩበት ሲሆን፣ በዘንድሮው ውድድር ላይ ከ1 ሺሕ 800 በላይ ተወዳዳሪ ቡና ቀርቦ አሸናፊ ለሆኑት የሽልማት እና የእውቅና መስጠት መርሃ ግብር ነሀሴ 20 በስካይ ላይት ተካሂዷል።
በሽልማት እና እውቅና መስጠት መርሀ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሆኑት ይናገር ደሴን(ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የግብርና ሚኒስትር የሆኑት ዑመር ሁሴን ባደረጉት ንግግር ላይ ”አገራችን ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላት ቢሆንም የአምራቾች ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው።“ ያሉ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የግብይት ስርዐቱ ላይ የተራዘመ ሰንሰለት መኖሩ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል።
የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) በበኩላቸው የተገኘው ውጤት ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ጠቅሰው በውድድሩ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የቡና አይነቶች መቅረባቸው ተነስቷል።
በዚህ አመት ላይ ሳዑዲ አረቢያ ዋነኛ የቡና ገዢ አገር ሆና ብቅ ማለቷ የተነሳ ሲሆን፣ ከቀረቡት የቡና አይነቶች አብዛኛውን በመግዛት ግንባር ቀደም ሆና ተገኝታለች። በዚህም ምክንያት አዲስ የገበያ መዳረሻ አገር እየተፈጠረ ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ መሆኑ ተጠቅሶ በአዲስ በተገኙት የገበያ መዳረሻዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013


