“ለውጡን የሚመጥን ሥራ ካልሠራን፥ አስቸጋሪ እንደሚሆን በደንብ እረዳለሁ”

0
725

ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። ፊታቸው በፈገግታ የተሞላው፣ ለማነጋገርም ቀለል ያሉት ብርቱካን ቀደም ሲል ዳኛ፣ የቅንጀት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የአንድነት ፍትሕና ዴሞክራሲ ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል። በፖለቲካ ተሳትፏቸው ጎላ ብሎ ከሚነሱት ሴቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፉት ብርቱካን፥ በመንግሥት ከተፈጸመባቸው ተደጋጋሚ እስራት በኋላ ለ8 ዓመታት በሥደት በሰሜን አሜሪካ ቆይተዋል።

በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕዝብ አስተዳዳር ከ‹ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ገቨርንመንት› አግኝተዋል። በአሜሪካ ቆይታቸው ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ባገኙት ምርምር የማድረግ ዕድል (‹ፌሎሺፕ›) እንዲሁም ‹ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ› በተባለ ድርጅት በተመራማሪነት ባገለገሉበት ወቅት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሒደት ያሉ ችግሮች ምን እንደሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና፣ የፓርቲዎች ጠንካራ አማራጭ ሊያቀርቡ አለመቻል ምክንያቶች በሚልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምርምር አካሒደዋል፤ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል፥ በሚጋበዙባቸው መድረኮችም ንግግር አድርገዋል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ፣ ተቋማዊ ማሻሻያና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በተሾሙበት ዕለት ተቋሙ በሠፊው በጥርጣሬ የሚታይ መሆኑን አስታውሰው፥ ተቋሙ በሁሉም አካላት ተዓማኒ እንዲሆን ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩም መግለፆት ይታወሳል። ሹመቱን ከተቀበሉ አጭር ጊዜ ቢሆንም በተጨባጭ የተቋሙን ተዓማኒነት ለመገንባት ምን እያደረጉ ነው?
ብርቱካን ሚዴቅሳ፡ ጊዜው አጭር ቢሆንም በብዙ መልኩ የሚደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች በጅምር ላይ ናቸው። ምርጫ ቦርድ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተዓማኒነት የሚሠምረው የሚሠራቸው ሥራዎች ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሐሳባቸውን ያካተተ፣ ግልጽ አሠራርን በመተግበር ነው ብዬ አምናለው። ተቋማዊ የማሻሻያ ሒደቱም አሳታፊና አማካሪ መሆን አለበት።

እስካሁን ድረስ ከዚህ አኳያ ትኩረት ሰጥተን ሠርተናል ብዬ የማስበው የሕግ ማሻሻያዎች ላይ ነው። ምክንያቱም እነሱ መሠረቶች ናቸው። የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሒደቱ በደንብ እንዲሳተፉ እያደረግን ነው።
ፓርቲዎች በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት መነሻ ሐሰቦች እያቀረቡ ነው። እነሱን በማገዝ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አጋዥ እንጂ አደናቃፊ እንዳልሆንን ለማሳየት እየሞከርን ነው። የሕግ ማሻሻያዎች ማዕቀፍ እንዳለ ሆኖ ፓርቲዎቹ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በማነጋገር እና መፍትሔ በመስጠት እገዛ እያደረግንላቸው ነው።

ሕጉን የማሻሻል፣ ምርጫ ቦርድን በአዲስ መልክ እስከታችኛው እርከን የማዋቀር ሥራ በጣም ተጓቷል ለሚሉት ምላሾት ምንድን ነው?
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የሕግ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ፤ በማሻሻያው መሠረት የቦርድ አባላትም ይሾማሉ። የሕግ ማሻሻያዎቹ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል ነው የሚካሔዱት የሒደቱን ፍጥነት በተመለከተ ለእኛም በፈለግነው ፍጥነት ሄዷል ማለት አልችልም። ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ እንዲወስድ ያደረገው ከፓርቲዎች እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይት በመደረጉ ነው። ይህም ጊዜ እንዲወስድ አድርጓል።

በቶሎ ወደ ማጽደቅ ብትሔድ የሚመለከታቸው አካላት ሐሳብ መካተቱን እርግጠኛ መሆን አትችልም። አሳታፊ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው።
ሌላው ፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይወያዩበት እንደሚታወቀው ፓርላማው መቶ በመቶ በገዢው ፓርቲ እጅ ስለሆነ ከዛ ውጪ ውይይቶች ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው።

የሆነው ሆኖ ለቦርዱ እንቅስቃሴ የሕግ ማሻሻያ መዘገየት ችግር አልፈጠረም ማለት አይቻልም።

መዘግየቱ ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለተ ጊዜ እንዳይካሔድ ተጽዕኖ አይኖረውም?
አሁን ቦርዱ በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገውን የምርጫ ዝግጅት እንዴት ነው ለማድረግ የምችለው ብሎ ውሳኔ የሚሰጠው የቦርዱ አባላት ሲሟሉ ነው። ማሻሻያዎቹ ምን ምን ናቸው? ለአንድ ነጻና የሚታመን ምርጫ ለማድረግ በመሠረታዊ ሁኔታ ማሟላት ያሉብን ነገሮች ምንድን ናቸው? ምን ያክል ገንዘብና ጊዜ ይጠይቃሉ? የሚሉትን ዝርዝር ጉዳዮችን አይቶ ነው ውሳኔ የሚሰጠው። በመሆኑም ቦርዱ መቋቋም አለበት።

ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ አይካሔድም ለማለት የሚቻልበት ደረጃ አይደለም ማለት ነው?
አዎን!

ነፃ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለመካሔደ ገለልተኛና የማስፈጸም ብቃት ያለው ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው የሚያስፈልገው ብለው ያምናሉ?
የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትና ተቋማዊ ብቃት ብቻ በቂ ነው ማለት የሚቻል አይመስለኝም። ከእኛ ተቋም ውጪ ሌሎች ተቋማት በምርጫው የሚኖራቸው አስተዋጽኦ አስፈላጊ ነው፤ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት የሚሳተፉበት ስለሆነ ማለት ነው። ለምሳሌ በምርጫው ላይ ክርክር ቢነሳ ፍርድ ቤት ምን ዓይነት ውሳኔ ይሰጣል፣ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ያሉ የክርክር ሒደት፣ አድሏዊ ያልሆነ የቅሬታዎች አፈታት፣ ተወዳዳሪዎቹ የመወዳደሪያውን መርህ እና ሕግ በምን ሁኔታ ያከብራሉ፣ ተከታዮቻቸውን በዛ መስመር እንዴት ያስኬዳሉ፣ የፀጥታም ሁኔታ በጣም ወሳኝና ሌላ አስፈላጊ ነገር ነው። ከቦርዱ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ አስፈላጊ ነገሮች እንዳሉ ነው የማስበው።

የአካባቢና የከተማ አስተዳደሮች ምርጫ መቼ ይካሔዳል? አንዳንድ ወገኖች በተለይ ከአገራዊ ምርጫ በፊት የሚካሔድ ከሆነ የቦርዱን ገለልተኛነት የማረጋገጥ ዕድል ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ይደመጣሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
የአካባቢና የከተማ አስተዳደሮች ምርጫ የሚባለው ከአጠቃላይ ምርጫው በተለየ ሁኔታ የተለየ ዓይነት ውሳኔዎች ለመስጠት ልዩ ሁኔታዎች አሉት። የአካባቢ ምርጫ አሠራር፣ አወቃቀር፣ ምርጫው የሚወስደው ጊዜ፣ አንድ ወረዳ ስንት የምክር ቤት አባላት ይኖሩታል፣ ዞን የሚባል አደረጃጀት በሌላቸው ክልሎች ደግሞ የማስተባበር እንጂ ውሳኔ የመስጠትና ምክር ቤት የማደራጀት ሁኔታ ላይሆን ይችላል።

ስለዚህ እያንዳንዱ ክልል፣ የአደረጃጀቱ ሁኔታ እና ምርጫውን የሚያካሒድበት አግባብ በተወሰነ መልኩ የመወሰን ሥልጣን አለው። ምርጫው የሚካሔድበትን ጊዜ ከመወሰን በፊት ሕጉ ላይ በቦርዱ ላይ የክልል ባለሥልጣናትን ማማከር ሥልጣን ይጥልበታል። ስለዚህ ምን ዓይነት ዝግጁነት እንዳላቸው የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሌላው አማራጭ የተለያዩ ክልሎችን የአካባቢ ምርጫ በተለያየ ጊዜ ማድረግ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት በሶማሌ ክልል አንደተካሄዱት ምርጫዎች ማለት ነው። ስለዚህ ከክልል መንግሥታት ጋር ብዙ መነጋገር ይጠብቀናል። ሁሉም ምርጫ በአንድ ላይ እናድርገው ቢባል ተቋማዊ አቅም ላይ ጫና ያሳድራል። መቶ በመቶ አይቻልም ባይባልም አሁን ባየሁት ሁኔታ የሚቻል ግን አይመስለኝም።

እኛ ከመምጣታችን በፊት የተወሰነ ዝግጅት አድርገው ስለነበር የንብረት ብክነት እንዳይኖር እንዴት መጠቀም እንዳለብን መወሰን ይገባናል።
ምርጫውን በተመለከተ ቦርዱ ስትራቴጂ ዕቅድ ሲወጣ አንዱ የሚያወጣው የአካባቢ ምርጫ በምን ዓይነት ሁኔታና ጊዜ ቢካሄድ ይሻላል የሚለውን ይወስናል።

ተቋሙ የሚያካሒደው ማሻሻያ ከአካባቢና ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ ጋር ይያያዛል?
የተቋሙ ማሻሻያ ሁሉንም ነገሮች ይነካል ብዬ አምናለሁ። ይሁንና የአካባቢና ከተማ አስተዳደር ምርጫን በተለይ ማዕከል የሚያደርግ ማሻሻያ እስካሁን አላየሁኝም፤ ሊኖር ግን ይችላል።

ምርጫውን መቼ ለማካሔድ አቀዳችሁ?
እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቦርዱ መሟላት አለበት። በተጨማሪም ተቋሙ ሳይሻሻል፥ ከዚህ ቀደም ይደረግ በነበረበት ሁኔታ ምርጫ ብናደረግ ትርጉም የለሽ ሥራ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም እስካሁን በነበረው የቦርዱ አሠራሮቹ፣ አደረጃጀቱ፣ አቅሙ ትክክለኛ ምርጫ ለማካሔድ አይመችም የሚል መንግሥትን ጨምሮ በሁሉም አካላት ስምምነት አለ። ስለዚህ የማሻሻያ ሥራው ሁሉንም ነገር ይመለከታል።

በርግጥ ማሻሻሉ እና ምርጫ ዝግጅቱ አብረን ልናካሒድ የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ለዚህም ቢሆን ግን መሻሻሉ የሆነ ደረጃ መድረስ አለበት። ዕቅዳችንን ከዘረጋን በኋላ የትኛውንም ነገር በየትኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ማጠናቀቅ ወይም መሥራት እንችላለን የሚለውን ውሳኔ የምናሳልፍበት ማለት ነው። ይሁንና ተቋሙ ሙሉ ብቃትና ተዓማኒነት እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀት አለበት።

የምርጫ ቦርድ መስፈርትን ያሟሉና የተመዘገቡ ስንት አገር ዐቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች አሉ?
እስካሁን በነበረው ሕግ መሠረት በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ የአካባቢ ፓርቲዎች የሚባሉት 60 አካባቢ ሲሆኑ ኻያዎቹ ደግሞ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተደራጅተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው ገና በሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው። ለቦርዱ ጥያቄ ያላቀረቡም ፓርቲዎች አሉ። የምዝገባ ሒደት ላይ ያሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ ዘጠና የሚጠጉ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በቦርዳችሁ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥም የተመዘገበ ፓርቲ አለ?
ኦነግ በቦርዱ አልተመዘገበም። ስለዚህ ጉዳይ ዘርዘር አድርጌ ልንገርህ።

እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ የሚነሳበት ኦነግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፓርቲዎችም አሉ። በሽግግር ወቅት [1983-1987] የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ ጥናት አካሂደናል።

የሽግግር መንግሥት ሲመሰረት የፓርቲ ምዝገባ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ይሁንና የሽግግር መንግሥቱን ያቋቋሙት ፓርቲዎች ነበሩ። የፓርቲዎቻቸውን አደረጃጀት ወስነው ይንቀሳቀሱ ነበር፤ የአካባቢ ምርጫም ያካሄዱት የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ነበር።

ከዛ በኋላ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ ከተቋቋመ በኋላ ፓርቲዎችንም ይመዘግባል ስለተባለ በ1986 ሁሉም ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ መመዝገብ አለባቸው የሚል የሕግ ድንጋጌ በመኖሩ፤ ቀደም ብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ፓርቲዎች እንደ ኢሕአዴግ፣ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) የመሳሰሉት ተመዝግበዋል። ኦነግ ግን ምዝገባው በሚካሔድበት ወቅት በአገር ውስጥ አልነበረም።

በአጭሩ ምርጫ ቦርድ ውስጥ ኦነግ በሚል ሥም የተመዘገበ ፓርቲ ኖሮ አያውቅም።

በቅርቡ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመዝግቧል?
[አብን] ጉባዔያቸውን አድርገው፣ ሰነዶቹንም አሟልተው ለቦርዱ አቅርበዋል፤ የቦርዱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በእኛ በኩል ሁሉንም አስፈላጊ ነገሮች ማሟላታቸውን አረጋግጠናል፤ ውሳኔ ያልተሰጠው ቦርዱ ባለመሟላቱ ነው።

ከዚህ ጋር አያይዤ የምናገረው የፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ የማሻሻያ አካል ስለሆነ እየታየ ይገኛል። እያንዳንዱ ፓርቲ መመዝገብ አለበት በማለት ወደማስፈጸም የማንገባበትም ምክንያት ማሻሻያው ሲጸድቅ ምናልባት አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ካሉትም ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የሚወጡ ሊኖሩ ይችላሉ።
በአጠቃላይ የመደራጀት መብትን በደንብ ለመተግበር የሚያስችል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ አማራጭ የፖለቲካ አመለካከት የማግኘት መብት አለው። እነዚህን የሚያካትቱ አሠራሮች ምን መምሰል አለባቸው ብሎ ፓርቲዎቹ እንደሳንካ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ስላሉ እነዚህን ሁሉ በሚገባ ታይተው ሕጉ እንደገና ይጸድቃል ማለት ነው። ስለዚህ እንደገና ሁለት ሦስት ጊዜ ምዝገባ ከማካሔድ ማሻሻያው ከፀደቀ በኋላ ሁሉንም ነገር አጠቃለን ማድረግ እንመርጣለን።

ሕጉ ሲጸድቅ ሁሉም ፓርቲዎች እንደ አዲስ ይመዘገባሉ ማለት ነው?
በሕጉ መሠረት የአመዘጋገብ ስርዓቱ ለውጥ ይኖረዋል። በለውጡ መሠረት ቀደም ሲል የተመዘገቡት በተጨማሪ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሊኖር ይችላል። ስለዚህ እንዲያሟሉ ይደረጋል። አዳዲሶቹ [ፓርቲዎች] ግን በሚሻሻለው ሕግ መሠረት ይመዘገባሉ። ሁሉንም ፓርቲዎች ግን በአዲሱ አመዘጋገብ መሠረት እንደገና ይታያሉ።

በፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ አይደለም የሚለው ትችት ይሰማል። ይህ በመሆኑም አንዳንድ ፓርቲዎች ሕግንና ስርዓትን ተከትለው እየሠሩ አይደለም ይባላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ቀደም ብዬ እንዳልኩት ሕጉ ከወጣ በኋላ ሁሉንም ፓርቲዎች በአዲሱ አሠራር መሠረት እንፈትሻቸዋለን። እኛም የምናውቃቸው ነገሮች አሉ። ለረጅም ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሔዱ፣ አድራሻቸው የማይታወቅ፣ ሒሳብ አያያዛቸው የማይታወቅ ብዙ ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህ ፓርቲዎችን በአዲሱ አዋጅ መሠረት በደንብ ፈትሸን የሚያሟሉትን እንዲመዘገቡ አሊያም እንዲሰረዙ እናደርጋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግድ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው የሚደነግግ ሕግ መኖሩ ይታወቃል። በተለይ ኢሕአዴግ ‹ኤንዶውመንት› በሚል ያደራጃቸው የንግድ ድርጅቶች እንዳሉ በሠፊው ይነገራል። በዚህ ረገድ ቦርዱ ምን እያደረገ ይገኛል?
በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ለመስጠት መልሼ ስለማሻሻያው ሕግ ላወራህ ነው ማለት ነው። ከሕግ ማሻሻያዎቹ አንዱ ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ፣ ምርጫ በሚደርስበት ጊዜ የሚደረግ የገንዘብ አጠቃቀም፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴን በተመለከተ የገንዘብ አጠቃቀም በተመለከተ ሕጉ ምን መሆን ይገባዋል የሚለው ይታያል።

ከሌሎች በዴሞክራሲ ከዳበሩ አገሮች ልምዶች የምናየው የገንዘብ ምንጭን ማሳወቅ ወይም መገደብ የታወቀ አሠራር ነው። ሕንድ በዚህ ረገድ ጥሩ ተመክሮ ያላት አገር ነች። ፓርቲዎችን የገንዘብ ምንጭ ማሳወቅና መገደብ ጉዳዮችን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመቀናጀት ይሠራል፤ ከሕዝብ የሚደርሱትን ጥቆማዎችም በደንብ ይጠቀምበታል።

ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመከታተያ አሠራሩ ምን መምሰል አለበት፣ የመከታተያ አቅሙስ እንዴት መፈጠር አለበት የሚለውን እንደ ቦርድ ማየት አለብን። የሁሉንም ፓርቲዎችን የገንዘብ ምንጭና አጠቃቀም የምንከታተልበት አቅም ከሌለን በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ሕግ ብቻ ሆኖ ይቀራል።

የምርጫ ቦርድ ሥራ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ቢሮውን ከመያዞት በፊት የነበሮት ግምትና ቢሮውን ተረክበው በተግባር ያገኙትን በንጽጽር ምን ይመስላል?
የዚህ ቤት [ምርጫ ቦርድ] የረጅም ጊዜ ደንበኛ ነኝ። በተለያየ መልኩ አንዱ ምርጫ አልፎ ሌላው ሲመጣ እንደተወዳዳሪ፣ የፓርቲ ጠበቃ፣ ከምርጫ መዛባት ጋር በተያያዘ፣ እንደ ፓርቲ መሪ ወዘተ. ስለዚህ ችግሮቹን በደንብ አውቃቸዋለሁ።

በርግጥ አሁን ቦርዱ ውስጥ ገብቼ ሳየው እንደጥበቃዬ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ከግምቴ በጣም የራቀ፣ አስደነገጠኝ የምለው ነገር የለም። [ችግሮቹም] አዲስ ሆኖብኛል ለማለት አልችልም ምክንያቱም የተለመድኳቸውም የማውቃቸውም ስለሆኑ ማለቴ ነው።

አሁን አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናዮች አሉ፤ የመገናኛ ብዙኃን በጣም ሊያግዙ ይችላሉ። ለውጡን የሚመጥን ሥራ ካልሠራን አስቸጋሪ እንደሚሆን በደንብ እረዳለሁ። ሥራው እንዳልከው ከባድ ነው፤ ከገመትኩት በላይ ግን ከባድ ነው ብዬ እስካሁን አንገቴን አልደፋሁም።

ስለዚህ በብቃት እወጣዋለሁ ብለው ያምናሉ?
እንደሱ ለማድረግ እምነት ባይኖረኝ እዚህ ለምን እቀመጣለው? እንደአገርም እንደግለሰብም ዕድሉ በጣም ዋጋ የሚሰጠው ነው ብዬ አምናለሁ። ያን ዕድል በጣም ወደ ተሻለ ውጤት ለማምጣት የምችለውን በሙሉ አደርጋለሁ። ‘ይሆናል አይሆንም’ ብዬ ብዙም አላመነታም፤ እንዲሆን መሥራት ነው ያለብኝ። አዕምሮዬ ውስጥም ያለው ይሔው ነው።

በተለይ ውጪ አገር ቆይቶ ለመጣ ሰው ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ፍጥነት እና ነገሮች ቀልጠፍጠፍ ብለው እንዲሠሩ ትፈልጋለህ፤ የቴክኖሌጂውም፣ የሰው ኃይል አቅሙም በምትፈልገው መንገድ አይሔድልህም። የፈለገ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብሆን እንኳን ነገ ጠዋት ተነስቼ እንደ አዲስ ቀን እቀጥላለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here