በአዲስ አበባ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ከ200 በላይ ሞተር ሳይክሎች ተወረሱ

0
1778

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲሠሩ ፈቃድ ከተሰጣቸው የሞተረኞች ሎጎ ጋር በማመሳሰል በሕገ-ወጥ መንገድ ሲሠሩ የተገኙ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሞተር ሳይክሎች መውረሱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።
“በሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ሎጎ በማመሳሰል ሲያሽከረክሩ ተገኝተዋል’’ የተባሉት ሞተረኞቹ እንደየጥፋታቸው የእስራትና የገንዘብ ቅጣት እንደተፈረደባቸው የትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሸን ዳይሬክተሩ አረጋዊ ማሩ ተናግረዋል።

ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሚያሽከረክሩ ሰዎችን የመቅጣትና ንብረቶችን የመውረስ ሥልጣን በመመሪያ የተሰጣቸው መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲሽከረከሩ የተገኙት 200 ሞተሮች እንደተወረሱና አሽከረካሪዎቹም በሕግ እንደተጠየቁ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ዳይሬክተሩ አክለውም በሕግ የተቀጡት 200 ሞተረኞች የሞተር እንቅስቃሴ ፍቃድን አስመልክቶ በአገልግሎት እንዲሠማሩ ነጭ በቢጫ እንዲሁም ነጭ በሰማያዊ አርማ ከተሰጣቸው ሞተረኞች ውጭ በተመሳሳይ አርማ ሲንቀሳቀሱ በትራፊክ ፖሊሶች አማካይነት የተደረሰባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በኹለት አይነት አገልግሎት ብቻ የሞተር እንቅስቃሴ መፈቀዱን የገለጹት አረጋዊ ማሩ፣ ዕቃ የማጓጓዝ ፍቃድ የተሰጣቸው ሞተሮች እያንዳንዳቸው ነጭ በቢጫ አርማና የደርጅቱን መለያ እንዲለብሱ ተደርገው የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ፣ በኹለተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ አንድ አንድ ሰው ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ፍቃድ የተሰጣቸው ነጭ በሰማያዊ አርማ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

አረጋዊ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በአጠቃላይ በከተማዋ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው ሦስት ሺሕ 600 ሞተሮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ሞተሮች ውጭ በተለያየ አጋጣሚ በከተማዋ ውስጥ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ እያሽከረከሩ በትራፊክ ፖሊሶች ቁጥጥር ሥር የዋሉ ሞተረኞች እየተቀጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ሦስት ሺሕ 600 ሞተሮች ማንኛውንም ዕቃና ሰው በመጫን የሞተር አገልግሎት ለመስጠት በአዲስ አበባ ታርጋ ቁጥራቸው የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ ከተለያዩ ክልሎች “በስርቆትም ሆነ በግዥ’’ ወደ ከተማዋ የገቡ በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች እንዳሉና አስፈላጊው ዕርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት።

እንደ ትራንስፖርት ቢሮው ገለጻ ከሆነ፣ ምንም እንኳን በሞተሮቹ አማካይነት የስርቆት ወንጀል በመስፋፋቱ የሞተር እንቅስቃሴ ቢታገድም፣ ትራንስፖርት አንዱ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ዘርፍ በመሆኑ በሥራ ላይ የነበሩ ወጣቶችን ዕድል ላለመዝጋት እና ምንም እንኳን ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ባይቀርፈውም ሥራን ለማቀላጠፍ ሲባል ዕቃና ሰው ለማጓጓዝ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጭ ሕገ-ወጥ ሞተሮች እየተገኙ ነው ብለዋል።

አርማቸውን ከሕጋዊው የሞተር ሳይክሎች አርማ ጋር በማመሳሰል በየሠፈሩ የሚንቀሳቀሱ ሞተረኞች በየጊዜው እየተገኙ ነው የሚለው ትራንስፖርት ቢሮው፣ ለከተማዋ ደኅንነት ሥጋትን ስለሚፈጥሩ ማንኛውም ማኅበረሰብ በማጋለጥ እንዲተባበር አሳስቧል።
የከተማዋን ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር እያንዳንዱ ሞተር ከየት ወደ የት እንደሚጓዝ ለማወቅ ጂ ፒ ኤስ የሚገጠምለት ሲሆን፣ ሌሎች ከዚህ ውጪ የሆኑ ሕገ-ወጥ ሞተሮች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚወረሱም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ማንኛውም የሞተር አገልግሎት ማግኘት የሚፈልግ የግልም ሆነ የመንግሥት ድርጅት ሰውን ወይም ዕቃን ለማንቀሳቀስ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ ፈቃድ የማግኘት መብት ቢኖረውም፣ ያለ ፈቃድ ማሽከርከር በተለይም በዚህ ወቅት አገሪቱን ለችግር ስለሚዳርግ ሕገ-ወጥ ተግባር መሆኑን ማወቅ ይገባልም ብለዋል።

በየጊዜው ስለሚጨምሩ ቁጥራውን ለመግለጽ የሚያስቸግሩ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሞተሮች በብዛት ተገኝተው እንደተወረሱና አሽከርካሪዎቹም በሕግ እየተቀጡ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በትራንስፖርት ቢሮ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ከተመዘገቡት ሕጋዊ ሞተረኞች ጋር የሚመሳሰል አርማ በማሠራት በሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የተሠማሩ ሞተረኞችን ለማጣራትም ክትትትሉ የቀጠለ መሆኑን አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ በመጨረሻም እስካሁን እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው የተመዘገቡት ሞተረኞች ብቻ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ሥርቆትና የትራፊክ አደጋ መስፋፋትን ለመቀነስ በማሰብ ከተመዘገቡት ውጭ ላሉ ሞተረኞች እንዲገደብ የተወሰነው እንቅስቃሴ ባለበት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here