ጉዳዩ የሁሉም ነው!

0
668

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ቀጥሎ የማነሳውን ነጥብ እንዳወሳ ምክንያት የሆነኝ ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ ማለዳ 153ኛ እትም ላይ አለቃ ዮሐንስ የተባሉ ሰው ‹የሴት መብት ተከራካሪ ወንዶች› በሚል ርዕስ በዚሁ የሲቄ አምድ ያስነበቡት ጽሑፍ ነው። ጽሑፉ በጥቅሉ የሴቶች መብት ጥያቄ ላይ የወንዶች ተሳትፎን በሚመለከት ያሉ ዕይታዎችን በወፍ በረር የጠቃቀሰ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በበኩሌ ለዚህ ሁሉ ነገር መግቢያና መቅድሙ መሆን አለበት ብዬ የማስበው የሴቶች የእኩልነትና መብት ጥያቄ በምን አውድ ይስተናገዳል የሚለውን ነው። የሴቶች የእኩልነትና የመብት ጥያቄ በተፈጥሮ የተገኙና ሰብአዊ የሆኑ መብቶችን ጭምር የሚያካትት ነው። ታድያ የሰብአዊ መብት ጉዳይ የማን ጉዳይ ነው?

በዚህ መሠረት እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ‹ፌሚኒስት› መሆን ግድ አይደለም፤ ሰው መሆን በቂ ነው። እንደዛው ሁሉ ሴቶች በጠቅላላ ‹ፌሚኒስት› መሆን አለባቸው የሚል አመለካከት የለም፣ መኖርም የለበትም። ስለሴቶች መብትና እኩልነት የታገሉና ውጤትም ያስመዘገቡ በርካታ ሴቶች አሉ። እነዚህ ለብዙዎች አረአያ የሚሆኑ ሴቶች የግድ ‹ፌሚኒስት› ናቸው ማለት ግን አይደለም።

ደግሞ ሁሉንም የማያስማሙ ጉዳዮች ያጋጥማሉ። አሁንም ምሳሌ እንጥቀስ፤ ከአንድና ኹለት ዓመት ገደማ በፊት ‹ወይዘሮ› እና ‹ወይዘሪት› የሚሉ የስም ቅጥያዎች አጠቃቀምን በተመለከተ ሙግቶች ተነስተው ነበር። እዚህ ላይ ጥቂት የማይባሉ የሴቶች መብት አቀንቃኞች ‹ለምን ይሄ ወይዘሮና ወይዘሪት ማዕረግ አይቀርም? ለምን ሴቶች ላይ ጫና ይደረጋል?› ብለው ሲሞግቱ ተሰምቷል።

በአንጻሩ የተወሰኑት በሐሳቡ ሳይስማሙ ቀርተው ‹ደግሞ ምን ችግር አለ? ሲሆን ወንዶችም በዛ መልክ ማዕረግ እንዲኖራቸው ማድረግ ነበር!› ብለዋል። እነዚህ ሰዎች በሐሳቡ አልተስማሙም ማለት የሴቶች ጉዳይ ግድ አይሰጣቸውም ማለት አይደለም።
ልክ እንደዛው ሁሉ ‹ፌሚኒስት› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የማይደግፉት አሉ። እንደውም እሳቤው አውሮፓዊ ነው በሚል ይተቹታል። ነገር ግን በፌሚኒስቶች የሚነሱ ሐሳቦችን በጠቅላላ ያወግዛሉ ማለት አይደለም። የሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በጊዜ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረገው ምክንያትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል።

ብዙ ጊዜ ወንዶች ለሴቶች ጉዳይ እንደ እንግዳ ይታያሉ። አስተያየታቸውም ‹እስቲ እንስማው› ተብሎ እምብዛም መድረክ አያገኝም። ‹በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ምን ብናደርግ መቀነስ እንችላለን?› የሚለው ጉዳይ ላይ የወንድሞቻችን ድምጽ በብዛት አይሰማም።
እንደዛው ሁሉ እንዲህ ባሉ ውይይቶችና ንግግሮች ላይ ሴቶች ጋር ያሉ ችግሮችም ቦታ አይሰጣቸውም። ጥቂት የማይባሉ ሴቶች አጎንብሰው እንዲሄዱ የሚያደርጉ ስርዓቶችን የሚያስቀጥሉት፣ ተንከባክበው የሚያቆዩት ራሳቸው ሴቶች ናቸው።

በድምሩ የሴቶች የእኩልነትና የመብት ትግል ውስጥ ጥያቄ ለማንሳትም ሆነ የመፍትሄ አምጪው አካል ለመሆን ሴት ወይም ወንድ መሆን አይደለም ጉዳዩ። ‹እየሆኑና እየተደረጉ ያሉ ነገሮች ትክክል ናቸው ወይ? እኔ በዛች ሴት ቦታ ብሆን ምን ይሰማኝ ነበር?› ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ነው። አለበለዚያ አለቃ ዮሐንስ በጽሑፋቸው እንደጠቀሱት፣ ‹የወንዶች መብት እየተጣሰ ስለሆነ መብታቸው ይከበር!› የሚል ትግል ከጥቂት ዓመታት በኋላ መነሳቱ አይቀርም።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here