ሰሞኑን ከወትሮው በተለየ መልኩ ሥራ በዝቶበት የሰነበተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልልቅ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። ውሳኔ ካስተላለፈባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ማክሰኞ፣ ጥር 28 የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባለት ሹመት አንዱ ነው።
እንደሚታወቀው ምክር ቤቱ ከሳምንታት በፊት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጆችን ማፅደቁም ይታወሳል፤ የኮሚሽኖቹ አባላት ሹመት ይህንኑ ተከትሎ የተካሔደ ነው።
በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም መሠረት የሆነው የፌዴራል ስርዓቱን በማጠናከር እየተገነባ የመጣውን የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ብዝኃነት ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙርያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮችን አገራዊ በሆነና በማያዳግም መንገድ መፍታት በማስፈለጉ፣ ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውዝግቦች በሕዝቦች መሃል የቅራኔ ምንጭ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተቋቋመ ኮሚሽን ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ለሆነ አለመረጋጋት መንሥኤ በመሆናቸው፣ ለነዚህ ችግሮች ገለልተኛ በሆነ፣ ከፍተኛ ሞያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ማፈላለግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ አዋጁ መግቢያ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚ አዋጅ ደግሞ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ዕርቅ ማውረድ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በሕገ መንግሥት እንዲሁም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም ዐቀፍና አሕጉራዊ ሥምምነቶች የተረጋገጡትን መሠረታዊ የሰብኣዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እና ተግባራዊ ለማድረግ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ጉልህ የመብት ጥሰቶችን ምንነት በግልጽ መለየት አስፈላጊ ስለሆነ እና ለዕርቀ ሰላሙም አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት መሆኑ ተጽፏል።
የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜዎቸ እና የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብኣዊ መብት ጥሰት እና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት በደል በግልጽ በማውጣት የሚፀፀቱበት እና ይቅርታ የሚጠይቁበት መንገድ በማበጀት እና ዕርቀ ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት እንደሆነም ተገልጿል። ኮሚሽኑ ለማቋቋም በተለይ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ እየፈረሰ የሚሠራ ሳይሆን እየተገነባ የሚሄድ ስርዓት ለመፍጠር፣ ዲሞክራሲያዊ አገርና ማኅበረሰብ ለመገንባት ሰፊና ተቀባይነት ያለው የእውነትና፣ የዕርቅ እና የሰላም ዓላማ ያነገበ፣ ለግጭትና ቁርሾ ምክንያት የሆኑትን ዝንፈቶች ምክንያቶችና የስፋት መጠን አጣርቶ እውነታውን በማውጣት ተመልሰው እንዳይመጡ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን የሚወስድና እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመነጭ ገለልተኛ እና ነጻ ኮሚሽን ማቋቋም በማስፈለጉ መሆኑ በአዋጁ ላይ ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ በመንግሥት ተነሳሽነት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ታደንቃለች። ለመጪው ትውልድ የዴሞክራሲ መሠረትን ለመጣል፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን እንዲሁም ይቅርባይነት ለማስተማር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች መሆናቸውንም ታምናለች።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኹለቱ ኮሚሽኖች አባላት ሆነው የተሾሙት ግለሰቦች የተመረጡት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራን፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከፖለቲከኞች እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሰላምና ዕርቅ ላይ ተሞክሮ ያላቸው መሆናቸው ተመላክቷል። የአባላት ስብጥሩ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በዕድሜ፣ በሥራ ተመክሮ፣ በትምህርት ደረጃ ወዘተ ያማከለ በመሆኑ ለሚሠራው ሥራ ጉልበት ይሰጠዋል፤ አንድ ዓይነት ሐሳቦች ብቻ ሳይሆን ብዝኃ ሐሳቦችም ተካተውበታል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናልች።
በጥላቻ፣ በግጭት፣ በቂም በቀል ወዘተ ለተሞላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፥ ዜጎችን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ስደት፣ የአካል ጉዳት፣ የሥነ ልቦና ቀውስ ሲከፋም ሞትን አስከፍሏል። አዲስ ማለዳ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንም ሆነ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ሥራ እንዲሠሩ መደረጋቸው ከዚህ በፊት ያልተሞከረ በመሆኑ ዕድል ሊያገኝ ይገባል ትላለች። በመሆኑም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የኮሚሽኖቹ ተልዕኮ እንዲሳካ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ስትል አበክራ ትመክራለች።
የኹለቱ ኮሚሽኖች አባላትም የመላ ኢትዮጵያውያንን አደራ እንደተሸከሙ በመቁጠር የአገራችንን ችግሮች በኃላፊነት ስሜት እንዲቀረፍ በማድረግ ሚናቸውን በሐቀኝነትና በአገር ፍቅር ስሜት እንዲወጡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች። ሥራቸውን በኃላፊነትና በብቃት መወጣታቸው የአገር አንድነት ለማስቀጠል እንዲሁም ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ እና አንድነት እንዲነግሥ ለማድረግ አንድምታው ከፍተኛ መሆኑን ታስገነዝባለች።
በመጨረሻም የኮሚሽኖቹ አባላት ሕጋዊ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተገንዝበው በከፍተኛ ወኔ፣ ዕውቀት እና ብቃት በመሥራት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚናፍቀውን ለሁሉም የምትመች ሰላማዊት አገር እንዲኖረን ማድረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011