ባንኮች በማኅበራት ለቤት ገንቢ አዲስ አበቤዎች እንዲያበድሩ ሊጠየቁ ነው

0
547

በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ከ960 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ቢኖሩም ግንባታውን በፍላጎቱ ልክ ማከናወን የተሳነው የአዲስ አበባ አስተዳደር ተመዝጋቢዎቹ በቤት ሥራ ማኅበራት እየተደራጁ ቤት እንዲገነቡና ባንኮችም የረጅም ዓመት የገንዘብ ብድር እንዲፈቅዱ የማግባባት ሥራ ሊከውን መሆኑ ተሰማ።

አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ እንደሰማችው በቤት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ቤት ለመገንባት የሚፈልጉ የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋዎች ቁጥር ከፍ እያለ መጥቷል። የከተማ አስተዳደሩ ከመስከረም 2010 ጀምሮ የማኅበራት ቤትን ለመገንባትና በጋራ መኖሪያ ቤት መርሃ ግብር ተመዝግበው ቤት የሚጠባበቁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፈለጉ ከምዝገባው እየወጡ ወደ ቤት ሥራ ማኅበራት እንዲደራጁና ቤታቸውን በራሳቸው እንዲገነቡ እቅድ ይዞ ነበር። ይህንንም ለማስፈጸም የሚያግዝ መመሪያን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ማዘጋጀቱ ይታወቃል። ይሁንና የተባለውን እቅድ በወቅቱ መጀመር አልተቻለም።

በመሀል አሁን ያለውን አዲሱን አስተዳደር ያዋቀረችው ከተማዋ መመሪያው እንደገና እንዲከለስና የፍላጎት ጥናት እንዲካሄድ እያደረገች ነው። ይህም ተግባር እየተጠቃለለ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ከሰባት በላይ የከተማዋ የመንግሥት ተቋማት በጋራ በፈጠሩት ኮሚቴ እየታሰበበት ነው የተባለው አዲሱ የቤት ሥራ ማኅበራት ለቤት ፈላጊዎች የተሻለ ተስፋ ሆኖ እንደሚመጣ ተስፋ ተጥሎበታል።

የማኅበራት መመሪያው ቤት ለመሥራት የሚደራጀው ግለሰብ መጀመሪያ 50 በመቶ መቆጠብ እንደሚገባው አንድ መሥፈርት አድርጎ የሚያስቀምጠው መሆኑ ለቤት ገንቢዎቹ የማይደፈር እንደሆነ ይገለጻል። ይህም ማለት አጠቃላይ የቤት ዋጋው አንድ ሚሊዮን ቢሆን ተደራጅቶ ቤት መሥራት የሚፈልግ ግለሰብ መጀመሪያ 500 ሺሕ ብር እንዲቆጥብ የሚያስገድድ ነው። ይህም ለቤት ፈላጊዎች የሚደፈር ባለመሆኑ እየተጠናቀቀ ያለው ትናትና መመሪያ ሲያልቅ ለከተማዋ ካቢኔ ቀርቦ መላ እንደሚፈለግለት ነው የተነገረው።

የገንዘብ እጥረቱን መላ ለመስጠት ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሰጡ መጠየቅ የተሻለው አማራጭ ሆኖ በጥናቱ መመላከቱን የጠቆሙት ምንጮቻችን ለዚህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር ውይይት እንደሚያደረግ አክለዋል። የገንዘቡ ጉዳይ በዚህ መንገድ ካልተቀረፈ በማኅበራት ተደራጅቶ እስከ አስራዎቹ በሚቆጠር የወለል ከፍታ የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎችን የመገንባት ህልሙ እንደሚያዳግት ተገልጿል።

ስለ ፍላጎት ጥናቱ ውጤት የጠየቅናቸው ምንጮቻችን ከዚህ ቀደም ከጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ወጥተው በማኅበራት በመደራጀት ቤት ለመገንባት ይፈልጉ የነበሩ ነዋሪዎች ቁጥር ከ150 ሺሕ እንደማይዘል ጠቅሰው ለካቢኔው ውይይት ሊቀርብ በዝግጅት ላይ ባለው ጥናት ግኝት ግን ቁጥሩ ወደ 300 ሺሕ ማሻቀቡን ነግረውናል። አስተዳደሩ ለ300 ሺሕ ቤት ገንቢ የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት ካልቻለም የራሱን ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በቅርቡ እንዳሉት ከሆነ ለቤት ልማት የሚውል አንድ ሺሕ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል። ከዚህ በኋላም የአስተዳደሩ ሚና የሚሆነው መሬትን የማቅረብና የመቆጣጠር ሥራ ሲሆን ቤት የመገንባቱን ኃላፊነት ባለሀብቶችና ቤት ፈላጊዎች በቅንጅት እንዲከውኑ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

በ2005 የቤት ፈላጊዎች ዳግም ምዝገባ ወቅት በሦስቱ የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የቤት ልማት መርሃ ግብሮች የተመዘገቡት ነዋሪዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ይጠጋል። ከእነዚህም ውስጥ የ10/90 ተመዝጋቢዎች በአንድ ዙር ሙሉ በሙሉ ቤት የደረሳቸው ሲሆን በ20/80 እስካሁን ቤት ያላገኙት ተመዝጋቢዎች ቁጥር 800 ሺሕ ይጠጋል። በተመሳሳይ ከነበሩት የ40/60 ተመዝጋቢዎች መካከል ቤት የወሰዱት ኹለት ሺሕ 292 ገደማ ሲሆኑ የተቀሩት ተመዝጋዎች ደግሞ 162 ሺሕ ናቸው። ካልደረሳቸው ውስጥ መጠኑ በግልጽ ባይታወቅም ቁጠባቸውን ያቋረጡ ስለመኖራቸው ሲነገር ይሰማል።

በአንጻሩ አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙት የ20/80 እና 40/60 የመኖሪያ ቤቶች 130 ሺሕ ሲሆኑ አስተዳደሩ ከ2009 አካባቢ ጀምሮ የአዳዲስ ግንባታዎችን ጅማሮ አቋርጧል። አስተዳደሩ ለቤት ግንባታ በ2009 በጀት 16 ቢሊዮን፣ በ2010 ደግሞ 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ቢገልጽም አዳዲስ ግንባታዎችን አለመጀመሩና ከተጀመሩ ዓመታት ያስቆጠሩትን ቤቶችም አለማጠናቀቁ እያስወቀሰው ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ እስከ 50 ሺሕ አዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ የመጀመር እንዲሁም ከ40 እስከ 50 ሺሕ ቤቶችን ለተመዝጋቢዎች የማስተላለፍ እቅድ ነበረው። በ2005ቱ ምዝገባም ሁሉም ተመዝጋቢ እስከ 2015 ቤት ይደርሰዋል የሚል ቃል በአስተዳደሩ በኩል ተገብቶ ነበር። አዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን ከጀመረችበት 1997 ጀምሮ እስካሁን ያስተላለፈቻቸው የመኖሪያ ቤቶች ቁጥር 176 ሺሕ ገደማ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here