ዴሞክራሲ ያለ ምርጫ ሊኖር ይችላል?

0
956

“Democracy is vicious cycle of elect and regret” የሚሉ ምሁራን መጥተዋል። መሪዎች ሕዝቦቻቸው መሥማት የሚፈልጉትን ብቻ ነግረዋቸው ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ ግን በሥራቸው መራጮቻቸውን መልሰው እንደሚያስቆጩ ለመናገር ነው ይህ አባባል የመጣው። የአሜሪካ የመጨረሻ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ማምጣቱ ብዙዎችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምርጡን ሰው እንደማያመጣ በድጋሚ አረጋግጦላቸዋል። በርግጥም ዴሞክራሲ የልኂቃኑን ሳይሆን የብዙኃንን ፍላጎትና ምርጫ የሚያሳይ መሆኑን ይህ ምርጫ አሳይቷል። በርግጥም ዴሞክራሲ “ምርጡን ሰው” ለሥልጣን እንደማያበቃ ይታመናል፤ ሆኖም የተለያዩ ድምፆች እንዲደመጡ ዕድል ይሰጣል። ዴሞክራሲ የሚያስፈልገውም በዚህ ምክንያት ነው።

ዊንስተን ቸርቺል “ዴሞክራሲ ከሌሎች የመንግሥት ስርዓቶች አንፃር ባይታይ ኖሮ አስቀያሚ ስርዓት በሆነ ነበር” ብለው ያውቃሉ። በዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ አምባገነን የሆኑ ብዙኃን ናቸው፤ በዚሁ መንገድ ሥልጣን ከተቆጣጠሩት መካከል ፋሺስቱ ሙሶሎኒ እና ናዚው ሂትለር ይገኙበታል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አምባገነን መሪዎችን የሚያፈልቀው መራጮች በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ስለሚካሔድ ነው። መራጮች ስለሚመርጡት ግለሰብ እና ድርጅት በቂ መረጃ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ይሁን እንጂ ይህ ዕሳቤ እውነት የማይሆንባቸው አጋጣሚዎች በርካቶች ናቸው። ለዚህ መፍትሔው ተቋማዊ ‘ቁጥጥር እና ሚዛን’ (‘ቼክ ኤንድ ባላንስ’) መኖር ይኖርበታል፣ በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን የሚይዙ ፖለቲከኞች ሥልጣን መገደብ አለበት። በአሜሪካ ምንም እንኳን “አምባገነናዊ ስብዕና አላቸው” የሚባሉት ዶናልድ ትራምፕ ቢመረጡም፣ ያሻቸውን በመፈፀም ወደ አምባገነናዊነት የሚለወጡበት ተቋማዊ ነጻነቱ የላቸውም የሚለውን መከራከሪያ ለዚህ ማሳያነት ማንሳት ይቻላል።

የሆነ ሆኖ ዴሞክራሲ ያለ ምርጫ አይታሰብም። ምክንያቱም ምርጫ ዜጎች ለሚወክሏቸው ሰዎች ይሁንታ የሚሰጡበት መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ በምርጫ ብቻም ምሉዕ አይሆንም፣ ምክንያቱም በምርጫው አማራጮች መኖር አለባቸው፣ መራጮች ስለመራጮቹ በቂ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል፣ የምርጫ ሒደቱ ነጻ እና ርትዓዊ መሆን አለበት፣ መራጮችም ይሁኑ ተመራጮች በሒደቱ የሚፈሩት አካል መኖር የለበትም። እነዚህ ባልተሟሉበት መንገድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን የይስሙላ ዴሞክራሲ ነው ሊኖር የሚችለው።

በተጨማሪም ዴሞክራሲ በምርጫ ወቅት በሚሆነው ብቻ አይገነባም። ይልቁንም በምርጫዎች መሐል ዜጎች በሚዲያ እና በሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም በሌሎች አማካይነት ወኪሎቻቸውን እና የአስፈፃሚው አካልን የሚፈልጉትን እንዲያደርግላቸው ተፅዕኖ በማሳደር አቅማቸው ልክ ይወሰናል። ስለሆነም ዴሞክራሲ ያለ ምርጫ ባይኖርም፣ በምርጫ ብቻም ሊኖር እንደማይችል መናገር ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here