የትግራይ መንግሥት ምላሽ ሕጋዊ አንድምታ

0
774

የማንነት እና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋም ዛሬም በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል አንዱ ላለመሥማማት መንሥኤ እንደሆነ ነው። ቀድሞውኑም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል ተወካዮች ሙሉ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረውና በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ቀርቦበታል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጉባዔውን ያጠቃለለው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ኮሚሽኑ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ስለመሆኑ ገልጾ እንደማይቀበለው የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ አፅድቋል፤ መግለጫም አውጥቷል።

ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ እንደ አዲስ መከራከሪያነቱን ቀጥሏል። የአለመሥማማቱ መነሻ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ነው፣ አይደለም የሚል ነው።
“የሕገ መንግሥታዊነት” ጥያቄ ስለአከላለል ለውጦች የሚያትተው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 (1) “የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ሥምምነት ይፈፀማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መሥማማት ካልቻሉ የፌደሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል” ይላል። በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረበ ጥያቄ ኹለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበትም በንዑስ አንቀፅ 2 ተጽፏል።

በአንቀጽ 62 ላይም የፌደሬሽን ምክር ቤት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ጥያቄዎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚወስን፣ በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔን እንደሚፈልግ እንዲሁም የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች እንደሚያቋቋም ተዘርዝሯል።
ይህን መነሻ የሚደርጉት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ መኮንን ፍስሐ የተቋቋመው የማንነት እና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ይላሉ። ኮሚሽኑ የክልሎችንና የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣን ወስዷል የሚሉት መምህሩ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ውጭ የሆነ የትኛውም ተቋምና አካል ለአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጥያቄዎች መፍትሔ በሚል ተቋም ማቋቋም አይችልም ባይ ናቸው። ምክንያቸውም መሰል ጥያቄዎችን መፍትሔ የመቸር ብቸኛ ሥልጣን የክልል መንግሥታትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ነው የሚል ነው።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 6/2011 ላይ ደግሞ “በሕገ መንግሥቱ እና በሌሎች ሕጎች ለፌደሬሽን ምክር ቤት እና ለክልሎች የተሰጠ ሥልጣን እና ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ” ሲል ያትታል። አክሎም ኮሚሽኑ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ለመወጣት ሲል እንዳቋቋመው፣ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ፣ ሰላምን ለማስፈን እና ተልዕኮውን በብቃት ለመፈፀም የሚያግዝ ኮሚሽን ስለመሆኑ ይጠቅስና “ኮሚሽኑ በማንነትና በአስተዳደር ወሰን ጉዳይ በራሱ የመወሰን ሥልጣን ያልተሰጠው መሆኑ” ሲል ይገልጻል። ይልቁንም “ኮሚሽኑ በጥናት ግኝት የለያቸው ከራስን በራስ የማስተዳደር፣ የአስተዳደር ወሰን እና ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ ከሆነ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል” ሲል በግልጽ ጽፏል። ምክንያቱ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ የመስጠቱ ሥልጣን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ስለተሰጠ እንደሆነ አብራቷል። የአስተዳደርና ማንነት ጥያቄዎች እየበዙና የግጭትም መነሻ እየሆኑ ስለመጡ ኮሚሽኑን መቋቋም እንዳስፈለገ ተጠቅሷል።

ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ደግሞ ጥናት የሚያጠና ኮሚሽን ስለሆነ ሕገ መንግሥቱን ጥሷል አይባልም፤ በእውነተኛ ጥናት ላይ ተመሥርቶ እስከተሠራ ድረስ የሚቀርበው ምክረ ሐሳብ ቅቡል የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም ይላሉ። ኮሚሽኑ የተቋቋመው እስከዛሬ ያልተሠራውን ተግባር ለመከወን ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያዎች የእያንዳንዱ ብሔር ማንነትና ፍላጎቱ እንደሚረጋገጥለት በሕገ መንግሥቱም ቢሆን መብት ተሰጥቶታል ሲሉ ይሞግታሉ።

የሕግ ባለሙው ዘፋኒያ ዓለሙ ቀድሞውኑ የፌደሬሽን ምክር ቤት አንቀጽ 39 ላይ በሰፈረው የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ጉዳይ ውሳኔ ያሳፋል ስለሚል ማንነትም በዚህ ውስጥ ይካተታል በሚል የተለጠጠ ትርጉም ሊኬድ ካልቻለ በስተቀር ሕገ መንግሥቱ በቀጥታ የማንነት ጥያቄ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤቱ መብት አልሰጠውም ባይ ናቸው። አክለውም ማንነት ተፈጥሯዊ ስለሆነ ማንም እከሌ ነህ ብሎ ሊወስን እንደማይችል ይልቁንም ተፈጥሯዊ ለሆነው ነገር ዕውቅና ሊሰጥ ብቻ እንደሚችል ያስገነዝባሉ።

“የመጀመሪያው ስህተት 9ኙ ክልሎች በሕገ መንግሥት አልተከለሉም፣ ሕገ መንግሥቱም መሬት ላይ አልወረደም” የሚሉት ዘፋኒያ አሁን ያለው አከላለል የሕዝብ ውክልና በሌለውና ጊዜያዊ በሆነው የ1984 የሽግግር ወቅት የተከለለ መሆኑንም ያነሳሉ። ሕገ መንግሥቱ በሚለው መንገድ እስካሁን የተከለለ አንድም ክልል የለም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚ ያልሆነን ሕገ መንግሥት እንደተፈፀመ ቆጥሮ መንቀሳቀሱም በራሱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊነት ነው ብለው ያምናሉ።

የኮሚሽኑ መቋቋም ከአንዱም የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ ጋር እንደማይጋጭ በመግለጽም፣ እንዲያውም ከ24 ዓመት በፊት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባት ይገባው የነበረና የፌደሬሽን ምክር ቤትም እንዲቋቋምለት መጠየቅ ሲገባው እስከዛሬ ያላደረገው እርምጃ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የማንነት ጥያቄ ከሚያነሱ አካባቢዎች አንዱ ራያ ነው። የራያ ማንነት ጥያቄ አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢው አግዘው ሕዳሩ ቀድሞውኑ ሕገ መንግሥቱ ሳይፀድቅ በ1984 ለተደረገ አከላል አሁን ሕገ መንግሥቱን እያነሱ መከራከር አይቻልም የሚል አቋም አላቸው። የማንነትና ወሰን ጉዳዮች ጥያቄ በራያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች እየተነሳ ያለና ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኖ የመጣ በመሆኑ ከልማትና አንድነት በፊት እነዚህ ጥያቄዎቸ መላ ይፈልጋሉ ባይ ናቸው።

ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚለው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት አቋም የማይሥማሙት አግዘው ሕገ መንግሥቱም ቢሆን በታሪክ፣ በሥነ ልቡና፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በኅብረተሰቡ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የሚከወን አከላለልን መከተል እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳል ሲሉ ያክላሉ። አሁን ላይ ክልሉ ኮሚሽኑን የሚቃወመው እውነተኛ ጥናት ከተደረገና ለፌደሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ ከቀረበ “በጉልበት የያዛቸውን ራያና ወልቃት ስለሚያጣ” ነው ብለውም ያምናሉ።

“የራያና ወልቃይት ጥያቄ አዲስ አይደለም” የሚሉት ዘፋኒያ፥ “የኹለቱ አካባቢዎች ጉዳይ ኢትዮጵያንና የፌደራል ስርዓቱን ይታደጋል ተብሎ የሚታመንበትን ኮሚሽን መቃወሚያ ሊሆን አይገባም” ሲሉም ይመክራሉ።

በሌላ በኩል “ሕገ መንግሥቱ ለዓመታት የመጨቆኛና ማጥፊያ መንገድ ሆኖ ነው ያገለገለው” የሚሉት አግዘው፥ “ዛሬ ላይ እንዴት መከላከያ ሊሆን ይችላል” ሲሉም ይጠይቃሉ። መኮንን በበኩላቸው “ሕገ መንግሥቱ እስከዛሬ ስላልተከበረ ዛሬ መከበር የለበትም አይባልም፤ ዛሬ ላይ መከበር ከጀመረም በጎ ነው” ይላሉ።

የተጠሪነት ጉዳይ
ኮሚሽኑ ከሚነሱበት ጥያቄዎች አንዱ የተጠሪነቱ ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል ለጠቅላይ ሚነስትሩ (ለአስፈፃሚው አካል) ተጠሪ መሆን የለበትም የሚሉ ባለሙያዎች ሲኖሩ፥ በሌላ በኩል ተጠሪነቱ ለፓርላማው (የሕዝብ ተወካዮችና ፌደሬሽን ምክር ቤቶችም) ጭምር ስለሆነና የመጨረሻ ውሳኔ አሳላፊው ፌደሬሽን ስለሆነ ችግር የለውም በሚል ይሟገታሉ።

መኮንን ኮሚሽኑ “የሽወዳ መንፈስ አለበት፣ እንደሚባለው የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቦ ያልፋል ተብሎ አይታሰብም” ይላሉ። ተጠሪነቱ ለአስፈፃሚው አካል መሆኑም ለፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በር ከፋች እንዳይሆን ሥጋት አላቸው።

ኮሚሽኑን ያቋቋመውና ተጠሪነቱም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ብቻ ቢሆን ኖሮ ችግር አልነበረበትም ማለት ነው ወይ? ለሚለው የአዲስ ማለዳ ጥያቄ መኮንን “በትክክል” በማለት ይመልሳሉ። እንደሳቸው ከሆነ ተጠሪነቱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢሆንማ ሕገ መንግሥታዊ ይሆን ነበር። ምክንያቱም ምክር ቤቱ ሥራውን ለማሳለጥ ሲል ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴዎችን የማደራጀት ሥልጣን ስላለው እንደሆነም ያክላሉ።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ የአማካሪነት ሚና ኖሮት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሚና ስለማይነካ የሕግ ጥሰት የለውም የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። ዘፋኒያ በበኩላቸው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን ለፓርላማውም ስለሆነ ችግር የለበትም ይላሉ። አዋጁ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚንስትሩ መሆኑን አስቀምጧል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ውሳኔና ሕገ መንግሥቱ
የክልሉ ምክር ቤት እንዴትና በምን አግባብ በሚለው ላይ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 1 (“ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም” በሚለው) መሠረት ኮሚሽኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በማለት ተፈፃሚ እንዳይሆንና ዳግም እንዲጤን መወሰኑን አሳውቋል።

የክልሉ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአንድ በኩል በራሱ የክልሉ ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው የሚሉ ባለለሙዎች ተደምጠዋል። ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል የሚባልባቸውን ጉዳዮች አብራርቶ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቤቱታን ማቅረብ እንጂ ክልሉ በምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፍና መግለጫን ማውጣት በራሱ ሕገ መንግሥትን መጣስ ነው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። ዘፋኒያ ስለዚህ ሲያስረዱ “ተጥሷል” የሚባለውን በዝርዝር አመልክቶ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ አዋጁን ውድቅ ማድረግ ሲቻል፥ “የ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተወካይ የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን አዋጅ አልቀበልም ማለት ራስን እንደሉዓላዊ አገር መቁጠር፣ የአገርን ደኅንትና ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ መጣል ነው” ይላሉ። ክልሎች ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች አመቺነት የሚቋቋሙ እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊ አገር አይደሉም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ የምትባል አንዲት ሉዓላዊ አገር ነው ያለችው የሚሉት ዘፋኒያ “አንድ ክልል ለራሱ ስላልጣመው አልቀበልም ማለት አይችልም፤ ኢ-ሕገ መንግሥታዊም ነው” ሲሉ ያክላሉ።

መኮንን እንደሚሉት ክልሉ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል፤ አልቀበለውም፣ ውሳውኔው እንደገና ይጤን ማለቱ ነውር ባይሆንም የሔደበት አግባብ ስህተት እንዳለበት ያስረዳሉ። ይህም “ዝም ብሎ አልቀበለውም ማለት ሳይሆን በሕገ መንግሥቱና በፌደራሊዝሙ ስርዓት ካመነ ጥያቄውን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔና ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ አለበት” የሚል ነው። ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የሚቀርበው ለኹለቱ አካላት እንደሆነም ያስታውሳሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የትግራይ ክልል ምክር ቤት ጥያቄውን ለፌደሬሽን ምከር ቤት አቅርቦ ውሳኔን መጠበቅ ሲገባው፥ አልቀበልም በሚል መወሰን የሕግ ጥሰት ያለበት አካሔድ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 74 ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠውን ሥልጣን የሚፃረር መሆኑንም የሚያነሱ አሉ።

መፍትሔው ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓትና የሥልጣን ክፍፍል በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል የውሳኔ መጋጨት ሲያጋጥም የየትኛው ውሳኔ የበላይ ይሆናል የሚለው በግልጽ የተቀመጠ ሕግ የለውም የሚሉት መኮንን ይልቁንም ኹለቱም የእኩል ሥልጣን ባለቤት እንደሆኑ ያነሳሉ። ይሁንና ተቃርኖው ስላጋጠመ መፍትሔው በትብብር መንፈስ መሥራትና የፌደራል ስርዓቱን ከአደጋ መታደግ እንደሆነ ያሠምሩበታል።

የሕግ ባለሙያው ዘፋኒያ በፌደራሉና በክልል መንግሥታት መካከል በውሳኔ መጋጨት ሲኖር ጉዳዩ አገራዊ ከሆነ የሚፀናው ውሳኔ የፌደራሉ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። የአስተዳደር ወሰኖችን የመከለሉና የማንነት ጥያቄዎች አገራዊ ስለሆኑ የፌደራሉ መንግሥት ውሳኔ በየትኛውም ክልል ያለቅድመ ሁኔታ እንደሚፈፀምም ያክላሉ። አሁን ላይ የፌደራል መንግሥቱ (የፌደሬሽን ምክር ቤት) ጣልቃ መግባት አለበት የሚል አቋም አላቸው። ምክር ቤቱ ኃላፊነት ወስዶ ከክልሉ ጋር መወያየትና መግባባት እንዳለበትም ይመክራሉ። ኮሚሽኑ በገለልተኛና ሳይንሳዊ መንገድ ጥናት አድርጎ ሐሳብ የሚያቀርብ መሆኑም በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች መፍትሔን ለመቸር አጋዥ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደሚባለው የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣን ተፃራሪ ሳይሆን ምክር ቤቱን የበለጠ ጠንካራ የሚያደርገው ይሆናልም ብለው ያምናሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here