በ100 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ሆስፒታል ለመገንባት ባለሀብቶች ጥያቄ አቀረቡ

0
394

• በአጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሊያስወጣ ይችላል ተብሎ ተገምቷል

በዓይነቱ ልዩ የሆነ በ100 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ሆስፒታል እና የጤና ማዕከል ለመገንባት 15 የግል ባለሀብቶች ለመንግሥት ጥያቄ አቀረቡ።
በአጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሊያስወጣ ይችላል ተብሎ የተገመተው ቪዥን አፍሪካ የተባለው ማዕከሉ፤ የግንባታው ወጪ ከመንግሥት ጋር በአጋርነት በመሥራት ለመሸፈን እና ከውጭ አበዳሪዎች ለማግኘት መታሰቡን ድርጀቱ አሳውቋል። ይሁን እንጂ፤ የፋይናንሰ ምንጩ ከየት እንደሚገኝ በግልፅ ይፋ አልተደረገም።
ለሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታሰበው ማዕከሉ፤ ድርጅቱ በተረከበው በቦሌ ለሚ አይ ሲቲ ፓርክ አካባቢ በሚገኘው መሬት ላይ የሚገነባ ይሆናል።

የሆስፒታሉ እና የጤና ማዕከል ዲዛይን የተጠናቀቀ ሲሆን 5000 አልጋዎች እና ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን የጠበቀ 3ሺሕ ተማሪዎች መያዝ የሚችል የጤና ኮሌጅ እንዲኖረው ታቅዶ ለመንግሥት ጥያቄ የቀረበ መሆኑን መረዳት ተችሏል። በተጨማሪም፤ ማዕከሉ በውስጡ የጥናትና ምርምር፣ የተማሪዎች ዶርም፣ አነስተኛ የእንስሳት ፓርክ፣ ላይበረሪና የገበያ ማዕከላት እንዲኖሩት ታቅዷል።

በተጨማሪም የባሕል ማዕከል፣ ሚውዚየም፣ ሆቴሎች እና የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅቶች በውስጡ እንደሚኖሩት ድርጅቱ አስታውቋል።
ከመንግሥት ተባብሮ አብሮ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ የፈረመው ድርጅቱ፤ በግማሽ ቢሊየን በር ካፒታል ሲሆን መሥራቾቹ 15 ከተለያዩ ዘርፎች የተወጣጡ ባለሙያዎች ይገኛሉ። በድርጀቱ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ዮሴፍ ግደይ የተባሉ ባለሀብት መሆናቸውን ምንጮች ገልፀዋል።
በሦስት ደረጃዎች ይገነባል ተብሎ የታቀደው የጤና ማዕከሉ፤ የመጀመሪያ ደረጃ በአራት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሏል። ኹለተኛው ደረጃ ደግሞ እስከ 2018 ለማጠናቀቅ የታሰበ ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ በ 2022 ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

የታሰበው ኢንቨስትመንት የወጣበት ወጪ ለመመለስም 3 ዓመት ተኩል በቂ እንደሆነ የገለፀው ድርጀቱ 40ሺሕ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታቅዷል። ይሁን እንጂ፤ መንግሥት ለድርጀቱ እስካሁን የመግባቢያ ሰነድ የዘለለ አብሮ ለመሥራት ይሁንታ እንዳልሰጠ ምንጮች ገልፀዋል።

የጤና ማዕከሉ በውጭ አገራት ለሕክምና የሚወጣውን ወጪ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ ለውጭ ምንዛሬን ከማዳን አንፃር ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሮጀክቱን ስፋት እና ጥልቀት የተረዱት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢንቨስትመንት ባለሙያዎች እንደገለፁት፤ አሁን መንግሥት ካለው አቅም ማነስ እና የፋይናንስ እጥረት ጋር ተያይዞ፤ እጅግ በጣም ትልቅ የሆነ ይህን ዓይነት ፕሮጀክት ለመተግበር አዳጋች ነው ብለዋል።

የፋይናንስ ምንጩን በግልፅ አለመጠቀሱም የፕሮጀክቱን ተፈጻሚነት አጠራጣሪ ያደርገዋል ሲሉ በአማካሪነት ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የሠሩ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here