የታሪክ መማሪያ ሞጁል ወይስ የጥላቻ ማንፌስቶ?!!!!

Views: 327

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለውጥ እየታየባቸው መጡ ከሚባሉ መስኮች ውስጥ ትምህርት አንዱ ነው። ለዚህም የትምህርት ሚኒስቴርን የሥራ ኃላፊነት ከመለየትና ከማካፈል ጀምሮ የትምህርት ስርዓቱን እስከመለወጥ ተደርሷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሚደረጉ ተግባራት መካከል አንዱ መጻሕፍት ላይ የተደረጉ ለውጦች ናቸው። ለታሪክ ትምህርት ይሆናል ተብሎ የወጣውን ሞጁል እንዳነበቡ የሚጠቅሱት መላኩ አዳል፤ ሞጁሉ ላይ የሰፈሩ ታሪክ ነክ ስህተቶችን ነቅሰው ጠቅሰዋል። ከፖለቲካ ታሪክ በተጨማሪ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ታሪክ መካከቱን ቢያደንቁም፣ ሞጁሉ የታሪክን አጻጻፍ ሳይንሳዊ ሂደት ተከትሎ ያልተሠራ፣ በሐሰት ማጠቃለያዎች የተሞላ ድርሰት ሆኖ አግኝቸዋለሁ ሲሉ በሞጁሉ የተካተተ መስተካከል የሚገባው ብዙ ታሪክ፣ አካባቢና ማኅበረሰባዊ ነክ ጉዳይ እንዳለ አሳስበዋል።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አነሳሽነት፣ በአራት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተዘጋጀ የተባለውን ሞጁል አነበብኩት። ስለሞጁሉ ምንም ከማለቴ በፊት ግን ማለት ያለብኝ ነገር አለ። በደረሰኝ ሞጁል የጸሐፊዎቹ ሥም ተሰርዟል። ለዚህም ደስ ብሎኛል። ሐሳቤን የምሰነዝረው በጽሑፉ ብቻ ተመስርቼ ነውና። ይህም እንደ ጸሐፊዎቹ አድሎዋዊ አካሄድ እንዳይኖር ያግዛል ብዬ አምናለሁ። በተጨማሪም፣ ከጸሐፊዎች ውስጥ ማን እንደሆነ ባላውቅም፣ አቅም ያለውና ለራሱ አእምሮ ተጠያቂ የሆነ ሰው እንዳለ መለየት ይቻላል። ነገር ግን የዚህ ሰው ሥራ በሌሎች አስቀያሚ ሥራ ምክንያት ተራ ተብሎ መውደቁ አይቀርም፣ እንስራ ውስጥ ያለ ውሃ ትንሽ እንኳን መርዝ ከተጨመረበት መርዝ ነውና።

ታሪክ ያለፈውን ጊዜ በተደራጀ መልክ የምናጠናበትና ከታሪክም ዛሬያችንና ነጋችንን የምናሳምርበት የተሞክሮ ትምህርት የምናገኝበት የጥናትና ትምህርት መስክ ነው። ታሪክ ምን ድርጊቶች፣ እንዴትና ለምን እንደተፈጸሙ ያጠናል። ታሪክ ዛሬን እንድንረዳ፣ ማንነታችንን እንድናውቅ፣ የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን አመጣጥ ለማወቅ፣ ሐሳብንና ድርጊትን ከጊዜ ጋር አገናኝቶ ለመተንተንና መቻቻልን ለማምጣት ይጠቅማል። ትናንት ዛሬን ባይሆንም፣ በዛሬ ውስጥ ግን ትናንት አለና።

ታሪክ እንደ ታሪክ የሚወሰደው፣ የጽሑፍ ወይም የአርኪኦሎጂ መረጃ ሲኖረው ብቻ ነው። ምክንያቱም ታሪክ ያለ መረጃ አይጻፍምና። ማንኛውም የታሪክ እውነታ በበቂ መረጃ መደገፍ ይኖርበታል። በቂ ያልሆነ መረጃ ከሆነና ተመሳሳይ መረጃዎች ካልተገኙ፣ ያለው መረጃ የሐሰት ሊሆን ስለሚችል ይህን መረጃ እንደ እውነት መጠቀም የታሪክ ባለሙያውን ተወቃሽ ያደርጋል። ይህ ሞጁልም ከመጀመሪያው፣ የታሪኩን ጊዜ ተከትሎና አቃፊና ወካይ እንዲሆን ተደርጎ የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንዱን ታሪክ ለማስተማር የተዘጋጀ ነው ይላል። አፍሪካ ቀንዱን በአንድ ማቅረብም ያስፈለገው፣ ይህ አካባቢ የተሳሰረ የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች የሰፈሩበት ስለሆነ ነው ይለናል። በጠቅላላው ከላይ የተባሉትን መመዘኛዎችና ዓላማዎችን ግን የሚያሟላ ሆኖ አልተጻፈም።

በሞጁሉ ውስጥ የጅቡቲም ሆነ የሶማሊያ ታሪክ በግልጽ አልተጻፈም። ወካይም እንዲሆን ታስቦ ነው የተዘጋጀው የተባለው ስሁት የታሪክ ትርክቶች ለማካተት ስለተፈለገ ለሽፋን ነበር ያሰኛል። ሞጁሉ የታሪክ መማሪያ ሳይሆን ያለፉት 30 ዓመታት የጎሳ ፖለቲካ ማሠልጠኛ ሰነድ፣ ለተወሰነ ቡድን የሥነ ልቦና ግንባታና ሌላውን ለማሸማቀቅ የተጻፈ ይመስላል። እንዲያውም የጽሑፉ ዓላማ ታሪክን በቋንቋ ልዩነት መሰረት በማድረግ፣ የጎሳ ፖለቲካ በአገራችን እንዲሰነብት፣ ብጥብጥ እንዲቀጥል፣ አገር ግንባታ እንዲደናቀፍና የአገር ህልውና ላይም አደጋ እንዲጋረጥ ተልእኮ ያለው ይመስላል። ይህ ‹‹ተቀናቃኝህ በተገኝበት ሁሉ የቤት ሥራ ስጠውሥ› አካሄድ፣ የቤት ሥራው የጋራ እንደሚሆን የረሱም ይመስላል።

ሞጁሉ የተጻፈው በላቲን ወይ በእንግሊዝኛ መሆኑን በእውነት መለየት አይቻልም። ኢትዮጵያ የሚለውን ስም አንዴ Ityopia ሌላ ጊዜ Ethiopia እያሉ ሲጽፉ ይታያል። ታሪካዊ የቦታዎች ሥም ሳይቀር ወደ ኦሮምኛ ተቀይሮና በላቲን ነው የተጻፈው። ለምሳሌ፣ ‹ይፋግ› የተባለውና በደቡብ ጎንደር የሚገኘው ቦታ ‹ይፋጂ ዳሪታ› ተብሎ ነው የተጻፈው። በዛው አካባቢ ላደግኩት እኔ እንኳን ‹‹ይህ ደሞ የትኛው ቦታ ነው?›› አስብሎኛል። የግእዝ ፊደል መጠቀም አቁመው፣ የላቲን ፊደል መጠቀም ይህን የጋራ እሴትን ለማዳበር እንቅፋት እንደሚሆን ከመጀመሪያ ቢነገራቸውም ያለማድመጣቸው ችግር የወለደው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። አሁን ግን በእንግሊዝኛ ይሁን በላቲን መለየት በማያስችል መልኩ የተጻፈ ጽሑፍ ሲያጋጥም ችግሩን የጋራ አድርጎታል። ይህም የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ እጅግ አስፈላጊ የመሆኑ ማሳያ ነው።

ጽሑፉ በአመዛኙ የሶሽዮሎጂ ወይም አንትሮፖሎጂ ጀማሪ ተማሪ የሴሚናር ጽሑፍ ይመስላል፣ ከዚህ የሚለየው ምንም ምንጭ ባለመጠቀሱ ብቻ ነው። የኢኮኖሚ ታሪክ ከንግድና ግብርና ጋር ተገናኝቶ ቀርቧል። የፖለቲካ ታሪኩ ባመዛኙ የክርስትያኑ መንግሥት የሚሉት ስለሆነ ለመወሰን የተቻላቸውን አድርገዋል። ሁኔታው አስገድዷቸው ሲገልጹት ግን ብዙ ስህተት ፈጥረዋል። ይህንንም በተቻለኝ መጠን በሚከተለው መልክ ለማሳያት ሞክሪያለሁ።
ጸሐፊዎቹ፣ አቀራረባቸው ልክ የሴሜቲክ ቋንቋ ተናጋሪ የክሪስቲያን መንግሥቱና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተጻራሪ ሆነው ነው። ለሁሉም የአገራችን ችግሮችም የክርስቲያኑ መንግሥት የሚሉት ተጠያቂ ነው የሚሉ ይመስላሉ።

ለዚህም ማሳያዎችን እንይ። እንደ መሪዎቹ የጥንካሬ መጠን ሲሰፋ ሲጠብ የኖረን አገር እንደ አዲስ ኢንፓየር (ቅኝ ግዛት) አድርገው ጽፈዋል። በዛግዌ ስርዎ መንግሥት ላይ የተጻፈው ዘመን ዝብርቅርቁ የወጣ ነው። የጻፉት የፖለቲካ ታሪክ በክርስቲያኑ መንግሥትና በሌሎች መካከል የተደረገውን መስተጋብር ብቻ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ፍልሰት በሌሎች ላይ ያስከተለው ተጽእኖ አልተዳሰሰም። ተሸነፈ የሚሉትን የኦሮሞ ጦር ጀግንነት ሲጽፉ፣ ግራኝን ከጠንካራ ውጊያ በኋላ ሞተ ሲሉ ይቆዩና አጼ ይስሐቅና አጼ ገለውዲዎስ የአዳል ግዛት በነበሩ ቦታዎች ወድቀው ቀሩ፤ ካሳ ኃይሉን (አጼ ቴዎድሮስን) ያህል ጀግና ንጉሥ ‘the freelance soldier, … in jungle, … became a bandit’ እያሉ ነው የጻፉት።

የምኒልክን ወደ ደቡብ መስፋፋት ምክንያት የክፉ ቀን ድርቅና የወረርሽኝ በሽታን ተከትሎ የመጣ የኢኮኖሚና የንግድ መስመሮችን ለመቆጣጠር ነውም ብለዋል። ብዙዎች የሚስማሙበትን የአባቶቹ የነበረው ግዛት ካልቀደምኩ በነጭ ቀኝ ገዥዎች የመያዙን እውነት ማመኑን በማበል። አርሲ በራስ ዳርጌ በሚመራው የምኒሊክ ጦር መያዝ ምክንያት የባዮሎጂካል መሣሪያ (small pox) መጠቀም ነው ይሉናል። በአኖሌ የሴቶች ጡት ተቆርጧል፣ በወላይታና ከፋ የዘር ማጥፋት ተካሂዷልም ይላሉ።

ክርስትናም ከግብጽ የመጣ ነው ብለው ነው የጻፉት። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አበርክቶዋን የሚክድ ሰነድም ነው። እንዲያውም የኦርቶዶክስ ሃይማሮት መስፋፋት በጉልበት፣ የእስልምና ግን በጂሃድ ሳይሆን በሰላም ነው ይላል። በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ብዙዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑት ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በመጥላት ነው ሲሉ አስፍረዋል። ከሳውዲ የመጡ እስላም ስደተኞችን ተቀብለው ያስተናገዱ ንጉሦችን ወደ እስልምና አማኝነት ተቀይረው ነበርም ይላሉ። ብዙዎቹ ጦርነቶች የሃይማኖት የበላይነትን ለማሳየት የተካሄዱ ናቸው ይሉናል፣ የብዙዎች ጦርነት ምክንያት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዋናው ምክንያት መሆኑንና ሃይማኖት ሽፋን ሆኖ ማገልገሉን ሳይለዩ። የአዳሎችን በቱርክ መረዳትን አሳንሰው፣ የክርስቲያኑን በፖርቱጋል መረዳትን ያጋንናሉ። የግራኝ ጦር ሽምብራ ኩሬ በ1529 እኤአ ላይ ያሸነፈው በጦር አዋቂነቱ እንጂ ከቱርክ መሣሪያ ስላገኘ አይደለም ብለው ሊሞግቱ ይቃጣቸዋል።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገኙ ጽሑፎችን እንደ ታሪክ መረጃ መጠቀም ታማኝነቱ የቀነሰ ነው የሚሉት ጸሐፊዎቹ፣ ከላይ ያለውን የሐሰት ትርክት ሲጽፉ ደካማና የማይባል ቋንቋ ሲጠቀሙ፣ ከላይ ታሪክ ለመጻፍ የሚያበቁትን ግብኣቶች ብለው በዘረዘሩት መመዘኛዎች ሙሉ በሙሉ እንደወደቁ ረስተውታል። በዚህም እጅግ አሳፋሪ ሥራ ሠርተዋል። ጽሑፉ ኢትዮጵያ በጣልያን መገዛቷን (Italian rule) በተከታታይ የሚገልጽና የአባቶቻችንን ትግል ገደል የሚከት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። አንድን ፈረንሳዊ በናዚ ጀርመን ተያዝን (Nazi occupation) እንጂ ተገዛን (Nazi rule) አይልም። የኛዎቹ እነዚህ ጸሐፊዎች ይህን በጣልያን ጦር ተያዝን (Italian occupation) ለማለት ለምን እንዳልፈለጉ ማወቅ ተቸግሪያለሁ።

የመሬት ባለቤትነትን አስመልክተው ሲጽፉ የጣልያን ቀኝ ገዥዎች፣ ከኢትዮጵያውያን ገዥዎች ይሻሉ ነበር ወደሚል ማጠቃለያ ሂደዋል። አሁን ባለው መረጃ፣ የኦሮምኛ ተናጋሪው ብዛት 33.8% ሲሆን የአማርኛ ተናጋሪው ብዛት 29.3% ነው ይሉናል። ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው አማርኛ በኹለተኛ ቋንቋነትም ቢሆን እንደሚናገረው ክደው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው፣ ጸሐፊዎቹ የደመቀውን ታሪክ ለማኮሰስና የጋራ እሴትን ለማዳከም የሄዱበትን እርቀት ነው።

ሙሉ ጽሑፉ የክርስቲያኑ መንግሥት ከሚሉት ውጭ ያለውን የሚያጎላና የኦሮሞን ታሪክና የገዳን ስርአት እስከ 9000 ዓመታት የሚገፋ፣ ምሥራቅ አፍሪካ የኩሽ ነው የሚል፣ እንዲያውም ሴሜቲክ የሆነው ሁሉ ቀይ ባህርን አቋርጦ የመጣ ነው የሚል ጽሑፍ ነው። ኦሮሞው ግን ከየትም አልመጣም፤ የኦሮሞ መስፋፋትም የሚባል ነገር የለም። ምክንያቱም የራሱ የነበረውን ነው የያዘው ይሉሃል።

የመንግሥት ጀማሪው ኩሹ ነው፣ ከዛም ሴሙ ቀጠለ ይሉናልም። ግን ሴም የሚሏቸው ሰዎቹ ናቸው የመጡት ወይስ ባህሉ? ባህሉ ከሆነ፣ የሴም ባህል ተከታዮችን ሥልጣኔው የእናንተ አይደለም ማለት እንዴት ይቻላል? የሰሜቲክ ቋንቋንና ባህልን ከአገሬው ባህል ጋር ተቀላቅሎ መገኘቱስ እንዴት መጤ ለማለት ያበቃል? ይህ ጽሑፍ ኦሮሞው ህንድ ውቅያኖስን ተሻግሮ ከማዳጋስካር ነው የመጣ ከሚለው በምን እንደሚሻል ብትነግሩኝስ? የገዳን ስርአት አቃፊ ሲሉ የሚያቀርቡት ምክንያት በኦሮሞው ውስጥ እኩልነት አለ እንጂ በሌሎች ባህሎች ላይ ያመጣውን ተጽእኖና የባህላቸውን መጥፋት አይደለም። ሞጋሳ የሌላውን ማንነት የሚያከብር ከሆነ፣ አሁን ኦሮሞው በሰፈረባቸው ቦታዎች የነበሩ ሌሎች ጎሳዎች የት ነው ያሉት?

የሰው አመጣጥና ታሪክ በሚቀርብበት ክፍል፣ የዝግመተ ለውጥና የድንጋይ ሥልጣኔ ዘመናትን የገለጹበት መንገድ ያልበሰለና ቆርጦ የመቀጠል እንደሆነ ያስታውቃል። የአረፍተ ነገሮች መደጋገምና የቋንቋው አለመታረም፣ የቆርጦ መቀጠሉ አመላካቾች ናቸው። አንዳንድ አንቀጾች ለታሪክ መማሪያነት የማይጠቅም ሙሉ የታሪክ ሂስ ብቻ የቀረበባቸው ናቸውና ለምን ይህን ማድረግ እንዳስፈለገ ማወቅ ይቸግራል (ገጽ 14-19)።

ከሃይማኖት ጋር የማይገናኝ (secular) የሆነ የትምህርት ስርአት እንዳለን እየታወቀ በዚህ ሞጁል ውስጥ የምናየው ግን ይህን ሂደት የጣሰ ነው። ጽሑፉ ቤተ ክርስትያን ወይም መስጊድ ውስጥ ያለን እንጂ፣ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ላሉ ተማሪዎች የሚሰጥ አይመስልም። ስለ ሃይማኖት ታሪክ ማስተማርም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተመጥኖ፣ በተገቢው መንገድ ብቻ ነው መቅረብ ያለበት። ሌላ ክፍል ደግሞ ጂኦግራፊ ይመስላል፣ እንዲያውም ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ከቱርክ እስከ ሞዛምቢክ ነው ይለናል (ከሶሪያ እስከ ሞዛምቢክ መስሎኝ?፣ ገጽ 20-23)። በሞጁሉ ውስጥ ያሉ ካርታዎች ሚዛናቸውን ያልጠበቁና ታማኝነትም የሌላቸው፣ በግልጽ የማይነበቡም ናቸው። በሚያሳፍር ሁኔታ፣ ኮንሶዎች የእጽዋት ጂን መምረጥ ይችላሉ ብለው ጽፈዋል። ግን ጂን ለእነዚህ ጸሐፍት ምን ይሆን?

ከፖለቲካ ታሪክ በተጨማሪ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ታሪክ እንዲካተት የተሄደበትን መንገድ እደግፋለሁ። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ አለመጠናታቸውና እንደ ድርሰት መካተታቸው፣ ተመርጠውና አስፈላጊነታቸው ታስቦበት አለመሆኑና ሶሽዮሎጂ ወይም አንትሮፖሎጂ ይመስል ማኅበራዊ የሆነው መብዛቱ ትክክል አይደለም። የፖለቲካ ታሪኩም የቀረበው መጠንና የቀረበበት መንገድ እጅግ አሳፋሪ ነው። የሥነ-ሰብእ ትምህርቶች በትምህርት ስርአቱ እንዲገቡ የተፈለገበት ምክንያት የማኅበረሰባችንን መስተጋብር በማሳደግ የተሻለ ማኅበረሰብንና አገርን ለመገንባት እንጂ ልዩነትን ለማስፋት አይደለም። የምንፈልገው፣ ሁላችንም የኛ የምንላት አገር ለመገንባት እንጂ የአንዱን አራክሶ የሌላው የሚያድግበትን ሁኔታ ለመፍጠር አይደለም።

በጠቅላላው ሞጁሉ የታሪክን አጻጻፍ ሳይንሳዊ ሂደት ተከትሎ ያልተሠራ፣ በሐሰት ማጠቃለያዎች የተሞላ ድርሰት ሆኖ ነው ያገኝሁት። በርግጥ ይህ ዶክመንት ከካሪክለም ክለሳ ጥናቱ መጠናቀቅ ከብዙ ጊዜ በፊት በሰዎች እጅ እንደነበር እየተነገረም ነው። የትምህርት ስርአቱ እንዳይተገበር እንቅፋት የሆኑ ፖለቲከኞች እጅ እንዳለበትም እያስተዋልን ነው? ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ጽሑፍ እንዲዘጋጅ በትክክል ሙያተኞችን አወዳድሮ ለምን እንዳልቀጠረ መጠየቅ አለበት። ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ አልተወጣምና። ስለዚህም ሥራው የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ በበቁና ገለልተኛ ሙያተኞች የሚሠራበት መንገድ ይፈጠር፤ በአጭር ጊዜ ተወያይተንበትም ለውጥ የመምጣቱ እድል አነስተኛ ነውና ተተግብሮ የንትርክ መድረክ እንዳይፈጥርም ጥንቃቄ ይደረግ እላለሁ።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com