ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡት የጋምቤላ ተወላጆች በኃይል ተበተኑ

0
492

በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት በስደተኞች ዙሪያ ያወጣውን አዋጅ በመቃወም በመስቀል አደባባይ ሐሙስ፣ ጥር 23 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተገኙ የጋምቤላ ክልል ተወላጆች ፈቃድ አላቀረቡም በሚል ምክንያት ሰላማዊ ሰልፉ እንዳያደርጉ በፀጥታ ኃይሎች ተከለከሉ።

በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መኖራቸው ለኅልውናቸው አደጋ መሆኑ የገለጹት ሰልፈኞቹ ለስደተኞች አገር ውስጥ ከመሥራት እስከ ዜግነት መብት የሚያጎናጽፈውንና በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ የፀደቀውን አዋጅ በፅኑ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

ይህን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ፤ ስልፈኞቹ የያዙት ፈቃድ ሕጋዊ መሆኑንና ከክልሉ መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ተፅዕኖ እያሳደሩባቸው እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ገልፅዋል።

አዋጁ የጋምቤላ ተወላጆችን ሳያወያይ የፀደቀ በመሆኑ ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን በአብላጫ ድምፅ መፅደቁ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ተቃውሞዎች በተለይም በጋምቤላ ክልል ተወካዮች ተሰምተው እንደነበር ይታወሳል። ለአብነትም ኡጁሉ ኦባንግ የተባሉት የምክር ቤቱ አባል ‹‹ሌሎች አገራት አቅማቸውን አገናዝበው ነው ስደተኛ የሚቀበሉት የእኛ አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው›› ሲሉ የተቃውሞ ሐሳባቸውን አሰምተው ነበር።

ኡጁሉ ‹‹የክልሎች ፍላጎት ባልተጠየቀበትና ባልተዋያዩበት ሁኔታ አዋጁ እንዲወሰን ማድረግ አግባብ አይደለም ብለው የስደተኞች ነባራዊ ሁኔታንም ታሳቢ ያደረገ አይደለም›› ሲሊ ተደምጠው እንደነበር አይዘነጋም።

አዲሱ አዋጁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች በኢኮኖሚ ዘርፎች ተሰማርተው ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ፤ በሚኖሩበት አካባቢ መሬት እንዲያገኙና በመስኖ የግብርና ልማት እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ ከመሆኑም በተጨማሪም ቋሚ ንብረት የማፍራት፤ የመሸጥና የመለወጥን ጨምሮ ዜግነት እስከ ማግኘት መብትን ያቀፈ ነው።

በጋምቤላ ክልል በ2007 በማዕከላዊ ስታትስተክስ ኤጀንሲ በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ አጠቃላይ የክልሉ ሕዝብ 307 ሺሕ 096 መሆኑንና አራት የተለያዩ ብሔሮች ሲኖሩ ትልቁ የኑዌር ብሔረሰብ ሲሆን 46 ነጥብ 6 በመቶ አኙዋክ፤ 22 ነጥብ 1 በመቶ መዥንገር እንዲሁም ኦፖ እና ኮሞ የሚባሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጎሣዎችና ያሉ ሲሆን የአማራ ኦሮሚያና ትግራይ ብሔረሰቦችም በክልሉ ይኖራሉ። በክልሉ አራት አስተዳደራዊ ዞኖች ሲኖሩ የጋምቤላ ከተማ በአኙዋክ ዞን ላይ ይገኛል።

የዓለም ባንክ ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረገው ጥናት (skill profile refugee survey) ተሳታፊ የነበሩት የጥናት ባለሙያ መሣይ ግርማ በጉዳዩ ላይ በሰጡን አስተያየት ‹‹የዓለም ባንክ ስደተኞቹ ከተረጂነት ወጥተው በኢኮኖሚው ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በዋነኝነት ደግሞ በኢንዱስትሪያል ፓርኮች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በመሥራት ላይ ይገኛል። ሆኖም በክልሉ የሚገኙ ስደተኞች ከክልሉ ነዋሪዎች በመብለጣቸው ሚዛኑን እንዳይዛባ ስጋት አላቸው።

ከቅርብ ግዚያት ወዲህ በሁለቱ ትልቅ ብሔሮች በአኙዋክ እና ኑዌር በጣም ብዙ ግጭቶች ተከስተዋል። ለግጭቱ መንስኤ የሆነው የክልሉ ተፈጥሮአዊ ባለቤቶች አኙዋኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሬታቸውን በመወረሩ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያው ጠቁመዋል። ከ20 ዓመት በፊት የአኙዋኮች ቁጥር ይበዛ የነበረ ቢሆንም የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ቁጥራቸው ከ400 ሺሕ በላይ የሆኑ ኑዌሮች በስደተኞች ካምፕ ይገኛሉ። ስደተኞቹ በአዋጁ መሠረት እስከ ዜግነት የማግኘት መብት የሚያገኙ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የአኝዋክ ብሔረሰቦች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ባለሙያው ጠቁመዋል።

ሌላው ከአኙዋክ ብሔረሰቦች የሚነሳው ቅሬታ ኑዌሮች በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት እያገኙ በመሆኑ የተሻለ ሀብት እያፈሩ እንደሆነና የተሻለ የሥራ ዕድል እየተመቻቸላቸው መሆኑና፤ በአንፃሩ ደግሞ አኝዋኮች በገዛ መሬታቸው እየተገፋና አናሳ እየተደረጉ እንደሆነ ቅሬታ ያቀርባሉ። በመጨረሻም ባለሙያው መሰል አዋጆች ሲወጡ ከሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በአግባቡ ማወያየት እንደሚያሰፈልግ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here