የሚያምረንን ሁሉ ሳይሆን የሚያምርብንን

0
272

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ወንድሞችና እህቶች በቤት ውስጥ አንዱ ድርሻቸው መስታወት መሆን ይመስለኛል። «አምሮብሻል» ብለው ይሸኛሉ፤ «ይህን አውልቀሽ ያንን ብታደርጊ ይሻላል» ብለው የተሻለውን ያመላክታሉ። ከቃላቸው እብለት የለበትም፤ ከመስታወት ይልቅም ሰው ራሱን እንዲህ ባሉ እውነተኛ ወዳጆቹ ያያል።

አንዳንዴ ብዙ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ነገር ግን አለባበሳቸው መላ ቅጡ ጠፍቶ ስናይ፤ መስታወት የሌላቸው መሆኑ ያሳዝነናል። «መላ ቅጡ የጠፋ አለባበስ ምን ዓይነት ነው?» እንደ ስምምነታችን ይለያያል። በእርግጥም ሱሪውን ዝቅ አድረጎ ከአሁን አሁን ወለቀበት እያልን እንድንሳቀስ ከሚያደርገን ጎረምሳ ይልቅ ነገሩ በሴቶች ላይ ጎልቶ መነጋገሪያ ይሆናል። አዎን! ስለእኛ ስለ ሴቶች አለባበስ ላነሳ ነው።

መስታወት ኖረም አልኖረ፤ ዋናው ቁም ነገር የሚያምረንን እና የሚያምርብንን መለየቱ ላይ እንደሆነ ወንድሜ ይነግረኛል። ጻታን መሠረት አድርጌ ሳይሆን ወንድሜን ስለማምነው ሐሳቡን እቀበላለሁ። በተለይ ሴቶች በብዛት የምንወቀስበት አለባበሳችን ይህን ካለመለየት የመነጨም ይመስለኛል። ይልቁንም ስለሴቶች አለባበስ ሲነሳ ብዙዎች «ኧረ ባሕላችን!» ሲሉ፤ ያማራትን ለብሳ፣ ያሻትን የሰውነት ክፍል ገልጣና ያሻትን ሸፍና የምትንቀሳቀስ ሴት ደግሞ፤ «መብቴ ነው!» ትላለች።

እዚህ ጋር አንዱ ባሕል የሚለወጥና የሚያድግ መሆኑን ካለመረዳቱ ሌላው ነፃነት የሚገለፅበትን መንገድ አለማወቁ፤ ሁለቱም ጋር ችግር አለ ባይ ነኝ። ይህን ስናልፈው ደግሞ በገዛ ፈቃድና ምርጫችን ለምን እንሳቀቃለን? ጭፈራና መዝናኛ ቤቶች፣ ሀይቅ ዳርቻ፣ ለዕራት ግብዣ፣ ለፀሐያማ ቀን ወዘተ ተብለው የተሠሩ ልብሶችን ለብሰን፤ ውረድ ወደ ታች፤ ከፍ በል ወደ ላይ እያልን የምንጨናነቀው ለማን ብለን ነው?

ልብስ መሸጫ መደብሮች ግንባር ላይ ተሰቃቅሎ የምናየው ልብስ፤ መደብሮቹ ያምራል ብለው የመረጡትን ነው። ግን ያ እኛም ላይ ያምርብናል ማለት አይደለም። የአንዲት ሴት አለባበስ ለጥቃትም ሆነ ለሌላ ትንኮሳ ሰበብ ይሆናል የሚለውን የነውረኞችን ሰበብ አንቀበልም። ግን ደግሞ ያማረን ሁሉ የሚያምርብን ላይሆን ይችላልና በወዳጆቻችን መስታወትነት ደጋግመን ብናይ እላለሁ።

«የፈለግኩትን መልበስ መብቴ ነው!» አዎን መብታችን ነው። በራስ መተማመንን በምን ዓይነት ልብስ ነው የምንገልጸው የሚለውን ግን መጠየቅ ያስፈልጋል። ነጻነታችንን፣ ውበታችንን፣ በራስ መተማመናችን እንድንገልጥ የሚያስችሉን አለባበሶች አሉ። ደግሞም አስተያየት ሰጪዎችም ውበታችንንና ማማራችን ሲነግሩን ተቀብለን ተግሳፃቸውን አለመቀበል ልክ አይመስለኝም። በዚህም ላይ ሴቶች ብቻ የሚኖሩባት አገር ተገኝታ፤ በዛ ብንኖር እንኳን፤ የምንለብሰው ልብስ ከእንቅስቃሴያችን ጋር የሚሔድ ሊሆን ይገባል። ስላማረን ሳይሆን ስለሚያምርብን ማድጋችን ለዚህ ምላሽ ጥሩ ግብዓት ነው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here