የቅድመ ምርጫ 2012 ውዝግብ ‘በወቅቱ ይካሔድ’ ወይስ ‘ይራዘም’?

0
752

መቶ በመቶ አንድ የፖለቲካ ድርጅት “ያሸነፈበት” ምርጫ በተካሔደ ማግስት አገሪቷን የሚንጥ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። ተቃውሞውን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ ውስጥ በተነሳ የልዩነት ማዕበል “የለውጥ ቡድን” እየተባለ የሚጠራው አካል አሸንፎ ወጥቷል። ለውጡን ተከትሎ የፖለቲካ ምኅዳሩ ቢሰፋም አገር ዐቀፍ ሰላምና መረጋጋት ገና ሙሉ ለሙሉ አልተሳካም። ዛሬ ላይ ቀጣዩ አገር ዐቀፍ ምርጫ ሊካሔድ 15 ወራት ብቻ ይቀሩታል። “ምርጫው ቶሎ በደረሰ” የሚሉ ቡድኖች ያሉትን ያክል፥ “የምርጫው ጊዜ እየቀረበ ነው” ሲባል አገራዊ አለመረጋጋቱ ያገረሻል የሚል ስጋት የሚያባትታቸውም በርካቶች ሆነዋል። ይህንን ተከትሎ ምርጫ ተካሔደ ለማለት ብቻ ማካሔዱ ፋይዳ የለውም፣ የአገር መረጋጋት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ይቀድማል የሚሉት “ምርጫው ይራዘም” ሲሉ፣ ይህንን ለማድረግ ሕገ መንግሥታዊም ይሁን ሕጋዊ መንገድ የለም፣ ምርጫው “በማንኛውም ሁኔታ በወቅቱ መካሔድ አለበት” እያሉ ነው። የእነዚህን ሁለት ወገኖች መከራከሪያ ነጥቦች፣ የአፍሪካ አገራት እና የኢትዮጵያ የምርጫ ልምዶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ታምራት አስታጥቄ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕስ አድርጎ አቅርቦታል።

ኢትዮጵያ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የፖለቲካ ለውጥ እያስተናገደች ነው። እስካሁንም ድረስ ያልጠሩ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለመክፈት የፖለቲካ አመራሮቹ ፈቃደኝነት ተስተውሏል። ብዙኃን መገናኛዎች በነጻነት እየሠሩ ነው፣ የሲቪል ማኅበራት መልሰው እንዲደራጁ ሕግጋቱ እየተከለሱ ነው፣ የምርጫ ሕግጋት እየተሻሻሉ ነው፣ የፖለቲካ ድርጅቶችም በነጻነት እንዲደራጁ ካለፉት 14 ዓመታት ወዲህ የተመቻቸ ጊዜ አግኝተዋል።

ይሁን እንጂ “አገሪቱ ስትናጥበት ከነበረው ሕዝባዊ አመፅ ሙሉ ለሙሉ አልወጣችም። ሁሉም አካል በእኩል ደረጃ ለምርጫ አልተዘጋጀም። አገር ዐቀፍ ምርጫ በዚህ ወቅት ማዘጋጀት በመረጋጋት ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ወደ አለመረጋጋት እንድትመለስ መዳረግ ነው” የሚሉ በአንድ ወገን፣ “ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምሰሦ ነው፤ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ካልተካሔደ ለአምባገነንነት በር የመክፈት ያክል ይቆጠራል” የሚሉት በሌላኛው ወገን ሆነው “ምርጫው ይራዘም”፣ “የለም! በወቅቱ ይካሔድ” እያሉ እየተሟገቱ ነው። በርግጥ ምርጫው በወቅቱ ቢካሔድ የሚፈጠረው ችግር ምንድን ነው? ይራዘም የሚሉት ወገኖችስ መከራከሪያ ነጥባቸው ምንድን ነው? የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ቀደምት የምርጫ ተሞክሮዎችስ ምን ይነግሩናል?

ምርጫ እና ዴሞክራሲ
ምርጫ መሠረታዊው የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆኑት አንኳር መርሖዎች መካከል ከፊተኛው መሥመር ይሰለፋል። ይሁንና የዴሞክራሲ ስርዓቶች የሚመዘኑት ምርጫ ወቅቱን ጠብቀው በማካሔዳቸው ብቻ ሳይሆን በምርጫዎች መካከል ባለው ጊዜ ሕዝባዊ ተሳትፎዎችን በሚያስተናግዱበት ሒደት ነው። የዴሞክራሲ መርሕን የሚያከብሩትም ሆኑ የማያከብሩት መንግሥታት እና የፖለቲካ ስርዓቶች ምርጫን እንደቅቡልነት መግዣ ይጠቀሙበታል። ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ‘በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ምርጫ ለምን ተግባር ይውላል?’ የሚለው ነው።

ምርጫ በተለያዩ ስርዓተ መንግሥታት ውስጥ ለተለያዩ ተግባራት ሊውል እንደሚችል ዋጅታሲስ ዋልዳማር የተባሉ ጸሐፊ “Functions of Election in Democratic System” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ዘርዝረው አስቀምጠዋል።

እንደአጥኚው፣ ፓርላሜንታዊ ስርዓት ውስጥ (ኢትዮጵያም በሕግ ደረጃ ይህንን ነው የምትከተለው) ምርጫ ፖለቲካዊ ሥምምነት ማስገኛ ሲሆን ብዙኃኑ የፓርላማውን አብላጫ በያዙት ሰዎች በተዘዋዋሪ በሚመረጠው አካል እንዲመራ ያስችላል። በሌላ በኩል፣ ፕሬዘዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ደግሞ የተረጋጋ አገረ መንግሥት ለመመሥረት እንዲሁም የተቃዋሚ ተወካዮች ተፅዕኖ ከግምት እንዲገባ ያስችላል። በሌላ በኩል በአኀዳዊ የመንግሥት አስተዳደር ምርጫ አካባቢያዊ ተመጣጣኝ ውክልና ላይ ትኩረት አይሰጥም። በተቃራኒው ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ውስጥ የምርጫ ዐቢይ ግብ ውክልናን በክልል ደረጃ ማረጋገጥ ነው።

ሌላው የተለያዩ የምርጫ ተግባራት ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩት ጉዳዮች መካከል ምርጫው የሚካሔድበት አግባብና ምርጫውን የሚያካሒደው አካል የሚከተለው የምርጫ መመሪያ ናቸው።

የአብላጫ ድምፅ እና ተመጣጣኝ ውክልና (ድምፅ) የምርጫ ዓይነቶች የምርጫው ተግባርን ይወስናሉ። ይህም ተለያዩ የምርጫ ሥነ ስርዓቶችን ለመተግበር አመላካች ይሆናሉ።

ምርጫ እስከምን ድረስ?
ምርጫና ዴሞክራሲ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አጠያያቂ ጉዳይ እንዳልሆ በዴሞክራሲ ላይ የተጻፉ ድርሳናት ያወሳሉ። በብዙዎች በተለይ በአህጉራችን የሚገኙ አገራት ምርጫ ማካሔድ የዴሞክራሲ ግብ ተደርጎ ሲወሰድ መታዘብ የተለመደ መሆኑ ይጠቀሳል። ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ መካሔዱ ብቻ ግን ዴሞክራሲን እንደማያረጋግጥ የአህጉራችን ተሞክሮዎች ራሳቸው ምሣሌ ናቸው።

“International Institute for Democracy Electoral Assistance” የተባለ ተቋም “Election, Electoral Systems and Party Syatems” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ በዓለማችን 132 አገራት ውስጥ ምርጫዎች ተካሒደዋል።

ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊሲ ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክትር ናቸው። አዲስ ማለዳ በምርጫና ዴሞክራሲ መስተጋብ ዙሪያ ላነሳችላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ከዴሞክራሲ ዋና ዕሴቶች መካከል ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የሚባለው አንዱ ነው። ይሔ እንዲሆን ደግሞ ታሳቢ የሚደረጉ ነገሮች (‘አሰምፕሽንስ’) አሉ” ይላሉ። ይኸውም “እያንዳንዱ ዜጋ ሙሉ መረጃ አለው፣ አገሪቱ ውስጥ የሚደረገውን ፖለቲካ ያውቃል፣ አመክኗዊ ነው” ወዘተ. የሚሉትን በምርጫ ወቅት ቅድመ ታሳቢ የሆኑ ሁኔታዎችን ለአብነት ጠቃቅሰዋል። ከዚህም አለፍ ሲል ዴሞክራሲ “ከማኅበራዊ መደብ (‘ሶሻል ክላስ’) ጋር እና ከትምህርት ደረጃ ጋርም ይያያዛል” በማለት አንዳንድ በጉዳዩ ዙሪያ የተጻፉ ጽሑፎች ይጠቃቅሳሉ። ይህም በቂ መረጃ የሌላቸው ዜጎች የሚያደርጉት ምርጫ ወደሚፈልጉት ዓይነት ስርዓት ላይመራቸው እንደሚችል ማሳያ ነው።

ብርሃኑ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎችም ታሳቢ ተደርገው ምርጫ ከተካሔደ፥ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ይኖራል ማለት ነው በማለት ያስረዳሉ። በተቃራኒው “ቅድመ ታሳቢዎቹ ባልተሟሉበት እና የዴሞክራሲ አረዳድ ዝቅ ባለበት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ‘ኤቶስ’ (ልማድ) ባልተፈጠረበት ሁኔታ ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም” ሲሉ ይገልጻሉ።

ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱ እኩል ግምት ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም በሒደቱ ውስጥ መሠረታዊ መብቶችን ለመለማመድ ዕድል ይኖራል። በዚህ ረገድ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመደራጀት መብቶች እንደ አብነት ሊታዩ ይችላሉ።

ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ውጤቱ ሁሌም ጥሩ መሪ ማስገኘት ብቻ አይደለም። ብርሃኑ የጀርመኑን አዶልፍ ሒትለር እና የአሜሪካኑን ዶናልድ ትራምፕን በመጥቀስ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሁሌም የምንፈለገውን ውጤት ያስገኛል ማለት እንዳልሆነ ያስታውሳሉ።

ምርጫ በአፍሪካ
ወንድወሰን ተሾመ (ዶ/ር) “ዴሞክራሲና ምርጫ በአፍሪካ፡ ሒሳዊ ትንተና” በሚል ርዕስ በ2008 በ”International Journal of Human Societies” ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሐፍ በአፍሪካ ውስጥ ‘ዴሞክራሲያዊ’ ምርጫን በተመለከተ ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምሮ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሞክረዋል።

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ያወጡበትን እ.አ.አ. በ1960ዎቹና 1970ዎቹ “የመጀመሪያው ነጻነት” በሚል የሰየሙት ሲሆን አዳዲሶቹ ነጻ የአፍሪካ መንግሥታት መምጣት ጋር ተያይዞ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉን የመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ፓርቲ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ያደረጉበት መሆኑን ያስቀምጣሉ።

ዘመኑ በምርጫ ወደ ሥልጣን መምጣት ብዙም ያልታየበት መሆኑን ጠቁመወል። ሕዝቡም ሆነ መሪዎቹ ስለዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲ ለመገንባት ስለሚካሔደው ምርጫ እምብዛም ግንዛቤው አልነበራቸውም። ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣትን የሚያጣጥሙበት ወቅት በመሆኑ ጭምር አሳሳቢነቱ አልታያቸውም ነበር። ምናልባትም ስለ ዴሞክራሲ ማውራት የቅንጦት ያክል የሚታይበት ጊዜ ነበር በሚል ቢቀመጥ ማጋነን እንዳልሆነ ተጠቅሷል።

በአፍሪካ ፈጣኑ ዴሞክራሲያዊ ሒደት የጀመረው “ሁለተኛው ነጻነት” ተብሎ በተሰየመውና እ.አ.አ. የ1991ዱን የቤኒን ምርጫ ተከትሎ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አጋማሽ ውስጥ የታየው መነቃቃት ነው።

ወንድሰን በጽሑፋቸው እንደሚያመለክቱት በዚህ ወቅት የብዝኃ ፓርቲ ምርጫ በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ውስጥ ተካሒዷል። እነዚህ ሽግግሮች የነጻነትት እጦት፣ ዝቅተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ (ከምርጫ ወቅት በስተቀር)፣ የግለሰብ ነጻነት መጥበብ፣ እና የጥቂት የልኂቃን ቡድኖች እጅ የፖለቲካ ሥልጣን ደጃፍ መከማቸት መገለጫዎዎቹ ወደሆኑት “ውሱን ዴሞክራሲ” ስርዓት አምርቷል።

ምርጫ ማካሔድ በራሱ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ይሁንና ቁልፉ የዴሞክራሲ ቅቡልነት ማግኛ መንገድ አይደለም። ብዙዎች በአፍሪካ ውስጥ የሚካሔዱት ምርጫዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚያሥማሙትን የነጻና ፍትሐዊ ምርጫ መሥፈርት አያሟሉም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ አገራት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የተደበላለቁበት ቢሆንም፥ ብዙዎች የአፍሪካ አገራት የየአገራቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምርጫን እንደዋነኛ ስልት ይቆጥሩታል።

በጋና፣ ናይጄሪያ፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሔድ የሚታወቁና ጥሩ አርአያ የሚሆኑ አገራት ሲሆኑ በሌላ በኩል ምርጫን እንደ ሥልጣን ማመንጫ ብቻ በመጠቀም ብዙ አገራት ይታማሉ። ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሔደውን የካሜሮን ምርጫ ለሰባተኛ ጊዜ ራሳቸውን እጩ አድርገው ላቀረቡትና ላሸነፉት ፕሬዘዳንት ፖል ቢያ ምርጫን ለምን ግብ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ግልጽ ነው። የዋነኛው ተቋዋሚ ፓርቲ ‘ካሜሮን ሬዚስታንስ ሙቭመንት’ መሪ የሆኑት ማውሪስ ካማቶ (ፕሮፌሰር) በዚህ ሳምንት ማክሰኞ፣ ጥር 21 የመታሰራቸው አንድምታ ብዙ መገናኛ ብዙኃን እንደሚዘግቡት ከምርጫው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነው። ይህ የካሜሮን ምርጫ፣ ምርጫ በአፍሪካ የት ድረስ እንደሚሔድ ጥሩ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ምርጫ በኢትዮጵያ
ከ1966 ዓብዮት በኋላ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው ደርግ የአንድ ፓርቲ ፖለቲካን ያስተዋወቀ ሲሆን ሥልጣን ለይመስሙላም ቢሆን በ‘ምርጫ’ እንደሚገኝ ፍንጭ ሰጥቷል። ከአታካቹ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ወታደራዊ መንግሥት በኢሕአዴግ አሸናፊነት ሥልጣን ተቆጣጥሮ ሲመጣ በ1986 ምርጫ ቦርድ አቋቁሟል። በ1987 የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ፥ የመጀመሪያው እና በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫ ተካሒዷል።

ምርጫ አስፈፃሚው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ ጀምሮ እስካሁን 5 ተከታታይ ምርጫዎች በ1987፣ 1992፣ 1997፣ 2002 እና 2007 ተካሒደዋል። ሁሉም ምርጫዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መሥፈርቶችን የሚያሟሉ ሳይሆኑ እንዲሁ ለይስሙላ የተካሔዱ እንደነበሩ ብዙዎች ሲተቹ ይደመጣል። የተለየ ነበር የሚባለው ምርጫ 1997 ብቻ ነው።

ለሦስተኛው ጊዜ የተካሔደው ብሔራዊ ምርጫ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በንፅፅር ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት የተሳተፉበት፣ የመንግሥት ሚዲያዎችን ጨምሮ (ለአጭር ጊዚያት ቢሆንም) ቅስቀሳ የተደረገበት፣ በንፅፅር ቅድመ ምርጫውም ሆነ የምርጫው ዕለት ዴሞክራሲያዊ የነበረበት መሆኑን ብዙዎች ዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች (የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ) የመሰከሩለት ሲሆን፥ ድኅረ ምርጫ ሒደቱ ግን አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት የመራበት፣ ገዢው ፓርቲ አፈሙዙን የተጠቀመበት፣ በውድድሩ ብዙ ድምፅ ያገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ እስር የተጋዙበት እንዲሁም ገርበብ ተደርጎ የነበረው የዴሞክራሲ በር ዳግም የተከረቸመበት ሆኖ አልፏል።

በምርጫ 2002 አንድ የተቃዋሚ ፓርቲና አንድ የግል ተወዳዳሪ ብቻ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ በ2007 በተደረገው ምርጫ ግን ምክር ቤቱ መቶ በመቶ የኢሕአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ‘መፈንጫ’ እንዲሆን ተደርጓል በሚል ብዙ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች በሰፊው ተችተውታል።

በተለይ የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ከታወጀ መንፈቅ በኋላ በተደረጉት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት በአደባባይ እንዲሁም በመሪ ድርጅቱ ኢሕአዴግ ውስጥ ‘የሞት ሽረት’ የተባለለት ትግል ተደርጓል። በዚህም ገዢው ቡድን ሳይቀየር፣ አመራሮቹን አገራዊ ማሻሻልን እንደ ራዕይ ባነገቡ ወጣት አመራሮች ሊተካ ችሏል።

ሕዝባዊ ተቃውሞውና የገዢው ግንባር ውጫዊ ተፅዕኖ እና ውስጣዊ ‘የለውጥ’ ፍላጎትን ተከትሎ በዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው “የለውጥ ኃይል” ተብሎ የሚጠራው ቡድን፥ ኢትዮጵያ የማትታወቅበትን የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ወንጀል ከሚጠረጠሩ የቀድሞ የደኅንነትና ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የተወሰኑትን በማሰር፣ ከአገር ርቀው በስደት የሚኖሩትን ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ እና ሌሎችም ብዙ የለውጥ እርምጃዎች የለውጥ ተስፋ ድጋሚ እንዲፈነጥቅ አድርጓል።

የለውጡ ድክመት ተደርጎ የሚወሰደው ለውጡ በላይኛው አመራር ብቻ ነው የመጣው የታችኛውን የመንግሥትም ሆነ የገዢ ፓርቲውን መዋቅሮች ምንም አልነካውም የሚለው ቅሬታ ነው። በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ነዋሪዎችን የማፈናቀል፣ የግድያ፣ የአካል ጉዳት ማድረስ፣ የመንገድ ላይ ፍርድ እና መሠል ሕገ ወጥ ድርጊቶች የአገሪቱን ሰላም ወደከፋ ሁኔታ እንዳይወስዱት ተሰግቷል። የፌደራል መንግሥቱ ልፍስፍስ ሆኖ መታየት ለሰላምና መረጋጋት መታጣቱ ዋናው ምክንያት ነው የሚሉትን ያክል፣ ይህ ሁኔታ እልባት ሳያገኝ ቀጣዩን እና በመደበኛ ጊዜው (ግንቦት 2012) የሚካሔደውን ምርጫ ማስተናገድ ማለት በእሳቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ቁጥር እየበረከተ ነው።

ይህንን የለውጥ ሒደት እየመራ ያለው የዐቢይ አስተዳደር ራሱን “የሽግግር መንግሥት አድርጋችሁ ውሰዱኝ” እያለ ነው። በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደሚመሠረተው ቀጣይ ስርዓት ‘እኔው አሻግራችኋለው’ ማለታቸው ለዚህ አብነት ነው። ይሁንና ‘በፊትም ነበረው ኢሕአዴግ አሁንም ያለው ኢሕአዴግ’ በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ ብዙዎች ይቃወማሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም ደግሞ አዲስ የተመሠረተ እና ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናዮች ያሳተፈ ምክር ቤት በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲሁም አመፅ ተቀስቅሶበት የነበረው ፓርቲ “ተመርጠዋል ያላቸው” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሁንም እዚያው ባሉበት ነባራዊ እውነታ “የሽግግር መንግሥት” ተመሥርቷል ማለት አይቻልም ይላሉ።

ምርጫው መቼ ይካሔድ?
ቀጣዩን አገር ዐቀፍ ምርጫ በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ምሁራን ኹለት ዓይነት አቋም ሲያንፀባርቁ ይሰማል። በአንድ ወገን ምርጫው በጊዜ ገደቡ መሠረት መካሔድ አለበት፣ በተቃራኒው ደግሞ ጊዜው ቢራዘም ይሻላል የሚሉ ናቸው።

የኦፌኮ ሊቀመንበር እና የመድረክ ከፍተኛ አመራር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) “ምርጫው በተሻለ ፍጥነት መካሔድ” እንዳለበት ሲያስረዱ “27 ዓመታት በአምባገነንነት ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ አሁን ካለንበት የበለጠ አመቺ ጊዜ ሊፈጥር አይችልም” በማለት ከአዲስ ማለዳ “ምርጫው የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ ይራዘም ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሥራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲው የሕግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጥበበ ሰይፈ ምርጫው በሕግ በተደነገገው መሠረት በየአምስት ዓመቱ መካሔድ አለበት የሚል መከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ። እንደ መረራ ሁሉ ሰይፈ በኢትዮጵያ ምርጫው እንዳይካሔድ የሚያደርጉ ተጨባጭ ሁኔታዎች እንደሌሉ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አበራ ደገፉ (ዶ/ር) እንዲሁም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር መኮንን ፍሰሐ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ በተግባር አለ ብለን ካሰብንና አገሪቱ በሕገ መንግሥቱ እየተመራች ነው እስካልን ድረስ ሕገ መንግሥቱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እንደሚኖር ደንግጓል፤ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ሕጎች ስለምርጫ መራዘም የሚያወሩ ድንጋጌዎች በሌሉበት ሁኔታ የምርጫ ይራዘም ጥያቄ በሕግ ፊት ውሃ እንደማያነሳ አስረግጠው ይናገራሉ።

በሌላ በኩል የአርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ኤፍሬም ማዴቦ ፓርቲያቸው ለ2012ቱ ምርጫ መሠረታዊ ሥራዎችን እየሠራ ያለበትን ሁኔታ ቢናገሩም፥ መሬት ላይ ያለው ነገር ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። ኤፍሬም “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ ማካሔድ ይቻላል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ግን ወሳኝ ጥያቄ መሆኑንና በጥንቃቄ መመለስ የሚባው ጉዳይ መሆኑን ያሠምሩበታል። ኤፍሬም “የማሻሻያ ሥራዎች እንዳሉ ሳይዘነጋ፥ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማስፈፀም የሚችሉ ተቋማት በሌሉበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ኢትዮጵያዊነትን ወይም ዜግነትን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የፖለቲካ ሥራ መሥራትና ሕዝብ ማደራጀት ባልቻሉበት ሁኔታ፣ የፌደራል መንግሥትን የማይታዘዙ ክልሎች ባሉበት አገር፣ ሚሊዮኖች በተፈናቀሉበት፣ በብዙ የአገሪቱ ክፍል የሰላምና መረጋጋት እጦት ባለበት ሁኔታ፣ ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት አውድማ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው ምርጫ የሚካሔደው?” በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ በጥያቄ መልሰዋል። ይህ በመሆኑም “የእኛ አቋም ምን ጊዜም ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ሁኔታ ምርጫ ማካሔድ የሚያስችል አይደለም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

የአብኑ ጥበበ ግን ኤፍሬም የዘረዘሩዋቸውን ከሰላምና ደኅንነት ጋር የተያያዙትን ሥጋቶች አይቀበሉም። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የሰላምና ፀጥታ ችግር እንዳሉ አምነው መንግሥት ለተፈጠሩት ችግሮች እየወሰደ ባለው እርምጃ ምርጫ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ የሰላምና መረጋጋት ሥጋቶችና ችግሮች አሁን ባሉበት እንደማይቀጥሉና ችግሮቹ መፍትሔ ያገኛሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

አበራ በበኩላቸው “በመጀመሪያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገ ያለው ምንድን ነው?” የሚለው ቁልፍ ጥያቄ መመለስ ያለበት ጉዳይ መሆኑን አስምረውበት፥ ጥርጣሬያቸውንም መልሰው ለውጡን በሕዝባዊ ግፊት ተገዶ አምጥቶታል በሚባለው ኢሕአዴግ ላይ አሳርፈዋል። “በእንደዚህ ዓይነት ለውጥ የማይጠቀሙ ወይም ጥቅማቸው የተነካባቸው በኢሕአዴግ አመራር ላይ የሚገኙ፣ ነገር ግን ለውጡ ሳንካ እንዲገጥመው የሚሠሩ ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት በጥርጣሬ ያነሱት አበራ “ምናልባትም ኢሕአዴግ ለራሱ የሚመች ሁኔታ እስኪፈጠር መረጋጋቱን ላይፈልግ ይችላል” በሚል ለጥርጣሬያቸው ግምታዊ ምላሽ በማስቀመጥ “[ኢሕአዴግ] አሁን መፍጠር ያልቻለውን ሰላምና መረጋጋት መቼ ሊፈጥር ነው?” በሚል መልሰው ይጠይቃሉ።

አብን ለቀጣዩ ምርጫ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታወሱት ጥበበ፥ በተለያዩ ቦታዎች በመንቃሳቀስ የፖለቲከ ሥራ እንዲሁም ሕዝብን የማደራጀት ሥራ አጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውሰዋል። “በተለይ ከውጪ አገር የተመለሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን ዝግጅት ባለማድረጋቸውና እያደረጉም ባለመሆናቸው ምርጫው እንዲራዘም ይፈልጋሉ” በማለት የአብኑ ጥበበ ሰይፈ የመጪውን ምርጫ “ይራዘም” ጥያቄ አጣጥለውታል።

ኤፍሬም በበኩላቸው “ጉዳዩ የአገር ኅልውና ጉዳይ በመሆኑ ከማንኛውም ፓርቲ በላይ ነው” በማለት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል። መጪውን ምርጫ በተመለከተ ኤፍሬም “እንደከዚህ ቀደሙ ጊዜ ጠብቆ ብቻ የሚካሔድ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወዴት አቅጣጫ እንደምትሔድ የሚወስን ትልቅ ምዕራፍ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ይገባዋል። የአገሪቱ ሰላም፣ የተቋማት መብቃትና እንደዚሁም አንድ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ መሟላት ያሉባቸውን መሥፈርቶች አሟልቶ መካሔድ ይገባዋል” ሲሉ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።

የሕግ መምህሩ አበራ የተቋማት ግንባታም ሆነ ዴሞክራሲ በአንዴ ተሠርቶ የሚያልቅ ሳይሆን በሒደት ውስጥ የሚያልፍ መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል።

መደምደሚያ
የሕግ መምህሩ አበራ “መንግሥት ማድረግ ያለበት ሁሉም ፓርቲዎች ቢሯቸውን ከፍተው፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ፣ ሚዲያዎች የሚሠሩበት ሁኔታ መፍጠር፣ የሲቪል ማኅበራት እንዲደራጁ ማድረግ ነው” ሲሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። “የምርጫ መራዘም ምንም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም” ያሉት ሰለሞን “በሰበብ አስባብ ምርጫ ማራዘም ቅቡልነትን ከማሳጣት በሻገር በሌሎች አገራት እንደሚታየው ለአምባገነን መንግሥት መፈጠር መሠረት ሊሆን ይችላል” ሲሉ በማስጠንቀቅ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

በሌላ በኩል የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ምርጫ መካሔድ ያለበት ተካሒዷል ለማለት ብቻ መሆን እንደሌለበት በማሳሰብ ምርጫ መራጩን በቂ መረጃ እንዲኖረው ማድረግን የመሳሰሉ ቅድመ ታሳቢ ሁኔታዎች ተሟልተው መካሔድ እንዳለበት ይጠቁማሉ።
ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ በፊት ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱት ብርሃኑ “በፓርቲዎች ምን ያክል የዳበሩ አማራጭ ፖሊሲዎች ቀርበዋል? ‘ሕዝቡስ ምን ያክል የሥነ ልቦና ዝግጅት አድርጓል?” ይላሉ። በተጨማሪም “የዴሞክራሲ ተቋማት የሕዝብ አመኔታና ተቋማዊ ብቃትን ያካትታል” በማለት የምርጫው ጊዜ ገፋ ቢደረግ መልካም ነው የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

ምርጫው መራዘሙ የቅቡልነትና ሕጋዊ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ያልካዱት ብርሃኑ፥ በሥምምነት ወይም በፖለቲካ ውሳኔ ምላሽ ቢያገኝ ግን ምኞታቸውን መሆኑን ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here