የአፋር እና ኢሳ ጎሳዎች ግጭትና መዘዙ

0
960

በቅርቡ የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የነዳጅና ሸቀጦች እጥረት እንዲከሰት እና የአለመረጋጋት ድባብ እንዲሰፍን ማድረጉ ይታወሳል። ሙሉጌታ ገዛኸኝ ከዚህም የባሰ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ያሉትን የአፋር እና ኢሳ ጎሳዎች ግጭት መንሥኤ እና ውጤት በአጭሩ ያስነብቡናል።

 

 

በኢትዮጵያ ሰሜን ምሥራቅ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የአፋር ምድር አሰፋፈርና ሥርጭት የድንበርና አጎራባች አካባቢዎች ሁኔታ በተሻሻለው የክልሉ መተዳደሪያ ሕግ ቁጥር 14/1994 መሠረት የተካለለ ሰፊ ወሰን እንዳለው ይገልጻል። በተለይም ከኤርትራና ጅቡቲ የባሕር በር መዋሰን ብቻ ሳይሆን የእርስ በርስ ጎሳዎች ቁርኝት አንድም በመልካም፣ አንድም በግጭት የታጀበ መሆኑ በታሪክ መረጃ ይጠቀሳል። ጥንት የአፋር (አዳል) ሡልጣኔት የባሕር ወደብ የነበረችው ኦቦክ ከጅቡቲ ሰባ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት በሰሜን ታጁራ ወደ ኤደን ባሕር ወሽመጥ መግቢያ ነበረች። የታጁራ ወደብ እስከ አሁን ድረስ አፋሮች በአብዛኛው የሚኖሩባት የጅቡቲ አካል የንግድ በር ሆና ታገለግላለች።

በዚሁ በታጁራ ውስጥ ሙሳ ዓሊ የተሰኘው ተራራ በከፍታው ይታወቃል። የአፋር ግዛት በአራቱ የሡልጣኔቶች ማለትም የአውሳ፣ የቢዱ፣ የራሃይታ እና የታጁራ ኢሚራዊ አስተዳደር እንደነበረው ተሾመ ብርሃኑ ከማል ካሳተመው መጽሐፍ መገንዘብ ይቻላል። አፋር ከራሱ ድንበር ባሻገር የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲያስከብር መኖሩን ብዙዎች ይሥማሙበታል።

የሳሆ ሕዝቦች ዝምድና ያላቸው አፋሮች የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆኑት ሱማሌ ጎሳዎች – ኢሳዎች ጋር ጥንትም ሆነ ዛሬ ማኅበራዊ ትሥሥር የጠበቀ ቢሆንም በአመዛኙ ግጭትና ጠብ ያልተለየው ተቃርኖ ይንፀባረቅበታል። ፈረንሳያዊው የሥነ ልሳን ተመራማሪ ሊዮ ሬኒስ እንደሚያስረዱት አፋርና ሳሆ በቋንቋ ዝምድናቸው አንድ መሆናቸውን ነው። በሌላ በኩል ሪቻርድ ፓንክረስት “ዘ ፖለቲካል ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ” እና ትርሚንግሐም “ኢዝላም ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ” በተሰኙ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸው የጥንቷ ዘይላ የአፋሮች እና ሱማሌ ጎሳዎች የሚኖሩባት የሥልጣኔ ማዕከል እንደነበረች ያብራራሉ። ዘይላ ከጅቡቲ፣ ሐረር፣ አውሳ፣ ሸዋ እና ሌሎችም ቅርበት ያላት የኢትዮጵያ ሲራራ ንግድ መሥመር መዳረሻ ነበረች። ከማዕከላዊ መንግሥት እንዲሁም ከአጎራባች የሱማሌ ጎሳዎች እና ራያዎች መካከል የእርስ በርስ ግጭት የቆየ ታሪካዊ አንድምታው ምን እንደሚመስል በርካታ መዛግብት ሲዘግቡት ኖረዋል።

የአፋር እና ኢሳ ግጭት
በአፋሮች እና ኢሳ ጎሳዎች ግጭት መቀስቀስ ለረጅም ዘመናት የኖረ ቢሆንም አሁን እንደ አዲስ እያገረሸ ችግሩ በአካባቢው ላለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ በፖለቲካ ተንታኝ ባለሙያዎች በየጊዜው ይዳሰሳል። አስናቀ ፈለቀ “ፌደራሊዝም ኤንድ ኢትኒክ ኮንፍሊክት ኢን ኢትዮጵያ፡ ኤ ኮምፕርሄንሲቭ ሪጅናል ስቴዲ” በሚል ጥናታቸው፥ ከዚሁ የአፋርና ኢሳ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የግጭት መስተጋብር ጋር በተያያዘ ጥናት ያቀረቡበት ጽሑፍ ይህንን ሐሳብ ያጠናክራል። በመሆኑም የግጭቱ መንሥኤዎች በሌሎች ግዛቶች ከሚገኘው የተለየ ነው ለማለት ባይቻልም፥ ሁለት መሠረታዊ ምክንቶች እንዳሉት ይጠቀሳል። ከአጎራባች ጎሳዎች የአኗኗር ዘይቤና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚነሳው ግጭት፣ እርስ በርሳቸው ካላቸው አካባቢያዊ ቁርቁስ ከሚነሳው ግጭት በዓይነቱ ለየት ያለ ነው። የግጭቱ መንሥኤና መግፍኤ ትኩረት ዘመናትን ተሻግሮ እስከቅርብ ጊዜ በአፋርና አጎራባች ኢሳ ጎሳዎች ጥቃት መሰነዛዘሩ፣ የፌደራሉ መንግሥት በፌደሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት አብጠርጥሮ የፈተሸው አይመስልም።

በአርብቶ አደርነት ሕይወታቸው የተመሠረተው አፋሮችና የሱማሌ ኢሳዎች ከጥንቱ ግጦሽ መሬት እርስበርስ ቁርሾ ሊላቀቁ ያልቻሉበት ዐቢይ ምክንያት በቀይ ባሕር አካባቢ ባለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ጠቀሜታ ላይ የተመሠረተ ውስጣዊ የተፈጥሮ ሀብትና የግጦሽ ሥፍራ ቁሳዊ ግጭት በሰበብ አስባቡ ጎሳዎችን መጠቀሚያ የማድረግ አዝማሚያ እንደሚኖር ጆን ማርካኪስ “አናቶሚ ኦፍ ኤ ኮንፍሊክት፡ አፋር እና ኢሳ” በተሰኘው መጽሐፍ ትንተናቸው ያወሳሉ።
በአርብቶ አደርነት የኢኮኖሚ መሠረቱን የጣለው አፋሮች እና ኢሳዎች በማዕከላዊነት ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ መዋቅር ይልቅ ቤተሰባዊ (ጎሳዊ) የዘር ግንድ መነሻ የሚያደርግ ባሕላዊ የዳኝነትና ዕርቅ ስርዓት አላቸው። የግጭት አፈታቱም በሽማግሌ ወይም የጎሳው አባት አማካኝነት የሚወሰንበትን ዘይቤ ይከተላሉ ሲሉ ዶክተር ጌታቸው ካሳ “አፋር ፓስቶራሊዝም ኤንድ ሶሳይቲ” በተሰኘው ሥራቸው ያብራራሉ።

በቀጠናው የተሟላ ትጥቅ ያነገቡት ኢሳዎች ከጎረቤቶቻቸው አፋሮች ጋር የሚያጋጫቸው የተስፋፊ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ኹለቱን በመጠቀም የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ ከሚመነጭ ሥውር ምክንያትም እንደሚመነጭ ዶክተር ክንፈ አብርሃም በጻፉት መጽሐፍ ጠቅሰዋል። ከተለመደው የአርብቶ አደር የግጦሽ ሥፍራ ቁርቁስ ከፍ ባለ ሁኔታ፣ በተለይም በሱማሌ ኢሳ ጎሳዎች የበላይነት ራሷን የቻለች የጅቡቲ ግዛት እንድትመሠረትና ቀጠናውን የመቆጣጠር ፍላጎት በሚመነጭ በአካባቢው ተገዳዳሪ አፋሮችን የማዳከም አካሔድ ለመከተል ተሞክሯል።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በሚያገናኘው ዋና መሥመር ላይ የምትገኘው አይሻ በኢሳዎች ይዞታ የምትገኝ በመሆኗ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማስተሳሰሪያነት አልፎ የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጠቀሜታ ለማዋል በርካታ ጊዜ ኢሳዎች መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ ያካሒዱባት ነበር። ከ1983 ወዲህ የኢሳና ጉርጎራ ነጻ አውጭ ግንባር የተመሠረተው ከአካባቢያዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ ድሬዳዋን ጨምሮ የይገባኛል ጥያቄ የሚያራምድበት ትግል ይታወሳል። በሌላ መልኩ “የታላቋ ሱማሌ ሪፐብሊክ” ምሥረታ እንቅስቃሴ ሕልም ጋር በተያያዘ ኢሳዎች ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን በማጠንከር የአፋር ሰፋፊ አካባቢዎች የዚሁ አካል ተደርገው እንዲቆጠሩ ሙከራዎች የተደረገበትን ሒደት ጸሐፍት ያስረዳሉ።

ጸሐፍቱ ከዚህም ባሻገር በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ወይም ኡጉጉሞ ሕወሓት በተዋናይነት እጁ እንዳለበት ጥርጣሬያቸውን ሲያስቀምጡ፥ የሶማሌው ልዩ ኃይል ኢሳዎችን እየረዳ በጋለ ምጣድ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈ ይገኛል ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። ወደፊትም መቋጫ ሊገኝለት ይችላል ተብሎ የማይታሰበው የአፋርና ኢሳ ጎሣዎች ግጭትና ፍጥጫ ለአካባቢው ቀጠና ብቻም ሳይሆን ዳፋው ለመላው የአገሪቱ አጠቃላይ መረጋጋት ተግዳሮት እንደሚሆን ምልክቶች ይታያሉ። ለአብነት ከሰሞኑ ተዘግቶ የነበረው የጅቡቲ መሥመር የነዳጅና ሸቀጦች እጥረት እንዲከሰት የሚያደርግ መስተጓጓል ፈጥሮ ነበር፤ ይህም አሳሳቢ ሥጋት ሆኖ መሰንበቱ አይዘነጋም።

ሙሉጌታ ገዛኸኝ የታሪክና ቅርስ ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gezahegn.mulu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here