መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየ“አዲስ ምዕራፍ” ጅማሮ

የ“አዲስ ምዕራፍ” ጅማሮ

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው መስከረም 24/2014 አዲስ መንግሥት መመሥረቷን ተከትሎ፣ አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና አዲሱ መንግሥት “አዲስ ምዕራፍ” በሚል መነሻ ሐሳብ ሥራቸውን በይፋ ጀምረዋል። አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን የጀመረው የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ እንዲሁም የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር በመምረጥ ነው።
አዲሱን ምክር ቤት ለሚቀጥሉት አመስት ዓመታት በዋና አፈጉባኤነት እንዲመሩ ታገሰ ጫፎ የተመረጡ ሲሆን፣ በምክትል አፈጉባኤነት ደግሞ ሎሚ በዶ ተመርጠዋል። ምክር ቤቱን አፈጉባኤዎችን መምረጡን ተከትሎ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲሱ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዐቢይ፣ የመንግሥታቸውን ሥራ አስፈጻሚ ካቢኔ አዋቅረዋል። አዲስ የተዋቀረው ካቢኔ 22 አባላት ያሉት ሲሆን፣ በዚህም ሦስት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተካትተዋል። አዲሱ መንግሥት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉባትን ተደራራቢ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።
አዲሱ መንግሥት በፖለቲካው ዘርፍ ለሚታዩት ችግሮች ቀዳሚ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ብሔራዊ መግባባት በቅርቡ እንደሚጀምር የገለጸ ሲሆን፣ በኢኮኖሚው ዘረፍ የሚታየውን የዋጋ ንርት ለማስቀረት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የአዲሱን መንግሥት ምሥረታ እና የካቢኔ ሹመት በቦታው ተገኝቶ በመከታተል የአዲሱን መንግሥት ጅማሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 ባካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፣ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉን ተከትሎ ባሳለፍነው መስከረም 24/2014 አዲስ መንግሥት መሥርቷል። አዲስ የተመሠረተው መንግሥት በምርጫው አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎችን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲያገለግሉ መሰየማቸውን ተከትሎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ እና ምክትል አፈ-ጉባኤ ሰይሟል።

አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ምክር ቤቱን በዋና አፈ-ጉባኤነት እንዲመሩ የመረጣቸው ምክር ቤቱን በዋና አፈ-ጉባኤነት ሲመሩ የነበሩትን ታገሰ ጫፎን ሲሆን፣ በምክትል አፈ-ጉባኤነት የሰየማቸው ደግሞ ሎሚ በዶን ነው።
አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤቱን አፈ-ጉባኤዎችና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በመምረጥ መስከረም 24/2014 ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ክቡር ዐቢይ አሕመድ አሊን (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንዲያገለግሉ በቀጥታ ሰይሟቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሊ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው መጽደቁን ተከትሎ፣ በዕለቱ በመስቀል አደባባይ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት በዓለ ሲመታቸውን አክብረዋል።

በዓለ ሲመታቸውን የአፍሪካ መሪዎች እና የክልል መንግሥታት በተገኙበት ያከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲስ መንግሥት መመሥረቱ ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የመንግሥት አሥተዳደር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ እና ተዓማኒ ምርጫ በማካሄድ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መሥርታለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ችግሮች ቢገጥሟትም ወደፊት ችግሮቿን ፈትታ የማትበገር አገር እንደምትሆን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያን ተስፋ ዕውን ማድረግ የሚቻለው በዜጎቿ ቁርጠኝነትና ቀና ዕሳቤ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል። “ኢትዮጵያ የምትበለጽገው እኛ አገራችንን ለመለወጥ በፈለግንበት መጠን እና የጋራ ራዕይ በሰነቅንበት ልክ ብቻ ነው” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትለው አሁን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን የማሻገር ታላቅ አደራ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በዚህም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉባትን ችግሮች መፍታት እና ለወደፊቱ የማትነቃነቅ አገር የማድረግ እና ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት የዜጎቿ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት አያሌ ውጣ ውረዶችን ተሻግራ አሁን ላይ መድረሷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የማንነት፣ የእኩልነትና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከአርሶ አደር እስከ አርብቶ አደር፣ ከከተማ እስከ ገጠር የዘመናት የሕዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ምንም እንኳን ከእንከኖች የጸዳ እና እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም፣ የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመትከል እና የማጽናት ሕልም ዕውን ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲ ብቻ ወይም የመንግሥት ብቻ አለመሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ድሉ የጋራ እና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነው ብለዋል። በዚህም የተገኘውን ድል በጥንቃቄ መጠቀም ከተቻለ ብዙ የኢትዮጵያ ችግሮችን ማስቀረት የሚያስችል መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዘመናት እየተከማቹ የመጡትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች በአንድ ፓርቲ መፍትሔ አቅራቢነት እና መሪነት ማስቀረት እንደማይቻል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተደራርበው የመጡ ችግሮችን በትብብርና በመተጋገዝ ለመፍታት መዘጋጀት ይገባል ብለዋል። “በእኛ በኩል ከሁሉም ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ሕልም ለስኬት እንዲበቃ አሳታፊ እና አካታች አካሄድ ለመከተል አጥብቀን እንሰራለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት የአሸናፊዎች ፍላጎት ነጸብራቅ ብቻ ሳይሆን፣ የመግባባት ውጤት እንዲሆን መንግሥታቸው እንደሚሠራ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመጭው ዘመን ብዙኃነትን እንደ ጸጋ በመቀበል መታረቅ የሚችሉ ሐሳቦችን በማስታረቅ እና መከበር ያለባቸውን የልዩነት ሐሳቦች በማክበር ወደ ከፍታ የምንጓዝበት ጊዜ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ይህንንም ለማሳካት የፖለቲካ ልዩነትን በማጥበብ አካታች ብሔራዊ የመግባባት መድረክ መንግሥታቸው እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ለችግሮች ከሚነሱ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ በቀዳሚነት ይቀመጣል። ብሔራዊ መግባባት አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ከሚያሳኩ የመፍትሔ ሐሳቦች ቀዳሚ ተደርጎ በዘርፉ ባለሙያዎች በብዛት ይነገራል። አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳመንት ዕትሟ “የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎች” በሚል የዘርፉ ባለሙዎችን አነጋግራ በሠራችው ሐተታ ዘ ማለዳ ላይ፣ የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል የተባለው አገር አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ነው።

አዲሱ መንግሥት ኹሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ እና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለበት ያሉት ባለሙያዎቹ፣ አዲሱ መንግሥት አሁን ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለመቀየር ቅድሚያ የተበላሸውን ፖለቲካ እና ሕገ-መንግሥት ለውጥ ማድረግ አለበት። ይህ ሲደረግ ደግሞ በቅድሚያ ኹሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ውይይት በማካሄድ የዜጎችን ፍላጎት ያማከለ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ሲሉም ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የዜጎችን ደኀንነት ማስጠበቅ እና እንደ አገር ያጋጠመውን ጦርነት ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጠው የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ባለሙያዎቹ፣ ያሉትን ችግሮች ከማስተካከል ጎን ለጎን የፖለቲካ ውይይትና አገራዊ መግባባት በፍጥነት ሊደረግ እንደሚገባ፣ ሁነቱ ለነገ እየተባለ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ በመሆኑ በቅርብ መጀመር እንዳለበት መክረዋል።

አዲስ ማለዳ በአዲስ መንግሥት ምስርታ ዋዜማ ዕትሟ ቀድማ ያነሳችው የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎች ጉዳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበዓለ ሲመታቸው ላይ አንስተዋቸዋል። ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታቂ ችግር አንፃር ብሔራዊ መግባባት እንደ ቀዳሚ ተግባር ይቀመጥ እንጂ፣ ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኹሉም ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መንግሥታቸው ከሕዝብ ጋር ተናቦ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ በቅርቡ እንደሚጀመር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ውይይቱ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ መፍታት ይቻላል ብለው የሚምኑትን የሚያካትት መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ የውይይት ሒደቱ ከላይ ባሉ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ብቻ የተገደበ እንደማይሆን እና እስከ ታች ድረስ ያለውን ማኅበረሰብ ያሳተፈ እና አካታች እንደሚሆን ጠቁመዋል። ውይይቱ በኢትዮጵያ እንደሚመራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለችግሮቻችን አገር በቀል መፍትሔዎችን ለማፈላለግ ታልሞ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ችግሮች መካከል ዋነኛ የሆነውን የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ያነሱ ሲሆን፣ መንግሥታቸው ወዶ ሳይሆን ተገዶ የገባበት ሕልውናን የማስከበር ጦርነት መሆኑን ጠቁመዋል። ጦርነቱ ኢትዮጵያን ቀላል የማይባል መስዋዕትነት ማስከፈሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጦርነቱን ተከትሎ ከውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ ጫና እየደረሰ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር ላይ የሚመጡ የውጭ ኃይሎችን ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከገጠሟት የአገር ውስጥ እና የውጭ የፖለቲካ ችግሮች በተጨማሪ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍም እየተፈተነች እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። በኢኮኖሚው የሚፈትናት ዋነኛ ችግር በየጊዜው ያለማንም ከልካይ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት ሲሆን፣ ይህም ዜጎችን ክፉኛ እያስመረረ ይገኛል። የዋጋ ንረቱ በየወሩ እያሻቀበ ይምጣ እንጂ እስካሁን ሁነኛ መፍትሔ ተገኝቶለት ዕድገቱን ማቆም አልተቻለም። መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

የአዲሱን መንግሥታቸውን የወደፊት ቀዳሚ ተግባራት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዜጎችን በእጅጉ እየፈተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በቁርጠኝነት እንደሚነሱ እና ለውጥ እንደሚያመጡ ጠቁመዋል። የዋጋ ንረቱ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ጫና ውስጥ እንደከተተው መንግሥታቸው እንደሚገነዘበው ያነሱት ዐቢይ፣ መንግሥታቸው በሚቀጥሉት ዓመታት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶች ዜጎችን ከኑሮ ጫና እንደሚያላቅቅ ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም “ጦርነት እና ኢኮኖሚ” በሚል ርዕስ በሠራችው ሐታተ፣ በጦርነት ወቅት የሚኖር ኢኮኖሚ ከወትሮው የተለየ ትኩረትና አካሄድ እንደሚፈልግ ከባለሙያዎች መረዳቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ ትኩሳቶች እየተፈተነች እንደምትገኝ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚታዩ ትኩሳቶች ከፖለቲካ ትኩሳት የመነጩ መሆናቸውን ደግሞ የየዘርፉ ምሁራን በሚሰጧቸው አስተያየቶች ይነሳል። በዋናነት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከሚታዩ የኢኮኖሚ ችግሮች መካከል የተጋነነ የዋጋ ግሽበት፣ በጦርነት የሚባክን ሀብትና የተከሰተ ውድመት፣ እንዲሁም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የማዕቀብና የብድር ክልከላ ዝንባሌዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም አዲሱ መንግሥት፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንዳለበትም ይነገራል።

አላስፈላጊ ወጪ መቀነስ እና የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ራሱን ችሎ እንዲቆም የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት አዲሱን ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት የምክር ቤት ውሏቸው ገልጸዋል።
በተለያዩ አቅጣጫዎች ከፊቱ ተግዳሮት የሚጠብቀውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከችግር ለመታደግ የአገር ውስጥ ገቢን ከማሳደግ ጀምሮ የውጪ ምንዛሬ ወጪን እስከመቀነስ የሚደርስ አሠራር መከተል እንደሚገባ ባለሙያዎች ያነሳሉ። በተለይ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ስልት መከተል ቀዳሚ የኢኮኖሚ ሥራ መሆን እንዳበት የሚገለጽ ሲሆን፣ የውጭ ዕርዳታ ቢቆም ኢትዮጵያ ራሷን ችላ የምትቆምበት የኢኮኖሚ ስልት መከተል የአዲሱ መንግሥት የኢኮኖሚ ዘርፍ የቤት ሥራ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙን ተከትሎ፣ ምክር ቤቱ 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 1ኛ ልዩ ስበሠባውን መስከረም 26/2014 አካሂዷል። ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሠባ የአዲሱን መንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበለትን ረቂቅ ዐዋጅ መርምሮ አጽድቋል። ምክር ቤቱ ያጸደቀው አዲሱ ዐዋጅ “የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ዐዋጅ ቁጥር 1263/2014” ሲሆን፣ በአዲሱ የምክር ቤት አባላት መስከረም 25/2014 በዝግ ተመክሮበታል።

ዐዋጁ በአዲሱ ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት በዋዜማው ምክር ቤቱ ባካሄደው ዝግ ስብሰባ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ በጸደቀበት ዕለትም በምክር ቤቱ አባላት ሠፊ ውይይት ተደርጎበታል። በዐዋጁ ላይ ሠፊ ሐሳብ ከሰነዘሩት የምክር ቤት አባላት መካከል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄው(አብን) ክርስቲያን ታደለ አንዱ ናቸው። የአብኑ ክርስቲያን ታደለ ምክር ቤቱን ከተቀላቁት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ቀደም ሲል ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበሩ ተቋማት በአዲሱ አዋጅ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ተገቢ አለመሆኑን በማንሳት ወደ ምክር ቤቱ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። እንዲሁም አዲሱ መንግሥት የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያጠናክር እራሱን የቻለ ተቋም እንዲያቋቁም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላቱ በሰጡት ምላሽ፣ ከዚህ ቀደም ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑ ተቋማት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ተቋማቱን በቅርበት ለመከታተል እንዲያመች መሆኑን በመግለጽ፣ ወደፊት እንደየአስፈላጊነቱ ተጠሪነታቸውን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመለስ ይቻላል ብለዋል። የተቋማት ተጠሪነት ለክትትል እንዲያመች ታስቦ የተሠራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኹሉንም ተቋማት በበላይነት የሚከታተላቸው ምክር ቤቱ በመሆኑ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በአዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አዋጁ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ካቢኔያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው በኹለት ተቃውሞ፣ በ12 ድምጸ ተዐቅቦ ሹመቱን በአብላጫ ድምጽ አጽድቆላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ያቀረቧቸው ካቢኔዎች 22 ሲሆኑ፣ ደመቀ መኮንን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚኒስትር፣ አህመድ ሽዴ የገንዘብ ሚኒስትር፣ ሙፈሪያት ካሚል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር፣ ዑመር ሁሴን የግበርና ሚኒስትር፣ አይሻ መሐመድ (ኢንጅነር) የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር፣ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢንጅነር) የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የትምህርት ሚኒስትር፣ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር፣ ገብረመስቀል ጫላ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር፣ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ብናልፍ አንዷለም የሠላም ሚኒስትር፣ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የፍትህ ሚኒስትር፣ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር፣ በለጠ ሞላ (ረ/ፕ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝም ሚኒስትር፣ ላቀ አያሌው የገቢዎች ሚኒስትር፣ ጫልቱ ሳኒ የከተማ እና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር፣ ታከለ ዑማ (ኢንጅነር) የማዕድን ሚኒስትር፣ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር፣ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቀጀላ መርዳሳ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት ሌብነትን እና ልመናን የሚጠየፉ፣ ከብሔር ውክልና ወጥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ በእኩልነት እንዲያገለግሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደራ ብለዋል።

በካቢኔ ሹመቱ ሦስት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባሎች የተካተቱ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ብርሃኑ ነጋ(ፕሮፌሰር)፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በለጠ ሞላ(ረ/ፕሮፌሰር) እንዲሁም ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ቀጀላ መርዳሳ ናቸው። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሾሙ ሚኒስትሮች ተቋምን መምራት እና መቃወም ፍጹም የተለያዩ መሆናቸውን ተገንዝብው አገራቸውን እንዲያገለግሉ እና ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ የልምምድ መንገድ እንዲከፍቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች