የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ ፍትሓዊ አይደለም ተባለ

0
683

የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ወስደው ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡ ተማሪዎች የምደባ ሒደት ፍትሓዊነቱ እንደሚያጠያይቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ። በትምህርት ሚኒስቴር ከወጣው የምደባ መመሪያ ውጭ ብልሹ አሰራሮች እንደሚስተዋልበትም ተጠቁሟል። በሚኒስቴሩ ላይ በርካታ ቅሬታዎች እንደሚነሱ የገለጸው ምክር ቤቱ ማብራሪያ እንደሚፈልግም አሳስቧል።

የትምህርት ሚኒስቴር የግማሽ አመት የዕቅድ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ከምክር ቤቱ ለቀረቡት ጥያቄዎች ሚንስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል። ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምደባ ጋር በተያያዘ በዝምድናና በገንዘብ የሚፈጸመ ተማሪዎች ምደባ አለ የተባለ ሲሆን ይሕም ፍትሓዊነቱን አዛብቷል በሚል ከምክር ብቱ አባላት ጥያቄ ቀርቧል።

ሚንስትሩ ምላሽ ሲሰጡ ሚንስቴሩ የተማሪዎችን ምደባ የሚሰራው በውጤት፣ በፍላጎት ወይም በምርጫቸው እና በ40/60 ድርሻ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል። በውጤታቸው ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች የመጀመሪያ ምርጫቸውን እንደሚያገኙ የገለፁት ሚንስትሩ በኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በምርጫ ከሞሏቸው ከፍተኛ ተቋማት የመጀመሪያ ምርጫቸውም ባይሆን በቀጣይነት በተመረጡት ላይ ይመደባሉ ብለዋል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች በክልላቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ የሚደረግበት አሠራር እንዳለ ጥላዬ አብራተዋል።

በምደባ ላይ በዝምድናና ገንዘብ ሳይቀር ይሰራል ስለሚባው አሻጥር ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ የሚታወቅ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሩ ችግሩን ለመፍታት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚተገብሩም ለምክር ቤቱ አስርድተዋል።

ሚኒስቴሩ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ማበረታቻ ከማድረግ ባሻገር፣ ለሚያጠቡ እናቶችና በፆታ ተመሳሳይ ለሆኑ መንትዮች በልዩ አሠራር እንደሚመድብም ታውቋል።
ሚንስትሩ ጥላዬ (ዶ/ር) ከተማሪዎች ምደባ ጋር በተያያዘ በ2011 በጀት ዓመት 149 ሺሕ ተማሪዎች በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመደባቸውን አስታውሰዋል። በምደባው ሒደት ላይም 788 ቅሬታዎች ወደ አገር ዐቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ቀርበው ምላሽ ማግኘታቸውን አሳውቀዋል።

በተያያዘ ባለፈው በጀት ዓመት 20 ሺህ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲመደቡ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ይህም ተቋሙ መቀበል ከሚችለው ሦስት ሺሕ ተማሪ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ መሆኑን ሚንስትሩ ተናግረዋል። እንዲህ የተማሪዎቹና የዩኒቨርሲቲው ፍላጎት በተራራቀበት መንገድም የመረጥኩት ዩኒቨርሲቲ አልደረሰኝም የሚሉ ቅሬታዎች እንደሚነሱ ይሰማል።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናዎች ላይ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ሆኖ ሳለ፣ ስለምን አሁን ላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ የሚስተዋለው ሥነ ምግባር ከውጤታቸው የራቀና ለየቅል ሆነ የሚል ጥያቄ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

ሚንስትሩ ሲመልሱም ችግሩን ሚኒስቴሩም የሚውቀውና በተደጋጋሚ የሚያነሳ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡ የሥነ ምግባር መመሪያውን በስብከት መልክ (‹‹ኢንዶክትሪኔሽን››) ወደ ተማሪዎች እያሰረፅን እንሰራለን ሲሉ ተደምጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here