መንግሥት ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ማንኛውንም አይነት ዕርምጃ ወሰደ ቢባል ላይገርም ይችላል። ሕጋዊ የሆነን የሚጠበቅበትንም ብቻ ሳይሆን፣ እንደነጭ ሽብሩ ዘመን ሊያጠፋው የመጣን፣ ቀይ ሽብር ተብሎ እንደታወጀው ቢያጠፋ ላይገርም ይችላል። “ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረስናቸው” በሚል የመጠፋፋት ቧልትም፣ ሒደቱን ሰብዕና ለመስጠት መሞከር ከተጀመረም በርካታ ዓመታት አልፈዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የመንግሥትም የአገርም ጠባቂ የነበሩ ወታደሮች ላይ ተፈፀመ በተባለ ጭፍጨፋ መንግሥት አጸፋውን ለመመለስ ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። የመንግሥት ታጣቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሕዝብም ከጎን ተሰልፎ አጭር ጊዜ በፈጀ “ሕግ የማስከበር” ነው በተባለለት ወታደራዊ ዕርምጃ ጥቃት አድርሷል የተባለውን አካል ከከተሞች ለማባረር ተችሎ ነበር። “አይመለስም፤ የተበተነ ዱቄት ሁኗል” የተባለው ታጣቂ ቡድን ግን፣ የለውም የተባለን መሣሪያ ተጠቅሞ፣ በፕሮፓጋንዳ መንግሥትን በልጦ መልሶ የተነጠቀውን ጨምሮ የሌሎች ክልሎችን ግዛት ከ8 ወር በኋላ ለመቆጣጠር በቅቷል።
በጊዜ ሒደት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት፣ ሥራዎቹ በመንግሥት ሚዲያ እየቀረበ የሠራውን ግፍ ተመልከቱ እየተባለ ሲነገር ተከርሟል። ቡድኑ በተደጋጋሚ በበቀል ስሜት ሕዝብ መጨፍጨፉን የሚያወግዙት ሚዲያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ባለሥልጣናትና ማኅበረሰብ አንቂዎችም ጭምር ናቸው። ታዲያ ይህ በሆነበት ልክ ከቡድኑ ጋር በማበሩ በተመሳሳይ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ የሚሠራቸው ግፎች፣ በግል ሚዲያው እንጂ በመንግሥት ጣቢያዎችም ሆነ በባለሥልጣናቱ አንደበት እኩል ሲኮነንም ሆነ ሲወገዝ አይሰማም። በዚህ አይነት መንገድ ወንጀለኛን ይቅርና የሚወዱትንም ማበላለጥ ተገቢ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።
“ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ” እየተባለ ለኖረ ማኅበረሰብ አንድ ወንጀለኛ ቡድንን ጭራቅ አድርጎ በመሳል የወጣበት ማኅበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እንደሚሞከረው ሌላውን መተው አያዛልቅም። መንግሥት ውስጥ የሰረጉ አሸባሪ የተባሉት ቡድን አባላት አሉ ብሎ ሕዝቡ እስኪጠረጥር ድረስ፣ አንደኛውን ከስር ከስር ማጋለጡና የሌላኛውን መሸፋፈኑ ሊቆም ይገባል።
በኦሮሚያ ክልል “አንድነትን ያላላል” በሚል ጎጠኛ አስተሳሰብ ወንጀለኛን ሸፍነው ለማቆየት የሚፈልጉ አካላት ነገ በራሳቸው ሲደርስ እስኪያዩት የሚሠሩትን ሥራ አስከፊነት የተረዱት አይመስልም። በቀደመው ዘመን ወደው ሳይሆን በመንግሥት ተገደው ሔደው እንዲሰፍሩ የተደረጉትን ጨምሮ፣ እዛው ተወልደው ያደጉትንና በተለያየ ምክንያት በቦታው የተገኙ የሌላ ብሔር አባላትን በመጨፍጨፍ የመንግሥትን ተቀባይነት ለመቀነስም ሆነ ለመጨመር የሚጥሩ እንዳሉ ይታወቃል።
በየጊዜው እንዲህ አይነት ተግባሮች እየተፈጸመባቸው መውጣትም ሆነ መሸሽ ሳይችሉ በሰቆቃ የሚኖሩ በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መኖራቸውን ከማንም ይልቅ መንግሥት ያውቀዋል። ማንኛውንም ዓይነት ሰቆቃ ሲፈጸም፣ ሕዝቡ ቀናት ካለፉ በኋላ ቢሰማም መንግሥትም ሆነ ካድሬዎቹ ግን ሕብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከተነጋገረበት ብቻ ጉዳዩን በአደባባይ ሲያነሱት ይስተዋላል። ይህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር የክልሉ መንግሥት ስለደረሰው ጉዳትና ስለተጎጂዎቹ ከማብራራት ይልቅ፣ በማስረጃ ተደግፎ የማይታይ ማስተባበያ የመሰለ ማዘናጊያ ዜና ያሰራል። “እርምጃ ተወሰደባቸው” የሚል ይዘት ያለውን ምላሽ የሚሰጡት ባለሥልጣናቱ፣ ድርጊታቸው የበለጠ ሕዝብን ቅሬታ ውስጥ እየከተተ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ትጠቁማለች።
መንግሥት እቆጣጠረዋለሁ ባለው ግዛት ይህን የመሳሰሉ ጭፍጨፋዎች እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ መሥራት ቢጠበቅበትም፣ ትምህርት ቤት አጉረው ከጨፈጨፏቸው ጊዜ አንስቶ ከወሬ የዘለለ ተግባር አለመፈጸሙን ድረሱልን እያሉ በየጊዜው የሚወተውቱት ተጎጂዎች ይናገራሉ። የአሁኖቹን ተጨፍጫፊዎች ለየት የሚያደርጋቸው ድረሱልን ብለው ለጋዜጠኞች በተናገሩ በነጋታው ሊገኙ አለመቻላቸው ነው።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በመንግሥት ሥልጣን የመጡትን እንደማይታገስ ደጋግሞ ያሳየው መንግሥት፣ ወደእሱ ሊመጡበት እንደማይችሉ ካረጋገጠ በኋላ ያሳየውን ቸልተኝነት የሚተቹ በርካቶች ናቸው። በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ ቅስቀሳና እሪታውን ሲያካሂድ የነበረው መንግሥት፣ በርብርብ ወረራው እንዲቆም ከተደረገ ወዲህ ለወራት ዝምታን መርጦ ባለበት ቆይቷል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተወሮ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት ሲማቅቅ መክረሙን የሚያውቀው መንግሥት፣ ሥልጣኔን እስካልደረሱበት በሚል አይነት እሳቤ ጊዜ ሰጥቷቸዋል። የውጭ ኃይሎችን ተቃውሞን ዝም ለማሰኘት በሚል፣ መጠላቱ ላይቀርለት የራሱ ወዳጅ የሆኑ ዜጎቹ እንዲማረሩ ማድረግ አልነበረበትም። አሁንም ጊዜ ስላለ ጭራሹኑ ዝም ከማለት በራሱ ላይ እንደተመጣበት ቆጥሮ የሕዝብን ምሬት ሊያስወግድ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ገለልተኛ ነን የሚሉ የሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተብለው የሚታወቁትም፣ እስካሁን በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ ጥቃቶችንና ጭፍጨፋዎችን እንደሰሜኑ ሊያጣሩና ለሕዝብ ይፋ ሊያደርጉ ይገባል። ምን ያህል ሰው እንደሞተ፣ ምን ያህል ንብረት እንደወደመ፣ ምን ያህል እንደተዘረፉ፣ ምን ያህሉ እንደተሰደዱ፣ እንዲሁም መንግስት የወሰደው ዕርምጃንና ያመጣውን ለውጥ በማስረጃ አስደግፈው ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ በአጽንኦት ማስታወስ ትወዳለች። በሠላም የመኖር መብት ሁላችንም ያለንን ያህል፣ ድረሱልን ስለሚሉ ዜጎቻችን ልንሰላችም ሆነ ልንዘናጋ አይገባም። አንድ ግለሰብም መብት አለው በሚባልበት ዘመን ማኅበረሰቦች የሚደርስላቸው አጥተው ሠርተው መብላት እስኪቸግራቸው ተሳቀው ቀስ በቀስ ማለቅ የለባቸውም። እነሱን መጠበቅ የነበረበት መንግሥት ካልቻለ፣ “አልቻልኩም” ብሎ እንደሰሜኑም ሆነ እንደቤኒሻንጉል ዕገዛ ቢጠይቅ መልካም ነው።
መንግሥት ዋና ሥራው ዜጎቹን ሀብታም ማድረግ ወይም መነገድ ሳይሆን፣ የሕዝቡን ደኅንነት መጠበቅ ነው። ይህን ቀዳሚ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ በዜጎች ዘንድ ተቀባይነቱ ይበልጥ ስለሚቀንስ ሌላውን ኃላፊነቱንም በአግባቡ መወጣት አይችልም። “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አሊያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” እንደሚባለው፣ መንግስት ለሕዝቡ ሲል ብቻ ሳይሆን ለራሱ ሲል ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ፍላጎት ለማስቀደም መሥራት ይጠበቅበታል።
በሰሜኑ ጦርነት እንዳለ ቢታወቅም፣ በደቡብ ምዕራቡ የኦሮሚያ ግዛት አሸባሪ አለ ተብሎ ጦርነትም ሆነ ውጊያ አሊያም ሕግ የማስከበር ዘመቻ በመደበኛነት ስለመኖሩ የሚታወቅም ሆነ የሚሰማ ነገር የለም። ጥቃት ሲደርስ ብቻ አጸፋዊ የሚመስል ዜና ይሰማል እንጂ፣ በዚህ ግንባር ይህ ተደረገ ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም። ቅድሚያ የሚሰጠው የሰሜኑ ነው ከተባለም፣ ሕዝቡ ቁርጡን አውቆት ራሱን እንዲከላከል አሊያም አካባቢውን ለቆ ሠላም እስኪመጣ ሌላ ደኅንነት የሚሰማው ቦታ ቢቆይ መልካም እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ።
በሰሜኑ ክፍልም ሕዝቡ ከመስከረም 24 የመንግሥት ምስረታ በኋላ የማጥቃት ዕርምጃ ይወሰዳል ብሎ እንደወለጋ ነዋሪዎች በተስፋ ቀኑን ሲጠባበቅ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት መከላከሉን ትቶ ወደማጥቃቱ አልተሸጋገረም። ይብሱኑ ተይዞ የማይታወቅ መሬት እየተቀማ ተጨማሪ ሕዝብን ለስቃይ እየዳረገ መሆኑን ብዙዎች በምሬት ይናገራሉ። ጦርነቱ በድጋሚ ተጀምሯል ቢባልም፣ በሌላ ዙር አሻጥር መልሶ እንዲቆም መደረጉን የሚናገሩ አሉ። ይህ አይነት አዝማሚያ የሕዝብን ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን የወታደሩንም ሞራል ሊያላሽቅ ስለሚችል ይታሰብበት ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
የሕልውና ዘመቻ ለተባለው ጦርነት አብዛኛው ሰው በፍላጎት ደሞዙንም ሆነ ሀብቱን እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል። አልፎ አልፎ ግን፣ “ካልሰጣችሁ ከሥራ ትባረራላችሁ” የሚሉ መኖራቸውን ከቅሬታ አቅራቢዎች መረዳት ይቻላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከወደ ደሴ የተሰማው ደግሞ አግራሞትን የሚፈጥር ነው። ነጋዴዎች በተደጋጋሚ እያዋጡ ተፈናቃዮችን ማስተናገዳቸውን ቢናገሩም፣ ለመንግሥት አካላት ለኹለተኛ ዙር ከበፊቱ የበለጠ አዋጡ ተብለው ባለመቻላቸው የንግድ ተቋማቸው እንደታሸገባቸው እየታየ ነው። ይህ አይነት ተግባር በመንግሥት አካሄድ ላይ ሌላ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በፊት ሊታሰብብት ይገባል። “አተርፍ ባይ አጉዳይ” እንዳይሆን፣ መንግሥት ለማን እንደሚዋጋ፣ ሕዝቡም ለማን እንደሚደግፍ ሊያሰላስልና ሊያውቅ ይገባል።
ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014



