50:50:0፦ በሐረር ብዙ ሺሕዎችን ያለውክልና ያስቀረ ፖለቲካ

0
790

በኢትዮጵያ የብሔር ፌዴራሊዝም ጉድለቶች ውይይት ላይ እንደማሳያ ሳይቆጠር የማይታለፈው ክልል የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው። ቤተልሔም ነጋሽ የግል ትዝታቸውን እና የሐረር ነዋሪ የሆኑ ቤተሰባቸውን ተግዳሮቶች እንደ ምሳሌ በመዘርዘር ክልሉ ውስጥ የተዘረጋውን አድሎአዊ የፖለቲካ ግንኙነት እንደሚከተለው ተችተው ጽፈዋል።

 

 

በ1983 የመንግሥት ለውጥ ተደርጎ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ አብሮ በመጣው ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ምክንያት ባለፉት 27 ዓመታት ከባቢውን ተቆጣጥሮት የነበረው የብሔር ፖለቲካ እንደነበር ማንም አይስተውም። ባሕልና የብሔር ማንነት፣ እንዲሁም የዜጎች በገዛ ቋንቋቸው የመማር፣ የመሥራትና የመተዳደር መብት መከበር ከዚህ ስርዓት በበጎ ጎን ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መንግሥት ሕዝቡን ይመስላል ቢባልም፥ በአገራችን ድሮ አልተወከልንም፣ ቦታ ተነግፈን፣ ተረስተን ኖረናል የሚሉት አስተዳዳሪ በሆኑበት ጊዜም ሳይቀር ዛሬም መንግሥት ሕዝብን አይመስልም። ዓለም ከፆታ ተዋፅዖ ጀምሮ በሁሉም መልክ ውክልናንና ብዝኃነትን አካታች ሆኖ ለመዋቀር እየጣረ ባለበት ጊዜ፥ በአገራችን ወር ተራ ደርሶኛል በሚል ጭቆናውን ገልብጦ በርካቶችን ውክልና ማሳጣት አሁንም አለ።

እስካለፉት ጥቂት ወራት ተስፋፍቶ፣ ሕዝቡን ረግጦ የኖረው ስርዓት የፖለቲካ ነጻነትን፣ ሰብኣዊ መብቶችንና የኢኮኖሚ እኩልነትን በመጨፍለቅ በብሔር መከፋፈልን አስፋፍቶ አንድነትን ስጋት ውስጥ ጥሎ እንደነበርም ይታወቃል።

በተለይ በደርግና ከዚያም በፊት በነበረው በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በፖለቲካው በዋነኝነት ተሳታፊ ያልነበሩት ወይም “ገዥዎች” ይባሉ ከነበሩት ውጪ ያሉ ብሔሮች በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ማግኘታቸው ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያዊነት የሚለው አንሶ እንዲታይ የተሠራ ሥራ መኖሩም በግልጽ የሚታወቅ ነው።

ሐረር እንደ ማሳያ
በ19 ቀበሌዎች የተከፈለችውን ሐረር ከተማንና በዙሪያው ያሉ ኦሮምኛ ተናጋሪ 17 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራትን ይዞ የተመሠረተው የሐረሪ ክልል በኢትዮጵያ ትንሹ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሕዝቡ በከተማ የሚኖርበት ብቸኛ ክልል ነው። በመጀመሪያው የክልል አወቃቀር ክልል 13 ተብሎ የነበረና በነዋሪው ዘንድም የልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን ስብጥር የያዘ እንደመሆኑ እንደ ድሬዳዋ የፌደራል ከተማ ይሆናል የሚል ተስፋ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ሐረሪ ክልል የሚለውን ሥያሜ አግኝቷል።

በማዕከላዊ ስታተስቲክስ ኤጀንሲ ወቅታዊ ግምት 246 ሺሕ ነዋሪዎች ያሉት ሐረሪ ክልል በኤጀንሲው ይፋዊ ግምት መሠረት 56.41 በመቶ የኦሮሞ፣ 22.77 በመቶ የአማራ፣ 8.65 በመቶ ደግሞ በድሮው አጠራር አደሬ ለክልሉ መጠሪያ በሆነው በአሁኑ አጠራር የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ሲኖሩበት የጉራጌ 4.34፣ የሶማሌ 3.87፣ የትግራይ 1.53፣ የአርጎባ 1.26፣ እንዲሁም ሌሎች ተብለው ተጠቀሱ 1.1 በመቶ ሕዝቦች መኖሪያም ጭምር ነው።

ከላይ በርዕሱ የተቀመጠው የክልሉ ፖለቲካዊ አስተዳደር ደግሞ ልክ ከተዋቀረበት 1986 ወዲህ 50፡50፡0 በመባል የሚታወቅ አሠራር ሲሆን፥ ሁለቱ ማለትም የኦሮሞ እና ሐረሪ ብሔሮች በፓርቲዎቻቸው ሐረሪ ብሔራዊ ሊግና ኦህዴድ (ያሁኑ ኦዴፓ) የክልሉን ምክርቤት 36 መቀመጫ እኩል 18 (50- 50) ሲካፈሉ በፌደራል መንግሥቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ያሉትን 2 መቀመጫዎች እንዲሁ በእኩል ይካፈሉታል። በክልሉ የቢሮዎችና የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይም እንዲሁ ይህ 50፡50 ክፍፍል ይቀጥላል።

በ1987 ወጥቶ የነበረው የመጀመሪያው የክልሉ ሕገ መንግሥት ከነበረው ታሪካዊ ሁኔታና በወቅቱ ከሚነገርበት ስፋት አንፃር አማርኛ የክልሉ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሲወስን በ1997 መስከረም ተሻሽሎ የወጣውና አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች ሐረሪና ኦሮምኛ መሆናቸውን ይደነግጋል። ሆኖም ከተናጋሪ ብዛት አንፃርና የአስተዳደሩ መቀመጫ፣ አብዛኛው የክልሉ አካል ሐረር ከተማ በመሆኑ አሁንም የሥራ ቋንቋው አማርኛ ነው። በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶችም ከጥቂት በኦሮምኛና አንድ በሐረሪ ቋንቋ ከሚሠራ ትምህርት ቤት ውጪ 99 በመቶ ትምህርት ቤቶች በአማርኛ የሚያስተምሩ ናቸው።

የሚገርመው የክልሉ ሕገ መንግሥት መግቢያው ላይ “የሐረሪ ሕዝብ ሲደርስበት የነበረውን ግፍና ጭቆና ሲካፈሉ ከነበሩት ከአካባቢው የኦሮሞ ሕዝብና ከሌሎች የክልሉ ነዋሪ ሕዝቦች ጋር በመሆን የክልሉን አስተዳደር በጋራ ማቋቋምና መምራት ያለባቸው መሆኑን በማጤን” ማለቱ ነው። ሌሎቹ የክልሉን ነዋሪ 34.87 በመቶ ወይንም በወቅቱ ግምት በድምሩ 85 ሺሕ 780 የሚጠጋ ሕዝብ የሚይዙት ብሔሮች ያለውክልና በታዛቢነት ይሳተፋሉ ካልተባለ በቀር በእውኑ ሥልጣን በኹለቱ ተይዞ መቆየቱ ከዚህ አባባል ጋር አይሔድም።

ከሁሉም በላይ ግን፣ ምንም ታሪካዊ ጭቆና እንደ ምክንያት ቢደረግ በየትኛውም አሠራር 8 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ 82 በመቶ የሚሆነውን ቀሪውን ሕዝብ ያስተዳድር የሚል ፖለቲካና ዲሞክራሲ የትም የሚኖር አይመስለኝም። ምናልባት ስናድግ ከሰማነው “ሕወሓት ሐረሪዎች በትጥቅ ትግሉ ወቅት ላደረጉለት ከፍተኛ ድጋፍ (በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩት የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ይልቅ በዳያስፖራና በአዲስ አበባ የሚኖሩት ቁጥር እንደሚበልጥ ይነገራል)፥ ክልሉን እጅ መንሻ ሰጥቷል” ከሚለው ወሬ ውጪ ብዙ ሺሕዎችን ያለውክልና ያስቀረ ውሳኔ ምናልባትም የኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም ከሠራቸው ታሪካዊ ስህተቶች አንዱ ተብሎ ሊቆጠር ይችላል።

ማንኛውም ሐረር ተወልዶ እንዳደገ ግለሰብ ባለኝ መረዳት መሠረት የሐረር አከላልና ሥያሜ [በተለይ የክልሉን ነዋሪ ከፍተኛ ቁጥር በያዘው በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ዘንድ፣ ከተማዋ (የክልሉን 17 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ጨምሮ) በኦሮሚያ ክልል ተከባ ያለች በመሆኑ] ማንንም አስደስቶ አያውቅም። የራሴን ምስክርነት ባቀርብ ክልሉ ከተመሠረተ ቀጥሎ ባሉት ጥቂት ዓመታት ዙሪያው የኦነግ ምሽግ ሆኖ ከቅርብ ርቀት በሚሠማ የተኩስ ድምፅ ምክንያት ከትምህርት ቤት የቀረንባቸውን ብዙ ቀናት አስታውሳለሁ።

በፍቅር መተሳሰብና ኃይለኛ ማኅበራዊ ትሥሥር የሚታወቀውና ለከተማሽ አዳላሽ ባትሉኝ የመልካም ሰውነት ምሳሌ የሆነው፣ ዩኔስኮ በ”ቻይነት” የምስክር ወረቀት የሰጠው የከተማዋ ነዋሪ ከመልካም አስተዳደር ተወካይ እስከማጣት፣ ከቤተሰቡ ጭምር ተወልዶ ባደገበትና ሌላ “አገሬ” የሚለው በሌለበት ባይተዋር ሆኖ ከርሟል። ከቀላሉና መብት ከሆነው የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት እስከ የቤት መሥሪያ መሬትና ሌላ ሌላውንም ተነፍጎ ዐሥርት ዓመታትን አስቆጥሯል። ዓመታቱን በተስፋ መቁረጥ ኖሮ ባለፉት ዐሥር ወራት በመላ አገሪቱ የለውጥ ነፋስ ሲነፍስም ለውጡ አሁንም ሐረር አልደረሰም። ምናልባት ከጥቂት የቄሮ አብዮተኞች ሁኔታውን ለመቀየር የተደረገ ማስፈራራትና ጉንተላ (የከተማዋን የውሃ መሥመር መዝጋትንና ቆሻሻ በስተቀር በብዙ ችግር እንደተዘፈቀ የሚነገርለት ክልሉ ተረስቷል።

ቀላል ምሳሌ ለማንሳት የክልሉ ነዋሪ 27.1 በመቶው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሲሆን በክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 27 (2) “የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸውን የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ” ቢልም በከተማዋ ባለፉት 20 ምናምን ዓመታት አንድም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አልተሠራም። የሕዝቡ ቁጥር ግን በ1986 ከነበረበት በእጥፍ ማደጉን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል።

ሌላው የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 (2) “ሕዝቡ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ሊያነሳው ይችላል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ቢልም ተሳታፊ ፓርቲዎች ከሚወክሏቸው ውጪ ያሉት የከተማዋ ሕዝቦችን ይህ አንቀፅ አይመለከትም ። በአስተዳደሩ ቅሬታ ቢኖርባቸው ምናልባትም የመረጧቸው ተወካዮች ስለሌሏቸው በየት በኩል እንደሚያደርሱ የሚታወቅ አይደለም።

ውክልናው እንደ ቅብጠት ቢታይ እንኳ፥ ሌላው በሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ የሚደርሰው እንደ ባይተዋርና ኹለተኛ ዜጋ መቆጠር የሚያንገበግብ ነው። በሐረሪ ክልል ነዋሪ በሆኑ ከኦሮሞና ሐረሪ ተወላጆች ውጪ በሆኑ ሌሎች ብሔሮች በተለይ በመምህራንና በመንግሥት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው በደል ይህ ቀረሽ የማይባል ነው። ክልሉ ሲዋቀር እንደ አዲስ በተዋቀሩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተለይም ትምህርት የሌላቸውና አማራጭ የላቸውም ተብለው የታሰቡት የቀረበላቸው አማራጭ መባረር ወይንም ማንም ወደማይፈልገውና ባለሙያ እጥረት ወደ ነበረበት የሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ሳይቀር መሔድ ነበር። ሠርተው መኖር የግድ የሆነባቸው የማውቃቸው ሰዎች የቤተሰቤን አባላት ጨምሮ አሁንም ድረስ ሙያቸው በሚፈለግበት፣ እነሱ ግን ከክልሉ ተወላጆች ጋር በእኩል በማይታዩበት በሶማሌ ክልል ይኖራሉ።

የሚገርመው ወላጆቼን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ክልሉን በጋራ ለሚያስተዳድሩት ለሐረሪ ብሔራዊ ሊግና ለኦሕዴድ (ያሁኑ ኦዴፓ) ብቻ ሳይሆን ዞር ብሎ አይቷቸው ለማያውቀው ብአዴን (ያሁኑ አዴፓ) ፈቃዳቸው ሳይጠየቅ ከደመወዛቸው የፓርቲ አባልነት ክፍያ ሲቆረጥባቸው መኖሩ ነው። ጭራሽ “ወደፊት የሐረሪ ቋንቋ የክልሉ ቋንቋ ስለሚሆን በግዴታ ትማራላችሁ” ተብለዋል፤ በተለይ መምህራኑ። በቡኩሌ ፀሎቴ እናቴ ተወልዳ ባደገችበት ከተማ ይህ ሳይደርስባት በጡረታ ከመምህርነት ሥራዋ እንድትወጣ ነው።

እዚህጋ ብዙ መፈናቀሎችና ብዙ በደሎች እንደሚደርሱባቸው ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የብአዴን (የአሁኑ አዴፓ) ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ ተወላጆቸን ዞር ብሎ አለማየቱ፣ በአንፃራዊ መልኩ እንደ ሐረር በቁጥር በዛ ብለው በሚገኙበት ሳይቀር ውክልና ይሰጣቸው ዘንድ ድምፅ አለማሰማቱ የሚገርም ነው። የብሔሩና የፓርቲው አባል ናችሁ ተብሎ የገንዘብና የድጋፍ ድምፅ ከማድረግ ውጪ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲሰቃዩ ንብረታቸው ሲቀማ ዝም ማለቱ ካለፈው የስርዓቱ መጥፎ ውጤቶች ጋር ከመደመር ውጪ ሌላ ምክንያት አይገኝለትም እንዳንል የአማራ ብሔር ተወላጀች 91.4 በመቶ በሆኑበት በራሱ በአማራ ክልል ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2007 ሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሠረት 3.46 የሆኑት የአዊ ብሔረሰብ ተወላጆች እና 2.62 የሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በራሳቸው ቋንቋ የሚሠሩበት፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የየራሳቸው ልዩ ዞኖች ሲኖሯቸው በክልሉ ምክር ቤቶችም መቀመጫ ኖሯቸው ውክልና ሲያገኙ ቆይተዋል። ይህ አሠራር ምነው እንደ ሐረሪ ባሉ የብዙ ብሔሮች መኖሪያ ክልሎች ለምን አልታሰበም? አማራ ክልልስ በክልሉ የሚኖሩ ብሔሮችን መብት ሲያከብር በሌሎች ክልሎች የሚኖሩየራሱን የአማራ ተወላጆች መብት ረሳ?

መፍትሔው ምን ይሁን?
ወደ መፍትሔውና የሁኔታው የመለወጥ ተስፋ ምንድነው ወደሚለው ስንመጣ እዚህም እዚያም፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች የሚደረጉ ጥቂት “ስለ ሐረር ዝም አንልም” የሚሉ ዘመቻዎችና “የሐረር ልጆች ኅብረት” በተሰኘው የክልሉ ተወላጆች መሰባሰቢያ ገጽ በከተማው በተለያዩ ምክንያቶች በሚደረጉ ሰልፎች ላይ “ዶ/ር ዐቢይ ሐረርን አስባት” የሚሉ መፈክሮች፣ እንዲሁም የክልሉን ባለሥልጣናት በሙስናና ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም በመዘርዘር፣ የክልሉን መንግሥት “የቤተሰብ ኃላፈነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” አድርገዋል ተብሎ የሚታሙትን ውንጀላ ከማቅረብ ውጪ የተጠናከረ፣ ከተማዋና ነዋሪው ያሳለፉትን ችግር የሚያወሳ እንቅስቃሴ አልታየም። ክልሉንና ከተማዋን የባለቤትነት ጥያቄ እያነሱባት ካሉት የአካባቢው ወጣቶች ጀምሮ ግፊት ማድረግ ካልተቻለ፣ ወይም ብሶ አመፅ ካልመጣ ግን ምናልባት ሕገ መንግሥታዊ መልስ የሚያሻው ችግር ላይፈታ ይችላል።

በተረፈ በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ከተሞች የመጀመሪያውን ማተሚያ ቤት በማቋቋም፣ የመጀመሪያው የስልክ መሥመርና ጥሪ እንዲሁም የፖስታ አሠራር ተቀባይ በመሆን እንደ ዘመነ ርዝመቷ ቀደምት የነበረች ከተማ፣ ተወላጇን ብቻ ሳይሆን የሚያውቃትን ሁሉ የምታሳዝን፣ በልማት ወደ ኋላ የቀረች፣ ሥሟ የከበዳት ሆና ለመቀጠል ወይም ለመሻሻል የለውጡን ጣልቃ ገብነት የምትሻበት መሐል መንገድ ላይ ቆማለች። በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿም “ፍትሕ ለሐረር” ይላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here