”እስረኞች ላይ ይሸኑ ነበር” የተባሉት ሴት 12 ክሶች ቀረበባቸው

0
759

የፌደራል ፖሊስ የአገር ውስጥ የጸረ-ሽብር ቡድን መርማሪና ኃላፊ በመሆን አገልግለው የነበሩት እቴነሽ አረፈአይኔ (ሳጅን) ክስ ተመሰረተባቸው።
በሰብኣዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ላለፉት 3 ወራት በእስር ላይ የሚገኙት ተከሳሽዋ ከዚህ ቀደም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ማዕከላዊ) የሚገቡ የአርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግና ሌሎች ድርጅቶች አባላትን ሰብኣዊ መብት በመጣስ የተለያዩ ጉዳቶችን በዋና ወንጀል አድራጊነትና በአባሪነት መፈጸማቸውን ክሱ ይገልጻል።

በፌድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ማክሰኞ፣ ጥር 28 ክስ የተነበበላቸዉ ተከሳሽዋ በተለይም ምርመራ የሚከናወንባቸው የተለያዩ ግለሰቦችን እስኪብርቶ በአፍንጫቸው ውስጥ በመክተት፣ ብልት በፒንሳ በመጎተት፣ ሽንት በመሽናትና በስቴፕለር በመምታት የተለያዩ ዓይነት የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያመላክታል። በተጨማሪም ተጠርጣሪዋ ምንም ዓይነት ሥልጣንና ኃላፊነት ሳይኖራቸው የተለያዩ ተጠርጣሪዎችን በሌሊት ከታሰሩበት በማስወጣት የመብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙባቸው፥ በዚህም ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ክሱ አትቷል። በዚህም የአካል ጉዳት በእስረኛ ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲደርስና የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል ብሏል። ለዚህም ጉዳይ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች ዐቃቤ ሕግ በእያንዳንዱ ክስ ላይ አስገብቷል።

ከዚህም በመነሳት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽዋ ላይ 12 የተለያዩ ክሶችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ አሰምቷል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ተከሳሽዋ ላለፉት 3 ወራት ሕጻን ልጅ ይዘው በእስር መቆየታቸውን ገልጸው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በማረሚያ ቤት መቆየት አዳጋች ስለሚሆንባቸው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

“የጸረ-ሽብር ቡድን ኃላፊ ሆኜ መስራቴን አልክድም ይሁን እንጂ ‘የፖለቲካ አጀንዳ’ ካልሆነ በስተቀር ያደረኩት አንዳች ነገር የለም” ያሉት ተጠርጣሪዋ አሁን በኃላፊነት የሚገኙ ሰዎች ቢጠየቁ ሊናገሩት የሚችሉት ይሄንኑ ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “በምርመራ ቢሮ አንድም ሌሊት አሳልፌ አላውቅም” በማለት የተከራከሩ ሲሆን ሰብኣዊ መብቴን በሚነካ መልኩ ዶክመንተሪ እንዲሰራብኝ ተደርጎብኛልም ብለዋል። አያይዘውም በዋስ ብፈታም ተመልሼ የማልቀርብበት ምንም ምክንያት የለም የሚል መከራከሪያም አቅርበዋል። ከዚህ ቀደም የተከሳሽዋን መዝገብ ሲከታተል የነበረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የዋስ መብት ለተከሳሽዋ ፈቅዶ እንደነበር አይዘነጋም።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በተከሳሽዋ ላይ ከተመሰረቱት 12 ክሶች መካከል አራት የሚሆኑት በከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚያስጠይቁ በመሆኑ የዋስትና መብት ሊሰጣቸው አይገባም በማለት ተከራክሯል። በተጨማሪም ጉዳዩንም ያስረዱልኛል ያላቸውን የተለያዩ የሰነድና የሰው ማስረጃዎች ከክሱ ጋር አያይዞ አቅርቧል። የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱም የተከሳሽዋን የአቆያየት ሁኔታ በሚመለከት ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here