የኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች አሊያንስ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌትነት በላይ እንደተናገሩት፣ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃደኝነት የተመሠረተ ማህበር ሲሆን፤ በቀጣይነት አቅሙን አሳድጎ አለም አቀፋዊ የመሆን አላማ እንዳለው በማህበሩ የምስረታ ስነስርአት ላይ ተናግረዋል:: በእለቱም ዋተር ሪሶርስ ግሩፕ (WRG) ለኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች አሊያንስ የሎጂስቲክስ እና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ማሰቡ ተነግሯል::
በነሐሴ 20፣ 2013 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች አሊያንስ ምስረታ ላይ የአባላት ቻርተር ፊርማ ስነስርዓትና የአመራር የስራ ቡድኖች ኮሚቴ ምርጫ ተከናውኗል:: የአመራር የስራ ቡድኖች ኮሚቴ ምርጫ በዋናነነት በበጎ ፈቃደኝነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ከውሃ 3፣ ከቢራ 2፣ ከደረቅ አልኮል አምራቾች 1፣ ከለስላሳ መጠጦች 1 እንዲሁም ከጁስ 2 አምራች ድርጅቶች ተመርጠዋል::
የኢትዮጵያ መጠጥ አምራቾች አሊያንስ ለውሃ ቁጠባ የተመሠረተው ውሃን በሰፊው የሚጠቀሙ እንደ የታሸጉ ውሃ፤ የለስላሳና የቢራ መጠጥ ያሉ አምራቾች ድርጅቶች የዉሃ አጠቃቅም በይበልጥ አግባባዊ እና ሳይንሳዊ እንዲሆን ታስቦ ነው ተብሏል::
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013


