የ ‘Ethiopian Business Review’ መጽሔት100ኛ ዕትምን በማስመልከት የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ

0
655

የ ‘Ethiopian Business Review’ መጽሔት፣ የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እና የአዲስ ማለዳ መጽሔት አሳታሚ የሆነው ‘ቻንፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንዲሁም የ ‘Ethiopian Business Review’ (EBR) መጽሔት 100ኛ ዕትም የምስጋና መርሃ ግብር ባሳለፍነው ማክሰኞ መስከረም 4/2014 በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩም ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የ’ቻንፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ መሥራች አማንይሁን ረዳ ስለ ድርጅቱ አመሠራረትና አጠቃላይ የሥራ ሒደት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ‘Ethiopian Business Review’ (EBR) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያግዙ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ዓላማው አድርጎ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ሥራ የጀመረ መሆኑን የገለጹት አማንይሁን፣ መጽሔቱ በ10 ዓመታት የኅትመት ጉዞው የተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ በአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የራሱን የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈዋል፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ አልፎና ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለውጤት መብቃት ደግሞ ከፍተኛ ድል ነው” ያሉ ሲሆን፣ በተለይም የግል የመረጃ ሰጪ ተቋም ሆኖ ይህን ያህል ዓመት በኅትመት ላይ መቆየት በራሱ ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

የ’ቻምፕየን ኮምዩኒኬሽንስ’ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታምራት አስታጥቄ በበኩላቸው፣ የመጽሔቱ 100ኛ ዕትም ለመድረስ ጉዞው ቀላል እንዳልነበር አውስተዋል። ይልቁንም በኢትዮጵያ ካለው ያልዳበረ የንባብ ልምድ እንዲሁም ብዙዎች በጅምር በሚያቋርጡበት ሁኔታ ላይ ዘልቆ ዓመታትን መቆየቱ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

አያይዘውም በድርጅቱና አጠቃላይ የኅትመት ሒደቱ ላይ የገጠሙ ተግዳሮቶችን አንስተዋል። ከእነሱ ውስጥም መጽሔቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደመዘጋጀቱ ውስን የኅትመት መጠን፣ ኋላ ቀር የሥርጭት ሥርዓት፣ የኅትመት ዋጋ በየወቅቱ መናርና የጋዜጠኞች የሙያ ብቃት እንዲሁም በኅትመት ሚዲያው ላይ የተፈለገውን ያህል ያለመቆየትን ችግር ጠቅሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here