አቺባደም ሄልዝ ኬር ግሩፕ በኢትዮጵያ ጽ/ቤቱን ከፈተ

0
811

በዓለም ግዙፉ የሆስፒታሎች አገልግሎት ሰንሰለት የቱርኩ አቺባደም ሄሌዝ ኬር ግሩፕ በኢትዮጵያ ተወካይ ጽ/ቤቱን ከፍቷል፡፡

ተቋሙ በ22 የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ከሚሠሩ 36 የጤና አገልግሎት ቢሮዎቹ በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያዊያን ስለ አገልግሎቱ የምክር አገልግሎት የሚያገኙበትን አዲስ ቢሮ ነው በአዲስ አበባ የከፈተው፡፡

አቺባደም ሄልዝ ኬር ግሩፕ በእነዚህ የግንኙነት ጽ/ቤቶች አማካይነት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለኢትዮጵያዊያን ለማቅረብ ማቀዱን የገለፀ ሲሆን፤ በሌሎች ሀገሮች በሚገኙ የመረጃ መስጫ እና ማስተባበሪያ ማዕከሎቹ የሚሰጠውን ተቀራራቢ አገልግሎቶት በኢትዮጵያ ጽ/ቤቱ ባሉ ባለሞያዎች ለመስጠት ዝግጅቱን መጨረሱን አስታውቋል፡፡

ታካሚዎች ከአገራቸው ሳይወጡ በአቺባደም ሆስፒታሎች የሚሰጠውን ተገቢ የምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት አማራጮች በተመለከተ በቢሮዎች በመገኘት ሙሉ መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉም ተብሏል።

የሕክምና ሪፖርቶች እና የላብራቶሪ ምርመራዎች በተመለከተ በቱርክ ከሚመለከታቸው ሆስፒታሎች ጋር መረጃ መለዋወጥ እንዲሁም በአቺባደም ሐኪሞች በተሰጡ ምክሮች መሠረት ታካሚዎች ስለ ሕክምናው ዝርዝር መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ ድርጅቱ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ተቋሙ እንዳስታወቀው ከሆነ ሰዎች ወደ ቱርክ ለሕክምና ሲጓዙ ሂደቱን ማስተባበር እና ከደረሱ በኋላም በኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ እና በሳቢሃ ጎኪን አየር ማረፊያ በሚገኙ ቢሮዎቹ ተወካዮች አቀባበል ተደርጎላቸው ወደ ሆስፒታሎች ይዘዋወራሉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የሕሙማን አገልግሎት ማዕከላት፤ ሕሙማን በምርመራ እና በሕክምና ሂደት ወቅት የጤና አጠባበቅ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላትና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲስተናገዱ፤ በአቺባደም ሆስፒታሎች 22 ቋንቋዎችን ተናጋሪ በሆኑ ከ140 በላይ ተርጓሚዎች የታገዘ አሠራር መዘርጋቱንም ገልጿል፡፡

አቺባደም ሄልዝ ግሩፕ እ.ኤ.አ. በ 1991 እንደ አካባቢያዊ ሆስፒታል ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን በጤና ክብካቤ አገልግሎት ውስጥ በተሳካ ሁኔታ እያደገ ሄዶ አገልግሎቱን አለም አቀፋዊ ለማድረግ የቻለ ግዙፍ ተቋም ነው።

በቱርክ፣ መቄዶንያ፣ ቡልጋሪያ እና ኔዘርላንድስን በመሳሰሉት ሀገሮች በሚገኙ 22 ሆስፒታሎች እና በ18 የሕክምና ማዕከላት በ5 ሀገሮች የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን ይሰጣል

በአሁኑ ጊዜም በሆስፒታሎቹ እና በየሕክምና ማዕከላቱ 3500 ዶክተሮችን እና 4500 ነርሶችን ጨምሮ ወደ 22 ሺህ 500 ሠራተኞች በመያዝ የጤና ክብካቤ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም ታውቋል።
________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here