“ረሃብ ጊዜ አይሰጥም፤ በረሃብ ከመሞት…፣ የራበው ሕዝብ…” እየተባለ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ብንሰማም፣ ድርቅ ሳይኖርና ተፈጥሮ ፊቷን ሳታዞርብን ሕዝብ እየተራበ መሆኑን እየሰማን እንገኛለን። ዜናውን እንዳደመጥን የማይሰማን፣ ተሰምቶንም ምንም የማናደርግ ከሆንን እያደር መልመዳችን ብቻ ሳይሆን ልንመልሰው የማይቻለን እልቂት ውስጥ እንደሚከተን ልንረዳ ይገባል።
በጦርነት ወቅት የሰውን ልጅ የሚገድለው ፈጣኑ ጥይት ብቻ ሳይሆን፣ ረሃብ በጅምላ አሰቃይቶ በመግደሉ ለዘመናት የማይረሳ የአእምሮ ጠባሳ ለትውልዶች ትቶ ይቆያል። አሁን እየተከሰተ ያለውን ሰው ሠራሽ ረሃብ ይቅርና በተፈጥሮ የአየር ጸባይ መዛባት ምክንያት በ66 እና በ77 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን መዘዝ በዘመኑ ያለፈ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ያልነበረበትም የሚረሳው አይደለም። ሁነቱ እርስበርስ ካመጣብን የአመለካከት ለውጥ ይበልጥ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መዝገበ ቃላት ላይ የረሃብ ማብራሪያ ምሳሌ እስክንሆን ድረስ ማሳቀቂያ ሆኖ መቆየቱ የማያቆስለው ያለ አይመስልም።
ኢትዮጵያ እስከዛሬ በተለያ ጊዜያት ባጋጠሟት ረሃቦች ቂም የሚያዝበትና አስከትሎታል የሚባል ወገን ባይኖርም፣ መርዳት እየቻሉ ያልሞከሩ፣ እንዲሁም ሌላው እንዳይረዳ በመደበቅና በማስተጓጎል ስማቸው በክፉ የሚነሳ አሉ። ይህ አይነት የቅርብ ታሪክ እያለን፣ አሁን በአጭር ጊዜ ውስጥ ድሃው ሕዝብ እንዲራብ ያደረጉና ተርቦ እንዲቆይ ያደረጉ፣ እንዲሁም መርዳት እየቻሉ ሳይረዱ የቆዩ፣ ተገቢውንም ትኩረት ሰጥተው ሌላውም እንዲያሳስበው ያላደረጉ ኃላፊነት ሊሰማቸው የሚገባ አካላት ይብዛም ይነስም ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። አንድም ሰው ምግብ አጥቶ ለሞትም ሆነ ለበሽታ እንዳይዳረግ የማድረጉ ኃላፊነት የኹሉም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
የሚችሉትን ባለማድረግ ከሚመጣ የሕሊና ፀፀት ለመዳን፣ እንዲሁም ከተጠያቂነት ለመትረፍ ዕርዳታ ማድረግ ያለበት ኹሉም እንደሆነ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ወደ ጦር ሜዳ መዝመት ግዴታ ሊሆን እንደሚችል ሕግ ቢደነግግም፣ የመንግሥት ሠራተኛን ደሞዝ ከመሰብሠብ ውጭ በኹሉም ላይ የተጣለ ግዴታ የለም። በፈቃደኝነት ላይ እየተባለ በይፋ ቢነገርም፣ ግብር የሚሰበሠብበትና የጋራ ዓላማ የሚፈፀምበት ገቢ በቂ ካልሆነ በሌሎች አገራት እንደሚደረገው ወደ ግለሰቦች ግዴታው ማምራቱ አይቀርም።
በጥንት ዘመን ለንጉሰ ነገሥት ጦር ስንቅ የማቅረብ ግዴታ የተጣለበት ጦሩ ሲያልፍ ያረፈበት አካባቢ ሕዝብ እንደሆነ በነገሥታቱ ዐዋጅ ቢደነገግም፣ ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆነ አካባቢን ጦሩ ዘርፎ እንዲበላ ሊታዘዝ ይችላል። ይህ ዓይነት ዐዋጅ ግን ወታደሮች ኹሉን አሟጠው እንዲወስዱ አይፈቅድም። ለአርሶ አደሮቹም ሆነ ለአርብቶ አደሮቹ መሠረታዊ ኑሮ መግፊያ የሚሆኑ የእርሻም ሆኑ የሚታለቡ ከብቶችን መንካት እንደማይችሉ በሕግ መደንገግ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጽሞ ዐዋጁን ተላልፎ የተገኘ ከተመሰከረበት ከባድ ቅጣት እንደሚከተለው አጤ ቴዎድሮስ ጫጩት የታቀፈች ዶሮ የበላ የገዛ ወታደራቸው ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ የሚያስረዳ ነው። በዚህ ዐዋጅ መሠረት ጦሩም ሆነ ዘማቹ እንዲሁም በጦርነቱ የተፈናቀሉን በማስተናገድ ለሚደርስባቸው ጉዳት የኢኮኖሚ ጫናውን እንዲቋቋሙ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ማዕከላዊውን መንግሥት በመጠየቅ ከግብር ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ድጋፍ የሚያገኙበት አሠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።
በሰሜን ምስራቋ ወሎ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ለዘማቾች የሚደረገው ርብርብ የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ ውጊያ ሸሽተው የተፈናቀሉትን በተመለከተ እየተደረገ ያለው ዕገዛ ግን ብዙ ቅሬታዎችን እያስነሳ ነው። ከመጠለያ ቦታ ዕጥረት ጀምሮ፣ ምዝገባው፣ የዕርዳታ መቀበያውና ማከፋፈያው መንገድ፣ የሰብሳቢውና አከፋፋዩ ማንነት እንዲሁም የችግሩ አድማስ በመስፋቱ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ የሚናገሩ እየበረከቱ ናቸው። በየሜዳው ረዳት አጥተው ከወለዱ እመጫቶች ጀምሮ የጦርነቱ ጉዳተኞች፣ አቅመ-ደካሞች፣ አዛውንትና ሕፃናት ቅድሚያ ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
የተረጂው ቁጥር እያደር በሚጨምርበት ኹኔታ ያለውን እውነተኛ ቁጥር ማወቁም አዳጋች እንደሆነ እየተነገረ ነው። ኹሉም መጠለያ ጣቢያ ባለመግባታቸው የተገኘችውን አነስተኛ ዕርዳታ እንኳን በፍትሐዊነት ማከፋፈል አልተቻለም። መድሎና መገለል ደረሰብን ብለው ቅሬታ የሚያቀርቡ ተፈናቃዮች የመኖራቸውን ያህል፣ መተሳሰቡ እንደቀረና ድጋፉ በሽሚያ መልክ እተከናወነ መሆኑን የሚያነሱ ባለሥልጣናት ጭምር ቅሬታቸውን አሰምተዋል። አቅም አላቸው የሚባሉና በአጭር ጊዜ የምንመለስ መስሎን ቤት በመከራየታችን እንደማንኛውም ጉዳተኛ እየታየን አይደለም እያሉ ስሞታ የሚያሰሙም አሉ።
በመጠለያ ጣቢያ ያለው አብዛኛው ተፈናቃይ ምንም ደጋፊ የሌለው ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከቁጥሩም አኳያ ቅድሚያ ተሰጥቶታል የሚሉ ቢኖሩም፣ ትኩረቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። ትክክለኛ ቁጥሩን ለማወቅ የሚያስቸግር በርካታ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ከከተሞች በመሸሽ ወደ ገጠር ቀበሌዎች በየዘመድ አዝማዱ ቤት እንደተጠለለም ይታወቃል። በዚህ መንገድ ከቆየ የሌላውን ሕይወት እያናጋ የተረጂውን አጠቃላይ ቁጥር ከማብዛቱ አስቀድሞ ኹሉንም በየደረጃው ማዕከል ያደረገ ሥርጭት ማድረግ ያስፈልጋል።
የሥርጭቱና የችግሩ አድማስ ከታወቀ በኋላ መድረስ የሚችልበትን ኹኔታ በፍጥነት ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህ ተግባር ጎን ለጎን ገደብ የሌለው ዕርዳታ በውዴታ ግዴታ ለማሰባሰብ የተለያዩ መንገዶችን ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። የመንግሥት አደረጃጀቶችንም ሆነ፣ ማኅበራዊ ዓላማ ኖሯቸው የተቋቋሙ አደረጃጀቶች ለእንዲህ አይነት ዓላማ መጠቀም ካልተቻለ ለመቼ ሊሆኑ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ዕርዳታ ማሰባሰቡ በዘመቻ መልክ ሲሆን ላልተፈለገ ወንጀል እንዳያጋልጥ ጥንቃቄና ቁጥጥር ያስፈልጋል። ለግል ተልዕኳቸው ለመጠቀምም ሆነ ዕውቅናና ለማግኘት፣ አሊያም አላግባብ በሒደቱ ለመበልፀግ የሚያስቡ ካሉ አስተማሪ የሆነ ፈጣን ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። እንዲህ ለድሃ የተባለን ሀብት ዘረፉ ብሎ በድሃ በጀት አስሮ አስቀምጦ መቀለቡ ስለማያዋጣ፣ የተለየ አይነት አስተማሪ ማረሚያ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውልበት አሰራር ሊታሰብበት ይገባል። ይህን እኩይ ክስተት ተጠቅመው ተገቢ ያልሆነ ተግባር የሚፈፅሙ ገንዘቡን ማጉደላቸው ብቻ ሳይሆን ሕዝብ የሚኖረውን አመኔታ የሚያሳጡ በመሆናቸው እንደጠላት ብቻ ሳይሆን ትውልድ ገዳይ ተደርገው መታየት አለባቸው።
በተቀደደ በርሚል ብዙ ቢሞላም፣ ጥቂቶች ከስሩ ቀደው የሚያጎሉት ከሆነ መቼም ሞልቶ ሊቆይ አይችልም። መያዣው ተቀዶ የሚሞላ ራሱ ጥፋተኛ ነው ብለው አፋሮች እንደተረቱት፣ በቀዳዳው ላይ ሙሉ እያሉ የተረፈው ይበቃል የሚል አይነት አስተሳሰብ ያላቸው አስተባባሪዎችም ሆኑ ሹመኞች ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል። የሚሰጥ ሰው ሀብቱ ባያልቅ እንኳን የሰው ትዕግስት በቀላሉ ሊያልቅ ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ተስፋ የቆረጠን ሕዝብ መልሶ ለማሳመን ምን ያህል አዳጋች እንደሚሆን ከሥልጣን ከተወገዱት አካላት በቀላሉ መማር ይቻላል። የጠፋ ስምንም በቀላሉ ማድስ ስለማይቻል፣ የረሃቡ ጉዳይ ቀጥታ ሕዝብን ስለሚመለከት ከጦርነቱ ማስበለጥ ባይቻል እንኳን በተመሳሳይ መልኩ እኩል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ቢሮክራሲው በበዛ ቁጥር በረሃብ ሊያልቁ የሚችሉ ዜጎችን ቁጥር ከግምት በማስገባት በአስቸኳይ ወደ ተግባሩ መገባት አለበት። የችግሩ አስከፊነትም ግልፅ ስለሆነ፣ የጦርነቱም ሆነ የረሃቡ ክስተትም እርስበርሱ የተሳሰረ ጉዳይ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ከሰው ልጆች ኹሉ እንዲሰጠው አዲስ ማለዳ አበክራ ትጠይቃለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014



