ኮሎኔል መለሰ ተሰማ “ተናፋቂ ትዝታችን” የሚል የግለ ታሪክ መጽሐፍ በ2010 አሳትመዋል። ብርሃኑ ሰሙ ይህንን የክቡር ዘበኛ የውስጥ ታሪክ እና ሌሎችንም በውስጡ ያጨቀ መጽሐፍ በማንበብ እነኾ ቅምሻ ይሉናል።
ለአዛውንትነት ያበቃቸውን ዘመናት ወደኋላ መለስ ብለው ሲገመግሙት፥ የጓደኛቸው፣ የወላጅ እናታቸውንና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩባቸውን ዕለታት “መሪር” የሐዘኔ ቀናት የነበሩ ናቸው ሲሉ በ“ልዩ” ሁኔታ የተደሰትኩባቸው የሚሏቸው ደግሞ፣ የመቶ አለቃ ማዕረግ ያገኙበት፣ በሌፍተናንት ኮሎኔልነት የተሾሙበት፣ አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ማራቶን ያሸነፈበት እና የግል ትዝታቸውን ያሰፈሩበት የመጽሐፍ ዝግጅት ያጠናቀቁበት ዕለታትን ነው።
የክብር ዘበኛ ጦር አካዳሚ ሁለተኛ ኮርስ እጩ መኮንኖች የምልመላ፣ የሥልጠና እና የሥራ ታሪክ ምን እንደሚመስል “ተናፋቂ ትዝታችን” በሚል ርዕስ በ234 ገጾች አሰናድተው፥ በ2010 ያሳተሙት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፣ ለሕይወታቸው “ልዩ ደስታ” የፈጠረላቸው መጽሐፍ ተደራሲያንንም የሚያስደስቱ፣ የሚያዝናኑና አዲስ ዕውቀት የሚሰጡ መረጃዎች አቅርበውበታል። መጽሐፉን ለማሰናዳት ያነሳሳቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ፦
“በጦር አካዳሚ በቆየንባቸው ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ፍቅርና መከባበር በመሐከላችን ስለነበረ፥ ያለፈው ትዝታ በወቅቱ እንደቀላል ነገር ቆጥረነው ማስታወሻ ሳንይዝለት ያለፈ ቢሆንም ዛሬ በአዛውንትነት ዕድሜያችን ሆነን ስናስታውሰው አንዳንዱ አስቂኝና ሌላው አሳዛኝ ትርዒት መሆኑን በየትኛውም ቦታ በተገናኘን ቁጥር እያነሳን ስንጨዋወተው ጊዜው ሳይበቃን እንለያያለን…
“ይህ ማስታወሻ ያሳለፍነውን ጊዜያት በናፍቆት የሚያስታውስ ሲሆን፥ ተናፋቂ ትዝታ ብዬ ርዕስ የሰጠሁበትም ምክንያት ሌሎች በሕይወት የሚገኙ የ2ተኛ ኮርስ ጓደኞቼ ይህንን መነሻ በማድረግ እኔ የረሳኋቸውን፣ እነሱ የሚያስታውሱትን ተናፋቂ ትዝታ መመዝገብ እንዲያስችላቸውና እንዲያነሳሳቸው ለማሳሰብም ጭምር ነው” ብለዋል።
የክብር ዘበኛ አመሠራረት ታሪክ ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በፊት መሆኑን የሚገልጸው “ተናፋቂ ትዝታችን” መጽሐፍ፥ በዚያ ወቅት በውጭ አገራት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በእንግሊዞች፣ በፈረንሳዊያን፣ በኢጣሊያዊያን የመሠልጠን ዕድል አግኝተው እንደነበር፣ አገራቱ ኢትዮጵያዊያንን ያሠለጠኑበት ምክንያት “ለአንደኛው የዓለም ጦርነት” ማሰለፍን ዓላማ በማድረግ እንደነበር፣ ዘመቻው ሲያበቃ ኢትዮጵያዊያኑ ከያሉበት ተሰናብተው ወደ አገራቸው ሲመጡም ከቤልጂግ በመጡ አሠልጣኞች ተጨማሪ ትምህርት እንደ አገኙ፣ የመጀመሪያው ክቡር ዘበኛ ከእነዚህ በተውጣጣ አባላት መመሥረቱን ያለመክታል።
ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ በአዲስ መልክ የተዋቀረውን የክብር ዘበኛ ጦር ያደራጁት በጦር ክፍሉ የመጀመሪያ ታሪክ ውስጥ ታዋቂ በነበሩ መኮንኖች ነበር። ለክብር ዘበኛ ጦር ማሠልጠኛ የተመረጠው ቦታ ንፁኅ አየርና ውሃ የሚገኝበት መሆኑ ዋነኛው ምክንያት ሲሆን፥ በተለይ ውሃው በነበረው ጥራትና ንፅኅና ምክንያት “ግርማዊ የሚጠጡት ነው እየተባለ ዘወትር ማታ ማታ ወደ 12፡00 ሰዓት ገደማ ከቤተ መንግሥት ሞተረኛ እየተላከ እየመጣ ከቪላ ሣህለሥላሴ ግቢ ውስጥ በጀሪካን ለቤተ መንግሥት ይወሰድ ነበር።” ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በመጽሐፋቸው ለ“ለቤላ ሠፈር” ሥያሜ መነሻ ስለሆነው “ቪላ ሣህለሥላሴ” ባሠፈሩት መረጃ፦
“በ1933 ግርማዊ ጃንሆይ በድል አድራጊነት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የኢጣሊያ ለጋሲዮን የነበረውን ቦታ ለመጨረሻ ልጃቸው ለልዑል ሣህለሥላሴ መናፈሻና ማረፊያ እንዲሆን ተሰጠ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያና የኢጣልያን መንግሥት ግንኙነት ተሻሽሎ ወደ ኤምባሲ ደረጃ ከፍ ብሎ፥ ቦታው ለኢጣልያን ኤምባሲ እስከ ተመለሰ ድረስ ቪላ ሣህለሥላሴ እየተባለ ነበር የሚጠራው። ይህ ሥም እየተለመደ ሔዶ ያ አካባቢ ዛሬም ድረስ ቪላ በመባል ይታወቃል። አሁን የታክሲ ረዳቶች ተሳፋሪ ሲጠሩ ‘ቪላ’ ለማለት ‘ቤላ’ በማለት ሥሙን ለውጠውት ሕዝቡም እነሱን በመከተል በዚህ ሥም ይጠራዋል።.. ለጦር ትምህርት ቤትነት የተመረጠው ይህ ቦታ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ተወርራ በነበረበት ወቅት የኢጣሊያን መንግሥት ወኪል የነበረው የጄኔራል ግራዚያኒ የክብር ጠባቂዎች መኖሪያና ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር ሲዋጉ የቆሰሉ የኢጣሊያ ወታደሮች ማገገሚያ ነበር።”
ከጣሊያን ወረራ በኋላ የክብር ዘበኛ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ዐፄ ኃይለሥላሴ ወስነው እንቅስቃሴው ሲጀመር፥ ልዑል ራስ ካሣ ሰምተው “ለዙፋንዎ የሚያሰጋ ተቀናቃኝ እያፈሩ ነው” ባሏቸው ወቅት ግርማዊ ጃንሆን “ለዙፋን ብለን አገራችንን ለጠላት አጋልጠን አንሰጥም” ማለታቸውን የሚያስነብበን የኮሎኔል መለሰ ተሰማ “ተናፋቂ ትዝታችን” መጽሐፍ፥ ከክብር ዘበኛ ጋር የሚያያዝ ሰፊ ታሪክ ካላቸው የጦር መሪዎች መሐል ስለ ሜጀር ጄነራል ሙሉጌታ ቡሊና ስለ ብ/ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ የቀረቡ አስደማሚ ምስክርነቶችንም ይዟል።
“ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ በሥራ ሰዓታቸው አንዲት ደቂቃ እንኳን በከንቱ አያሳልፉም፥ ግርማዊ ጃንሆይ ለሥራ ጉዳይ ሲጠሯቸው እንኳ ቶሎ ካላነጋገሯቸው ከጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ወደ ቢሯቸው ይመለሳሉ እንጂ እንደሌሎች መኳንንትና ሚኒስትሮች ደጅ አይጠኑም። ይህንን ደኅና አድርገው የሚያውቁላቸው ጃንሆይ ሙሉጌታን ሲያስጠሯቸው ሥራ በማይበዛባቸው ሰዓት ወይም የፈለጓቸው ለአስቸኳይ ሥራ ጉዳይ ከሆነ ሥራቸውን አቋርጠው ይቀበሏቸዋል እንጂ አያስጠብቋቸውም ነበር።”
ስለ ብ/ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ ለጋስነት፣ አዛኝነት፣ የወላዋይነት ፀባይ እና ቆራጥነት፣ ይህ ተፈጥሮና ባሕሪያቸውም ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ለውትድርና ሙያቸውና ለታሪክ ስላስገኘው ጥቅምና ጉዳትም ሰፊ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ መረጃዎችን ያቀረቡት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፥ “ጄነራል መንግሥቱ ከአዛኝነታቸው የተነሳ ይመስለኛል ከፍተኛ የሆነ የማወላወል ባሕሪይ ያለባቸው በመሆኑ እንደ አንድ ቆራጥ የጦር አዛዥ በአስተዳደር ላይ ቆራጥ ውሳኔ መስጠት ይሳናቸው ነበር። ይህ ባይሆንላቸውም ግን ከሩኅሩኅነታቸው የተነሳ ሥር የሰደደ ቂመኛ ባለመሆናቸው ያስቀየሟቸውን መኮንኖች እየጠሩ ይቅርታ” የመጠየቅ ልዩ ችሎታ እንደነበራቸውም መስክረውላቸዋል።
የ“ተናፋቂ ትዝታችን” ደራሲ ስለ ብ/ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ፣ በ1967 በኦጋዴን ከሻምበል ባሻ ተፈራ አገኘሁት ብለው በመጽሐፋቸው ገጽ 63 ያኖሩት መረጃ የሚያነጋግር ይመስላል። የሻምበሉ ምስክርነት “ጌታዬ በሁኔታው ሳናውቅ ተሳስተናል፣ በጣም ተፀፅተናል፤ ልንለቅዎ ነው የመጣነው፣ የጀመሩትን የመንግሥት ለውጥ ልናደርግ ነው። እርስዎ ይምሩን እባክዎ? መኮንኖችዎን እንፍታቸውና እንዲመሩን ይዘዙልን፣ መሣሪያ በሙሉ በእጃችን ነው ያለው” የሚል ሲሆን “እኔ አብቅቶልኛል፤ የሙከራዬ ዓላማ ከገባችሁ እናንተ ቀጥሉበት” በሚል ብ/ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ የሰጡት ምላሽም ቀርቧል።
ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ቀደም ብሎ በ1949 እንግሊዞች ኦጋዴንን ለቀው ሲወጡ ቦታውን ለመረከብ በቅድሚያ በመመረጡ፥ በ1943 ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ስትወርር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወረራውን የሚመክት ዓለም ዐቀፍ ጦር ሲያሰባስብ በኢትዮጵያ ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ወደዚያ መዝመት የቻለው ክቡር ዘበኛ፥ የምሥረታ ታሪኩ ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በፊት አድርጎ ከነጻነት በኋላ በአዲስ መልክ ተስፋፍቶ ዝነኛና ታዋቂ የሆነበት አንዱ ምክንያት፣ አባላቱ ከዳግማዊ ምኒልክ፣ ከኮከበ ጽባሕ፣ ከተግባረ ዕድ፣ ከተፈሪ መኮንን፣ ከአርበኞች፣ ከአሥፋ ወሰን፣ ከኮተቤ ወንድይራድ፣ ከአሜሪካን ሚሽን፣ ከስዊድን ሚሽን፣ ከንግድ ሥራ፣ ከመድኃኒዓለም፣ ከኮልፌ ካሣ ገብሬ፣ ከጂማ ቀ.ኃ.ሥ፣ ከሐረር ቀ.ኃ.ሥ ትምህርት ቤቶችና ከኤርትራ፣ ከናዝሬት፣ ከግምቢ፣ ከአድዋ፣ ከኢሊባቡር አካባቢዎች የተመለመሉ በመሆናቸውም ጭምር ነበር።
በፍላጎት ብቻ ሳይሆን በግዴታና በአፈሳ መልክ ከየትምህርት ቤቱ ተመልምለን ነበር ወደ ማሠልጠኛው የገባነው የሚሉት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፥ እርሳቸው ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በተመለመሉበት ዘመን በኋለኛው ዘመን ዕውቅ ሰዓሊና ገጣሚ መሆን የቻለው ገብረክርስቶስ ደስታ በተመሳሳይ መልኩ በግዴታ ታፍሶ ወደ ማሠልጠኛው ገብቶ እንደነበርና የወታደርነት ሙያን እንደማይወደው እየነገራቸው በግድ ያመጡት መሆኑን በብስጭት ሲናገር መሥማታቸውን ያስታውሳሉ።
ደራሲው የክቡር ዘበኛ ጦር አካዳሚ ኹለተኛ ኮርስ እጩ ሠልጣኝ በነበሩበት ጊዜ፣ ወደሥራ ዓለም ከተሠማሩ በኋላ፣ ከኮሪያና ኮንጎ ዘመቻ ጋር በተያያዘ፣ በተጨማሪ ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ታሪክን ማዕከል አድርገው በርካታ ልምድና ገጠመኞቻቸውን በ“ተናፋቂ ትዝታችን” መጽሐፍ ውስጥ አኑረዋል። የዐፄ ኃይለሥላሴን ፀባይ፣ ባሕሪይ፣ ተፈጥሮና ብልሕነት ማሳያ የተለያዩ ታሪኮችን አቅርበዋል።
ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ የማኪያቬሊ ፍልስፍና ይከተላሉ፣ በዚህ ምክንያትትም በጦር ሠራዊቱና በክብር ዘበኛ መሐል መቀራረብ እንዳይኖር ማድረግ ችለው ነበር። ይህ ብልሐታቸው የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንዲከሽፍ አስተዋፅዖ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ የሚሉት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፥ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በኋላ የክብር ዘበኛ ሥምና ሥራ ለመደምሰስ ጥረት የተደረገው በዚህ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል ይላሉ። ዐፄ ኃይለሥላሴ ስለ ዓለም አገራትና ሕዝቦች ያላቸው ግንዛቤ ታላቅ እንደነበር፣ ንጉሡ በአንድ አጋጣሚ ከደራሲው ጋር ያደረጉት ጭውውት አመልካች ነው። ዐፄ ኃይለሥላሴና ደራሲው በእቴጌ (አሁን ሐምሌ 19) መናፈሻ ነበር የተገናኙት።
ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡ ፈረሶች፣ ዐፄ ኃይለሥላሴ ወታደራዊ ሕጎችን ለማክበር ያሳዩት ስለነበረው ታዛዥነት፣ የሻምበል አበበ ቢቂላ አሠልጣኝ ነበር ተብሎ በተደጋጋሚ ምስክርነት የሚሰጥለት ሜጀር ኦኒን ኒስካነን የሚነገረውና አበበ ቢቂላን ለውጤታማነት አብቅቶታል የሚባለው ታሪክ ሐሰት ስለመሆኑ እና መሰል ታሪኮች የያዘው “ተናፋቂ ትዝታችን” መጽሐፍ የደራሲውን የደስታ ቀናት በአንድ እንዳሳደገው ሁሉ ለአገር፣ ለሕዝብና ለታሪካችን የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ቀላል አይደለም።
ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛወች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን የመጻሐፍትም ደራሲም ናቸዉ። በኢሜይል አድራሻቸዉ ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011