የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምክር ቤት ውሎ “ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሠርቶ ያልታሰረ የለም”

0
354

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርብ፣ ጥር 24 በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በንግግራቸው ለመዳሰስ የሞከሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያ አካላትም ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዴሞክራሲ፣ ፖለቲካና ሰብኣዊ መብት
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ወደ አገር ውስጥ ከገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማያያዝ ምላሻቸዉን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ መንግሥት ዲሞክራሲን ለመገንባት ዋነኛው ምሰሶ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም ምክንያት መንግሥት ብዙ ሆደ ሰፊነት አሳይቷልል፣ ከኃይልም መለስ ብሎ ማስተናገድ ስለሚገባው መንግሥት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ትዕግስት አሳይቷል ብለዋል። ይሁንና የአገር አንድነትንና ሰላምን በሚያደናቅፉ ላይ ግን መንግሥት የታገሰውን ያህል የመረረ እርምጃ ለመውሰድ እንደማያንገራግር በንግግራቸው አክለዋል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 20 የሚጠጉ የታጠቁም ያልታጠቁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ገልፀው ‹‹አሁን ላይ ውጭ አገር ሆኖ የሚቃወመን የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ሚዲያ የለም በአገር ውስጥም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም›› ብለዋል። የፖለቲካ ምኅዳሩን መስፋት ያልተመቻቸው እና ጉራማይሌ አካሄድ የሚከተሉትን መንግሥት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንደሚመክርና በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱት ደግሞ ጊዜው አጭር ስለሆነ ፍጠኑ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚሰሩ እንዳሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን መጠቀሚያ በማድረግ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሚተጉ አሉ። “የአገር ሰላም እና አንድነት እንዲረጋገጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማኅበረሰብ ምን ይጠበቃል?” ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ “እንዲህ ዓይነት ችግር በዩኒቨርስቲዎች እንደሚከሰት እናውቅ ነበር” ሲሉ የጀመሩት ዐቢይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከተማሪዎች መግቢያ ጊዜ አስቀድሞ ተወያይተናል፤ ነገር ግን አሁን ላይ የፀረ ሰላም ዓላማን የሚሸከም ተማሪ አልታጣም ይላሉ ። የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተማሪዎችን መጠቀሚያ ማድረግ በየትኛውም ዓለም የሌለ መሆኑን ከንግግራቸው መረዳት የተቻለ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከዚህ ነገር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

በሐሳብ ልዕልና መንግስትን መሞገት ስልጣኔ መሆኑን ለተማሪዎች ምክር አዘል መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋለልኝ መኮንንን ለአብነት አንስተዋል። ዋለልኝ መኮንን መንግስትን በእውቀቱ ብቻ ሲሞግት እና ለሐሳቡ መደመጥ ሲታገል እንደነበር ተናግረው፣ አሁን ላይ ግን አንዱ ተማሪ የሌላውን ነብስ እየቀጠፈ የሚደረግ የፖለቲካ አካሄድ ላይ ትችትን ሰንዝረዋል ።

በተደራጀ መንገድ ዝርፊያ በመፈፀም ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙ ግለሰቦች ዙሪያ ብሔር ተኮር ጥቃት ነው እየተባለ ስለሚነሳው ቅሬታ እና በሰብኣዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው መንግሥት የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸው እስካሁን ባለተያዙትና የክልሉ መንግሥት አሳልፎ በመስጠት ሒደት ላይ ስለታዩት ክፍተቶች ተጠይቀዋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ያልታሰረ የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም እንደማብራሪያ ሲያስቀምጡ መንግሥት በሕግ ጥላ ሥር አድርጎ እየቀለበ፣ ጤናቸውን እየተከታተለ የሚያኖራቸው እንዳሉ ሁሉ በሕግ ቁጥጥር ሥር ሳይውሉ ከሕግ ሽሽት ተደብቀው ራሳቸውን የራሳቸው እስር ቤት ውስጥ ያሰሩ አሉ ሲሉ ምላሽ ሰጥተውበታል። አያይዘው ወንጀል ሰርተው በግልፅ እየተንቀሳቀሱ ክልሉ አስሮ የማቅረብ ግዴታ አለበት ብለዋል። የብሔር ተኮር ነው የተባለው ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሒደቱ ላይ ሲመልሱ ደግሞ “ሌባ የሚባል ብሔር የለም፤ በሁሉም ብሔር ውስጥ ሌቦች አሉ” በማለት የማንንም ብሔር ለማጥቃት የተወሰደ እርምጃ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ምጣኔ ሀብት
አገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ያለችበትን የምጣኔ ሀብት ደረጃ እና ንግድ እንቅስቃሴ በተመለከተ ምላሻቸውን ሲሰጡ በባለፈው ዓመት በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ከፍተኛ የጥቅል ምጣኔ ሀብት (‘ማክሮ ኢኮኖሚ’) ላይ መዛባት የታየቱን ያስገነዘቡ ሲሆን አሁንም ቀጥሎ እንደሚገኝ ከምላሻቸው ለመረዳት ተችሏል። አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባ አስረግጠው ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለመግታት የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሆነና በዚህም መሰረት የመንግሥት ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ሰፋፊ የመንግሥት ፕሮጄክቶችን በማስቆም ሥራዎችን ሰርቷል። በተሰራውም ሥራ ላለፉት 15 ዓመታት 14 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት ወደ 10 ነጥብ 3 እንዲቀንስ ማስቻሉ ታውቋል። ይሁን እንጂ ሰፋፊ የመንግሥት ፕሮጄክቶች እንዲቆሙ ቢደረግም ታላቁ የሕዳሴው ግድብ ላይ ግን መንግሥት ከመቼውም በላይ በትጋት እየሠራ እንደሆነና ግድቡ በመጓተቱ ምክንያት 60 በመቶ የግብዓት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳጋጠመውም ተገልፆ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለማጠናቀቅ ዕቅድ እንደተያዘለት ተገልጿል።

በሌላም በኩል ከዓለም ዐቀፍ ለጋሾች ድጋፍ እየተገኘ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት ከዓለም ባንክ ለበጀት ድጋፍ የሚሆን 1 ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ዶላር በመጀመሪያ ጊዜ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ቀጥሎም ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ መገኘቱንና በድምሩ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ መደረጉን ገለፀዋል። ይህም የዓለም ባንክ ከ16 ዓመታት ወዲህ ለበጀት የሚሆን ድጋፍ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለምጣኔ ሀብቱ መቀዛቀዝ የሥራ አጥ ቁጥር በየጊዜው መጨመርን እንደ አንድ ምክንያት ያስቀመጡ ሲሆን በየዓመቱ ወደ ኹለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሥራ ፈላጊ ገበያ ላይ እንደሚወጣ እና ግማሽ ለሚሆነው ብቻ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አስታዋል። ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ እንዲሆን ታስቦ ሥራ ላይ የዋለው 10 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለክልሎች ቢከፋፈልም እስካሁን መሰብሰብ የተቻለው 1 በመቶ ብቻ መሆኑን ታወቋል።

በገቢ እና በወጪ ንግድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ አሁንም አገሪቱ ከፍተኛ የንግድ ጉድለት ላይ እንዳለች የተገለፀ ሲሆን የገቢ ንግዱ ከወጪ ንግዱ በትንሹ በ500 በመቶ ብልጫ እንዳለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገልጿል። ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ዕቃ እዚህ መመረት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ የሚታወቅ ቢሆንም በተለይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር ገና ረጅም ጊዜ እንደሚፈልግ ዐቢይ ንግግር ውስጥ ጠቅሰዋል።

የገቢ እና ወጪ ንግዱን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወን የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀም መግባባት ላይ የተደረሰ እንደሆነ እና የዓለም ባንክም ድጋፍ እንደሚያደርግ ይሁንታውን መስጠቱን ተገልጿል።

መገናኛ ብዙኃንን
በመጨረሻም ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ ከማቅረብ ይልቅ ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣ ብዝሃነትን የማያከብሩ፣ አንድነትን የሚንዱ የሕዝብም ሆነ የግል ሚዲያዎች እንዳሉ ከምክር ቤቱ ተጠቅሷል። በዚህም መሠረት መንግሥት ሕጋዊ መሠረትን የሚከተልና ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ለመፍጠር በመንግሥት በኩል ምን እየተሠራ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም መልስ ሲሰጡ “የትኛውም ሚዲያ ለሚያስተላልፈው የትኛውም መረጃ ምንጩን መጥቀስ ይኖርበታል” ያሉ ሲሆን አያይዘውም ከዚህ በፊት እንደነበረው የሀሰት ዘገባ እየዘገቡ ሕዝብን ማወናበድ እንደማይቀጥልና ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልፀው ምንጭ በሚጠቀስበት ጊዜም ተጠያቂነቱ ወደ ምንጩ እንደሚዞር ከንግግራቸው ለመረዳት ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here