የኮቪድ-19 ክትባት አንከተብም የሚሉ መምህራን

ወቅቱ አብዛኛው የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች የ2014 ትምህርት የሚጀምሩበት ነው፡፡ መምህራን ለማስተማር በሚመጡበት ወቅት መከተብ እንደሚገባቸው በጤና ሚኒስትር አስገዳጅ ሆኖ መመሪያው እንዲተገበር ተደርጓል፡፡
ይህ አስገዳጅ የኮቪድ-19 ክትባት ለመምህራን የሰራ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ክትባቱን ለመውሰድ በርካታ መምህራን ፍላጎት እንደሌላቸውና የግለሰብ መብታችንን የሚጋፋ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ሕይወት አለሙ (ስማቸው የተቀየረ) ለስድስት ዓመት ያህል በመምህርነት ሙያ ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የአንድ ልጅ እናት ናቸው፡፡ በቅርቡ መምህራን የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከል ክትባት እንዲወስዱ መገዳደቸውን ተከትሎ መከተብ ከማይፈልጉት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸው ያቀረቡ በርካታ መምህራን ውስጥ የሚገኙት ሕይወት፣ ‹ልጄን ስለማጠባ ክትባቱን መውሰድ አልፈልግም፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በርካታ መምህራን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ መምህራን መከተባቸው ግዴታ የሆነበት ምክንያት ብንረዳም መከተብ ሳንፈልግ ተከተቡ የሚል አስገዳጅ ህግ መኖር የለበትም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ክትባቱን የተከተቡ ጓደኞቻችን በኮቪድ መያዛቸውን እያየን ለምን እንከተባለን ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ክትባቱ የሚሰጠው የሰዎችን ያለባቸውን የህመም ሁኔታ ባለገናዘበ መልኩ በመሆኑ የተከተቡ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ አንዳንድ ሰዎች የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲገጥማቸው አይተናል ብለዋል። የኮቪድ-19 ክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶቹ መርፌውን በሚያገኙበት ቦታ ህመም ፣ መቅላት ወይም እብጠት፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ትኩሳት እና ማቅለሽለሽ መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከኹለት ዓመት በፊት አንድ ብሎ በኢትዮጵያ የመግባቱ ነገር የተሰማው ኮቪድ 19 ወረርሺኝ፣ ከ340 ሺሕ በላይ ሰዎችን አዳርሷል። በመካከል ቀንሶ የነበረው የሞት መጠንም አሁን ሦስተኛ በተባለው የወረርሺኙ ማዕበል ከፍተኛ ደረጃ እየደረሰ ሲሆን፣ በትንሽ በትንሹ እየጨመረ እንደ ዋዛ ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወት ለመጥፋቱ መንስኤ ሆኗል።

በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ወረርሽኝ ምላሽ ግብረ-ኃይል አስተባባሪ መብራቱ ማሴቦ እንደሚሉት ከሆነ፣ ክትባቶች በሁሉም የጤና ጣቢያዎች የሚሰጥ ሲሆን የሚከተበው የሰው ብዛት ግን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም ብለዋል። ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡ ጋር ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ያሳያል። ሰው በክትባት መዳን እየቻለ በሚናፈሱ የተሳሳቱ መረጃዎች ውዥንብር ውስጥ በመግባት ክትባትን ፈርቶ አለመከተቡ የቫይረሱን ስርጭት እንዲጨምር አድርጎታል።

የተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ለኮቪድ -19 ክትባት የተለያዩ የመቀበል ደረጃዎች እንዳላቸው ያሳያሉ። ለምሳሌ ፣ በአውስትራሊያ ውስጥ በኮቪድ-19 ክትባት ላይ ለመስጠት ፈቃደኛነት ላይ የተደረገ ጥናት 4.9 በመቶ ክትባቱን እንደማያገኙ እንዲሁም 85 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ክትባቱን ማግኘት እየቻሉ ያልተከተቡ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የክትባት ማመንታት የተለመደ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በተለያዩ ሰዎች እና ማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶችን በመስማት ክትባቱን የመፍራት ሁኔታ እንዲፈጠርባቸው ሆኗል። የክትባት መውሰድ እና መከላከያ መንገዶችን መጠቀም የኮቪድ-19 በቀላሉ የመቀነስ መንገዶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ክትባቱን ለሚወስዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ክትባቱ የመልእክት ልውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ፣ የክትባቱን የመቀበያ እና ግንዛቤ ደረጃ በተወሰነ ደረጃ የተስተካከለ የክትባት ግንኙነት መርሃ ግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው።

ሆኖም ፣ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ለኮቪድ-19 ክትባት እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ማወቅ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ በደንብ ግንዛቤ እየተፈጠረ አይደለም። በክትባቶች ላይ የህዝብ አመኔታን ማጎልበት፣ ተቀባይነት ያለው እና ደህንነቱ የተጠበቀ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመውሰድ አስፈላጊ መነሻ ነው። በዚህ ረገድ በሕዝብ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ክፍተቶችን እና ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር የተዛመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን መለየት እና መፍታት ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ቁልፍ አካል ነው፡፡
ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሁሉ አሁን የኮቪድ -19 ክትባት ለመውሰድ ብቁ ናቸው። ሰዎች በማንኛውም አጋጣሚዎች ክትባቱን በመውሰድ የቅድመ መካላከል አቅምን መገንባት አለባቸው፡፡

በቅርቡ የሚጀመረውን ትምህርት ተከትሎ መምህራን መከተብ ግዴታ እንዳለባቸው መገለጹ ያወሱት መብራቱ፣ በመሆኑም መምህራን በየትኛውም ዓለም የመከተብ ግዴታ አለባቸው ሲሉ ጠቁመዋል። ‹‹ሰዎች መረዳት ያለባቸው ይህ የዴሞክራሲ ወይም የነጻነት መብት ጉዳይ አይደለም። የግለሰብ ነጻነትን መተግበር የሚቻለው ሌሎችን የማይጎዳ ሲሆን ብቻ ነው። ሰዎች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እየላኩ መምህራኖች አንከተብም የሚሉ ከሆነ ሕጻናትን አደጋ ላይ ለመጣል እንደተዘጋጁ ይቆጠራል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

“ሳልከተብ አስተምራለሁ” የሚሉ መምህራን ካሉ፣ ሌሎችን በተለይ ደግሞ ሕጻናትን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ መቀጠል መፈለጋቸው ለሞራላቸው ራሱ ሊከብዳቸው ይገባል ብለዋል። መምህራን ለሌሎች ሞዴል መሆን ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን፣ በጤና ሚኒስትር በኩል ያለው አስገዳጅ ሕግ ከሚተገበሩ መከላከያዎች ጋር እንጂ ከክትባት ጋር በተያያዘ በግድ ተከተቡ የሚል እንዳልሆነም ገልጸዋል።

በድምሩ ግን ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የጥንቃቄ መንገዶችን አለመጠቀሙ በራሱ ወንጀል ነው ብለዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱም፤ ‹‹በግለሰቡ አለመጠንቀቅ ኀብረተሰብ ይጎዳል። የሌላን ሰው ሕይወት የሚጎዳ ነገር ላይ ጥንቃቄ አለማድረግ በየትኛውም አገር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። የኮቪድ ወረርሺኝ ደግሞ ሞት ድረስ የሚያደርስ ነው። ክትባቱ የራሱ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖረውም ለጥቂት ሰዓታት የሚቆይ ነው። ትንሽ ሰዓት ለክትባት መታገስ ባለመቻል እስከ ሞት በሚያደርስ በሽታ መጠቃት የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም›› ሲሉም ዕይታቸውን አካፍለዋል።

ዪኒሴፍ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኮቪድ-19 ክትባት ለመምህራን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል፡፡ በተጨማሪም “የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ በልጆች ትምህርት ላይ ጥፋት አስከትሏል። የመምህራን መከተብ ደግሞ ወረርሺኙ ወደ ተማሪዎች እንዳይተላለፍ የሚረዳ ትክክለኛው እርምጃ ነው ሲል ዩኒሴፍ አስታውቋል።

በፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋት በዓለም ዙሪያ ወደ 90 በመቶ የሚጠጉ ተማሪዎችን ትምህርት አስተጓጉሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቁጥሩ እያሽቆለቆለ ቢሆንም፣ ትምህርት ቤቶች የማህበረሰብ ስርጭት ዋና አንቀሳቃሾች አለመሆናቸው ማስረጃ ቢጨምርም፣ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት የበሽታውን ስርጭት ሊቀንስ ይችላል የሚል ያልተደገፈ አስተሳሰብ አሁንም አለ። በዚህ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች ወረርሺኙን እየጨመሩ በመምጣታቸው ሀገራቶቹ ትምህርት ቤቶችን እንደገና እየዘጉ ነበር። በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት የ320 ሚሊዮን ሕፃናት የመማሪያ ክፍሎች ተዘግተዋል።

ከመምህራን ባሻገር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑት የጤና ተቋማት ሰራተኞች እና ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ክትባት ከወሰዱ በኋላ የኮቪድ -19 ክትባት ለመቀበል ፍቃደኛ የሆኑ መምህራን ቅድሚያ መሰጠት እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ይህ መምህራንን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ፣ በአካል ለማስተማር እና በመጨረሻም ትምህርት ቤቶችን ክፍት ለማድረግ ይረዳል።

የክትባት ምደባን በተመለከተ ውሳኔዎች በመጨረሻ በመንግሥታት ላይ ቢሆኑም ፣ የተራዘመ ወይም የተዳከመ ትምህርት የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ ነው ፣ በተለይም በጣም ለተገለሉ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ሲቀሩ ፣ የመመለሳቸው ዕድላቸው ይቀንሳል፣ እና ወላጆቻቸውም ሥራቸውን መቀጠላቸው በጣም ከባድ ይሆንባቸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here