የቤተ እምነቶች ቃጠሎ

Views: 232

ቤተ እምነቶችን እና ምእመናን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቃሚያ እያደረጉ ከጀርባ ያዘሉትን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም መውደቅ መነሳት መቼም የቅርብ ጊዜ ትውስታ እና እየኖርንበት ያለው ነባራዊ ሃቅ ለመሆኑ ማስረጃ የሚያስፈልግ ጉዳይ አይደለም። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከራስ ዳሽን አናት እስከ ዳሎል ረባዳ መሬት ድረስ የቤተ እምነቶችን እና አማኙን ኅብረተሰብ መጠቀሚያ ያላደረገ የፖለቲካ አጀንዳ አቀንቃኝ ማግኘት እጅግ ፈታኝ የሆነበት ዘመን ላይ ለመድረሳችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሱ የመጡት ኹነቶች አይተኛ ማስረጃ ናቸው።

‹‹እኔ ለአንተ ቆሜያለሁ››፣ ‹‹እምነትህ ተጨቁኗል›› እና መሰል ክፍተቶችን በመንገር ወይም ባስ ሲልም ደግሞ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ተግባር አንጸው በሚያሳድጉ ቤተ እምነቶች ላይ፣ የእሳት እና የድንጋይ ናዳ እያወረዱ ‹‹የእንትን እምነት ተከታዮች ጥቃት ፈጸሙ›› በሚል የምዕመኑን ቁስል እየነካኩ ወደማያባራ ውጥንቅጥ ውስጥ ኅብረተሰቡን መክተት ከብዙዎቹ ጥቂት አካሔዶች ናቸው። ምንም እንኳን በደም፣ በዘር፣ በወግ በባህል ቢተሳሰርም፣ በእምነቱ ሳይደራደር ነውና የኖረው፤ ኅብረተሰቡም አብሮት ከኖረው ጎረቤቱ ጋር መቃቃር ይጀምራል። ወደ ተካረረ ጸብም ይገባል፤ ነገሮችም እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት ከወደ አማራ ክልል ሞጣ ከተማ የተሰማው ጉዳይ ደግሞ ትንሽ ሰሚን ግራ ያጋባ ነበር። በአንጻራዊነት በሰላማዊነቷ ስትሞካሽ የነበረችው ጎጃም በምሥራቃዊ ክፍሏ ሞጣ ከተማ አራት መስጊዶች እና አንድ ቤተክርስቲያን በሙሉ እና በከፊል መቃጠላቸው የሳምንቱ መነጋገሪያ እና መነታረኪያም ጭምር ነበር። በወቅቱ መስጊዶች እየተቃጠሉ ከበው የሚጨፍሩ ወጣቶችን ተንቀሳቃሽ ምስልም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በመልቀቅ የውግዘትና የስድብ ዓይነቶች ሲስተናገዱ ነበር።

የመስጊዶችን ቃጠሎ ተከትሎም በመላው ኢትዮጵያ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሕዝበ ሙስሊሙ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሔዱም የአደባባይ ምስጢር ነበር። የሆነው ሆኖ ግን በአንዳንድ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይት ያላቸው ግለሰቦች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለጥፏቸው ጽሑፎች በርካቶችን ኹለት ቦታ ከፍሎ ጸያፍ ቃላቶችን እስከማሰናዘር የሚደርሱ ትችቶችን ሲያስተናግዱ ነበር።

በተለይም ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ሰይፍ እና ሌሎች ስለቶችን በመያዝ እንዲሁም የአረብ አገራትን ባንዲራም በማውለብለብ በግልጽ ጠብ አጫሪነትን እየታወጀ ነው በሚል፤ ብዙዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች መወያያ ርዕስ ሲያደርጉት ሰንብተዋል።

ይህንኑን የመስጊዶች መቃጠል ተከትሎ ትናንት ዓርብ ታኅሳስ 17/2012 ከዓርብ የስግደት መርሃ ግብር (ጁመዓ) በኋላ ሕዝበ ሙስሊሙ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲያሰማ እና ሐሳቡን እንዲገልጽ በርካታ የሙስሊም ሐሳብ አራማጆች ቅስቀሳ ሲያደርጉ የተስተዋለበት ሳምንት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com