በቅርስነት የተመዘገበው የራስ ኃይሉ ተክለኃይማኖት ቤት ለመፍረሱ የኮርፖሬሽኑ ተከራይ እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት ተጠያቂዎች ናቸው ሲል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ ለቅርስ ቤቱ የዕድሳትና ጥገና ፈቃድ እንዲሰጥ ለወረዳ 5 የመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት ደብዳቤ ፃፍኩኝ እንጂ ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ አላዘዝኩም ሲል ለአዲስ ማለዳ በላከው ማብራሪያ አስረድቷል።
የራስ ኃይሉ ተክለኃይማኖት ቅርስ ቤት በቀድሞው ወረዳ 1 ቀበሌ 08፣ የቤት ቁጥር 1222 በአሁኑ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የሚገኝ ሲሆን፤ የኮርፖሬሽኑ ተከራይ ደንበኛ የዕድሳትና ጥገና ፈቃድ እንዲሰጣቸው ኮርፖሬሽኑን ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው መጠየቃቸውን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
በዚህ መሰረት ኮርፖሬሽኑ የቤቱ ዋናው ቤት ግድግዳ ሳይነካ የልስንና የቀለም ሥራዎች እንዲታደስ፤ የዕድሳትና ጥገና ፈቃድ እንዲሰጥ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁንም አስረድቷል።
ቢሆንም ግን ጽ/ቤቱ ኮርፖሬሽኑ ባላዘዘውና ባልጠበቀው መንገድ ቤቱን ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ለተከራይ ደንበኛው ያለአግባብ ፈቃድ መስጠቱን ነው ኮርፖሬሽኑ የገለፀው።
በዚህም መሰረት ተከራዩም ከወረዳ 5 የመሰረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት የተሰጡትን የዕድሳትና ጥገና ፈቃድ ወደ ኮርፖሬሽኑ ይዘው በመቅረብ፣ የጥገናና ዕድሳት ውል ከኮርፖሬሽኑ ጋር ሳይፈጽሙ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሥራ የገቡ መሆኑን በሱፐርቪዥን በማረጋገጡ ሕገ-ወጥ ሥራውን እንዲያቆሙ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው መደረጉን ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
“የተጠቀሰው ቤት ከቆይታ ብዛት እያረጀና እየፈራረሰ ሲሄድ በተጠና ሁኔታ ዋናውን የቤት መዋቅር ሳይነካ የልስንና የቀለም ዕድሳት እንዲሠራ ለሚመለከተው አካል ፈቃድ እንዲሰጥ ከመጠየቅ ውጭ፤ ቤቱ ፈርሶ እንደ አዲስ እንዲሠራ ኮርፖሬሽኑ ለወረዳው ፈቃድ አልጠየቀም” በማለትም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ስለጉዳዩ አስረድቷል።
ስለዚህ በዚህ የቅርስ ቤት የማፍረስ ሒደት የተሳተፉት፣ ይህንን ቤት ሙሉ በሙሉ ፈርሶ እንዲገነባ የፈቀደው የወረዳ 5 የመሰረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ጽ/ቤት እና የጥገና ዕድሳት ውል ሳይፈጽሙ ወድ ቅርስ ማፍረስ የገቡት ተከራይ ግለሰቡ ናቸውም ብሏል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ተገቢውን ክትትል የሚያደርግ መሆኑንም ገልጿል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አያይዞም የአዲስ አበባ ታሪካዊ ቅርስ ከነበረው የቡፌ ደላጋርን መፍረስና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ወይም ኮሜርስን ለማፈረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን ገልጿል።
በኮርፖሬሽኑ ተጠያቂ ናቸው የተባሉትን ወረዳ 5 እና ተከራዮቹን አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀርቷል።
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013


