ሕገ-ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ በመዲናዋ

0
1899

አንዲት ውብና ጽዱ የሆነች ከተማ ከመልካም መገለጫዎቿ ውስጥ አንዱ የመንገዶቿ ጥራትና ምቾት ነው። ፍልስስ ያሉና በእግረኞች የማይጨናነቁ መንገዶች ሊኖሯት ይገባል። ይህም ለነዋሪዎቿ ጤና እና ደስታን ከመፍጠር በላይ ከሌሎች ከተሞች በተሻለ ለኑሮ ተመራጭና አልፎ ተርፎም የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋታል። በዚህም በየጊዜው ጥራታቸውን የጠበቁ መንገዶችን በመገንባት ውበቷን ትጨምራለች፤ ብልጽግናዋንም ታፋጥናለች።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በብዙ ከተሞች ያሉ መንገዶች ለንግድና ለመሳሰሉት ሕገ-ወጥ ተግባሮች በመዋል በከተማ ነዋሪዎች ላይ አሉታዊ ጫና በመፍጠር እና የከተማዋንም ገጽታ በማበላሸት ይታወቃሉ። ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
በመዲናዋ ውስጥ ባሉ ብዙ መንገዶች ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ሕገ-ወጥ ንግድ መኖሩ ይታወቃል። ይህ ተግባር ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ የእግረኛ መንገዶች ላይ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ዘርግተው በሚሸጡ ግለሰቦች የሚደረግ ነው።

ሕገ-ወጥ ንግዱ ከልብስና ጫማ ጀምሮ የቤት ዕቃዎች፣ የመጻሕፍት እና የትምህርት ቁሳቁሶች፣ የኮስሞቲክስ ምርቶችና የሌሎች ጥቃቅን ሸቀጣሸቀጦች ሽያጭ ያካተተ በመሆኑ በቀላሉ የማይቆም፣ ሠፊና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ይህ ሕገ-ወጥ ንግድ በርካታ ጉዳቶችን የሚያስክትል እንደሆነም ይነገራል።

ማንኛውም ግለሰብ የንግድ ሥራውን ማከናወን ያለበት ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ በተፈቀደ የንግድ ቦታ መሆን ያለበት ሲሆን፣ መንግሥትም ይህን የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት። ይህ ካልሆነ ደግሞ ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች በዚህ ወቅት በመዲናዋ ከሚታየው በላይ በመብዛት በከተማዋ ገጽታና በሕብረተሰቡ ማኅበራዊ ኑሮ ብሎም ጤና ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖ የጎላ ይሆናል። ከዚያም አልፎ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ጫና እንዲሁ ከፍ ያለ ይሆናል።

አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ ካነጋገረቻቸው መካከል አድነው የተባሉ ግለሰብ እንደሚሉት፣ “ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች በዋናነት የትራፊክ መጨናንቅ በመፍጠር በእግረኞች ላይ ጉዳት ያስከትላሉ። እንዲሁም፣ መንገዶች እንዲቆሽሹና የከተማዋ ገጽታ እንዲበላሽ ያደርጋሉ” ብለዋል።

በብዙ መንገዶች ላይ የንግድ ሥራ ስለሚሠራ ነዋሪዎች የእግር ጉዞ ለማድረግ እና ለመዝናናት እንደሚቸገሩ ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተገነቡት መንገዶች ያለ ጊዜያቸው እንዲያረጁና የታቀደላቸውን አገልግሎት እንዳይስጡ ያደርጋል ባይ ነው።
መንገድ ላይ ልብስና ጫማ ሲሸጡ የነበሩና የመንገድ ዳር ንግድን በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ ሐሳብ የሰጡ የተወሰኑ ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ መንገድ ዳር እንድንሠራ ያደረገን ድህነትና የአቅም ማነስ እንጂ፣ ሥራችን በነዋሪዎች እና በከተማ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጸዕኖ እንዳለው እናውቃለን ይላሉ። መንገድ ዳር ዘርግተው ልብስና ጫማ መሸጣቸው እግረኞች ተጨናንቀው እንዲጓዙና መንገዶችም እንዲቆሽሹ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከዚያም ባለፈ መንገዶቹ ውበት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ደርጊት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። እኛም የምንሠራው በልቶ ለመኖርና ግዴታ የቤት ኪራይ ለመክፈል በመሆኑ፣ በደንብ አስከባሪዎች ወከባ እየደረሰብንና ንብረታችንን እየተቀማን መንገድ ዳር የመሥራት ፍላጎት የለንም ብለዋል።

ሕጋዊ ሆነው ሥራቸውን የሚሠሩበት ቦታ ቢያገኙ ከማንም በፊት ተጠቃሚ የሚሆኑት ራሳቸው እንደሆኑ የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ ሸቀጣቸውን ለመሽጥ ሲጮሁ ስለሚውሉ ከድካም ባለፈ ወደፊት የጤና እክል ሊፈያጋጥመን ይችላል የሚል ሥጋትም አላቸው።
ነጋዴዎቹ በሕጋዊ መንገድ የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም የሌላቸው በመሆኑ እና እገዛ የሚያደርግላቸው አካል ባለመኖሩ ተቸግረዋል። በዚህም ምክንያት የመንገድ ላይ ንግዱ በራሳቸውና በማኅበረሰቡ ላይ ያለውን ጉዳት እያወቁም ቢሆን ችላ ማለትን መርጠው ሥራውን እንዲሚሠሩ ይናገራሉ።

ከዚህ በፊት ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶችን ለማስቆም በርካታ ጊዜ የተሞከረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ማስቆም አልተቻለም። ይልቁንም ተግባሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ሲሄድና በዚያው ልክ ጉዳቱም አብሮ ሲጨምር ይታያል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንገድ ዳር ንግድ ለምን ማስቆም አልተቻለም በሚለው ጉዳይ ለአዲስ ማለዳ ሐሳብ የሰጡት ሔኖክ የተባሉ ግለሰብ ደግሞ፣ ነዋሪው ሸቀጦችን ወደ ሱቅ በመሄድ በውድ ዋጋ ከመግዛት ይልቅ መንገድ ላይ በዝቅተኛ ዋጋ መግዛትን ይመርጣል። ይህም ነጋዴዎችን ገበያ እንዲያገኙ ስለሚያደርጋቸው ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶችን በቀላሉ ለማስቆም እንዳይቻል አድርጓል ሲሉ ይገልጻሉ። ይህን ተግባር የማስቆሙ ኃላፊነት ከመንግሥት እኩል የነዋሪውም ጭምር ነው ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት ማሞ የተባሉ ግለሰብ ደግሞ፣ “መንገድ ዳር ንግድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ሥራ እንዲያቆሙ ከማድረግ ይልቅ ሕጋዊ መስመር ተከትለው በተደራጀ መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ግንዛቤ መስጠት ይገባል ይላሉ። ከዚያም ባለፈ ምቹ የሥራ ቦታና ሁኔታ መፍጠርም አስፈላጊ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ማሞ አያይዘውም፣ “ከዚህ ውጭ ግን የኑሮ ውድነቱ ጣራ በነካበትና መኖር አዳጋች በሆነበት በዚህ ጊዜ ሕገ-ወጥ ናችሁ ብሎ ማባረር ብቻ ችግሩን አይፈታውም” ሲሉ ገልጸዋል። መንግሥት ሕገ-ወጥ የመንገድ ላይ ንግዱ በነዋሪዎች እንቅስቃሴና በከተማ ጽዳት ላይ ከሚያስከትለው ችግር ጎን ለጎን ኑሯቸውን ከሥራው በሚያገኙት ዝቅተኛ ገቢ የሚመሩ ዜጎችንም ሕይወት ለመለወጥ ኃላፊነት በመውሰድ መሥራት እንዳለበት ጨምረው ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች በተለይ በበዓላትና በክረምት ወራት በነዋሪዎች ላይ የሚያስከትሉት ጫናም የበዛ ነው። በዓላት በመጡ ቁጥር መንገድ ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚነግዱ ግለሰቦች ቁጥር ይጨምራል። ከዚህ በተጨማሪ ነዋሪዎችም ከወትሮው ይልቅ ለበዓል ሸመታ ከቤታችው የሚወጡበት ጊዜ ስለሆነ የሰዎች ትርምስና መጨናነቅ ይጨምራል። ይህ ደግሞ ሌቦች በቀላሉ በሰዎች ኪስ በመግባት ስርቆት እንዲፈጽሙ ከማድረጉም በላይ፣ በበዓላት ወቅት የሚፈጠረው ትርምስና መጨናነቅ የሚያስከትለው የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ ነው።
በክረምት ወራት የእግረኛ መንገዶች ላይ ውኃ ሊያቁር ስለሚችልና የቀሩትም በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ስለሚያዙ ዜጎች እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ከማድረግ በተጨማሪ ለመኪና አደጋ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በተለይ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ባለበት በዚህ ወቅት ለእግረኞች ትርምስና መጨናንቅ እንደምክንያት ስለሚሆኑ ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች በዚህ ረገድ የሚያስከትሉት የጤና ጠንቅ ቀላል የሚባል አይደለም። በንክኪና በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች በዚህ ጊዜ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድል ያገኛሉ።

በእግረኞች ደኅንነት፣ በከተማ ጽዳት፣ በመንገዶች ጥራትና አገልግሎት፣ እንዲሁም በከተማዋ ገጽታ ላይ ይህን ሁሉ ችግር እያስከተለ ያለው ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግድ ሕጋዊ ሁነው የሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖም ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል።
በሕጋዊ መንገድ ሥራቸውን በመሥራት ለመንግሥትም የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ላይ ያሉ ነጋዴዎች ኪሳራ እንዲያጋጥማቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ደግሞ ሕጋዊ ነጋዴዎችም ሕገ-ወጥ ንግዱን እንዲቀላቀሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። መንግሥት አጠቃላይ ኹለንተናዊ ችግሮቹን ተመልክቶ ለችግሩ ፈጣን ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ አዳዲስ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች እንዲፈጠሩ እና ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ ያደርገዋል።

ከፈቃድ አሰጣጥና ሕገ-ወጥ ንግዱ በኢኮኖሚ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን እንደማይመለከተው ነው። ቢሮው በዋናነት ንግድ ፈቃድ መስጠት፣ መከታተልና ድጋፍ ማድረግ እንጂ ሕገ-ወጥ ንግድን አይከታተልም ያሉት ኃላፊው፣ ሕገ-ወጥ ንግዱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዳለ ማንኛውም ቢሮ መናገር እንደሚችለው እኛም መግለጽ እንችላለን ሲሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ዳንኤል አክለውም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሕጋዊ ሆነው ነገር ግን መደበኛ ያልሆኑ ቅዳሜና እሁድ “ሰንደይ ማርኬት” በመባል የሚውሉ ንግዶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከአስር ስዓት በኋላ መንገድ ተዘግቶላቸው በጦር ኃይሎች፣ ስድስት ኪሎ እና መገናኛ አካባቢዎች የሚከናወኑ መደበኛ ያልሆኑ ንግዶች በመኖራቸው ቢሮው እነሱን ይቆጣጠራል ብለዋል።

በርግጥም ቅዳሜና እሁድ ከአስር ሰዓት በኋላ መንገድ ተዘግቶላቸው “ሰንደይ ማርኬት” በመባል የሚሠሩ መደበኛ ያልሆኑ ንግዶች አሉ ይበሉ እንጂ፣ እነዚህ ንግዶች ዘወትር የሚከናወኑ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ከሰኞ እስከ አርብ ሰዎች ከሥራ በሚወጡበት ሰዓት የእግረኛ መንገዶችን በመዝጋት መተላለፊያ ያሳጣሉ። ዘወትር ምሽት ሜክሲኮ አካባቢ የሚደረጉ ንግዶች የዚህ ማሳያ ናቸው። በሌሎች አካባቢዎችም ሕገ-ወጥ እና መደበኛ ያልሆኑ ንግዶች መንገድ ላይ በብዛት ሲከናወኑ ይታያል።

በአጠቃላይ፣ የብዙ ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው አዲስ አበባ ግርግርና ወከባ የሌለበት፣ ለኑሮ አመች እንድትሆን የመንገድ ዳር ሕገ-ወጥ ንግድ መኖር እንደሌለበት ይታመናል። ከትራፊክ አደጋ የፀዳ ምቹ የከተማ ትራንስፖርት እንዲኖር፣ የመንገድ ተጠቃሚዎችም ደኅንነታቸው የተረጋገጠ ሆኖ በሠላም ወጥተው በሠላም እንዲገቡ ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግዶች ሥርዓት ሊበጅላቸው ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here