ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች መካካል የአዲስ ካቢኔ ምስረታውና በዓለ ሲመቱ ጋር ተያይዞ የነበረው ሒደትን የሚስተካከል የለም። ከዓመት በላይ ሲጠበቅ የቆየው ቀን ደርሶ ስያሜና ምልክት ተቀርጾለት ይፋ ቢደረግም፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ ከፈጠረው የመንገድ መዘጋጋትና ጭንቀት በስተቀር ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ይዞ አልመጣም።
ከመስከረም 24ቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት በኋላ ባለ ቀጣይ ቀን ይካሄዳል ተብሎ የነበረውና ለአንድ ቀን የተራዘመው የሚኒስትሮች ሹመት ይበልጥ መነጋገሪያ ሆኗል። ሹመታቸው ከጸደቀላቸው 22 ሚኒስትሮች መካከል ተደርድረው ቃለ መሃላ የፈጸሙት ኹሉም አለመሆናቸው አንዱ ያወያየ ጉዳይ ሲሆን፣ ዋናው ግን እገሌ ይህን ተሾመ፣ እንትና ደግሞ ምንም ሹመት ሳያገኝ ቀረ የሚል ይዘት ያላቸው ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል።
ሕዝብን ‹በጥላቻ ንግግሩ የተሳደበ› እንዴት ተወካይ ሆኖ ምክር ቤት ይገባል ያሉ የመኖራቸውን ያህል፣ ከራሳቸው ከተወካዩ የተደመጠም ስሞታ ነበር። ከተሾሙት መካከል ሌባ አለበት ብለው ማስረጃ ጭምር አለኝ በማለት በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የሚያደርግ አይነት ውንጀላም ያሰሙ ነበር። በአንጻሩ የእሳቸው የቆየ ንግግር እየቀረበ ያለመከሰሰስ መብታቸው ብቻ ሳይሆን አባልነታቸውም እንዲታገድ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ተጀምረውባቸዋል።
በሌላ በኩል፣ እንዲህ አይነት እውቀት እያላቸው ለምን በዚህ ዘርፍ ተሾሙ ተብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ የመለሱትን እየጠቀሱ፣ የሌሎቹን ሹመት ከምላሻቸው ጋር እያነጻጸሩ ለመተቸትና ማብራሪያ ለመጠየቅ የሞከሩም ነበሩ።
ከብልጽግና ፓርቲ ውጭ የተሾሙትን በተመለከተ በሕዝብ ተመርጦ ምክር ቤት የገባ መካተቱን እያመሰገኑ፣ ያላሸነፈ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ በምርጫው ያልተሳተፈ እንዲሾም ተደርጓል እያሉ ቀደም ተብሎ የተነገረ ቃል ታጥፏል ያሉም ተሰምተዋል።
ብዙዎች ሹም ሽሩን በበጎ ቢመለከቱትም፣ ባለውለታ የተባሉት የእንጂነር ስለሺ በቀለ መቅረት አሳዝኗቸው ፎቷቸውን በመለጠፍ ውለታቸውን ለመመለስ የሞከሩ ነበሩ። አንዳንዶች “ፈልገው እንጂ ተገደው አይደለም” በማለት የመቅረታቸውን ምክንያት ለማስተባበል ሲሞክሩላቸው ታይቷል። አንዳንዶች ደግሞ ሕዝብ ስለወደዳቸው ነው፤ ፖለቲከኞች ሕዝብ የወደደውን ማቅረብ ስለማይወዱ ነው በሚል ጥፋቱ የሕዝቡ የራሱ እንደሆነ ለማመላከት የሞከሩም አሉ።
በሌላ በኩል ባለመካተታቸው ቅር የተሰኙ መሆናቸውን የገለጹ አንዳንዶች፣ በቀጣይ ኢትዮጵያን በሚወክሉ ዓለም አቀፍም ሆነ በማናቸውም ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ እሳቸውን ለማየት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በአጠቃላይ “ጦርነት መሀል ላይ ፈረስ አይቀየርም” በሚል የጀመሩትን ተልዕኮ ከግብ ሳያደርሱ ቦታውን በመልቀቃቸው ብዙዎች አዝነዋል።
እሳቸው በበኩላቸው፣ በአዲሱ ሹመት መደሰታቸውን በመግለጽ አጠር ያለ ጽሑፍ በፌስቡክ ገጻቸው ከሰዓታት በኋላ አውጥተዋል። “በቀጣይ አገሬ በምትፈልገኝ አገልግሎት የምሰማራ ይሆናል። ለነበረኝ ትልቅ ኃላፊነትና ለተደረገልኝ ትብብር አመሰግናለሁ” በማለት ሐሳባቸውንም ደምድመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n


