“ወጣቱ የዕርዳታ እህል እየጠበቀ ከተማ መቀመጥ የለበትም”

0
455

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ለብዙ ዓመታት ፖለቲካዊ ትንታኔዎችንና አስተያየቶችን በተለያዩ ሚዲያዎች በመስጠት ይታወቃሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝምና የህግ መምህር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ፣ በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ በብልጽግና ተወክለው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ለመሆን በቅተዋል። ከህወሓት ጋር ሆነው ደርግን ተዋግተው የነበሩት እኚህ የቀድሞ ታጋይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱኑ መልሰው ሲታገሉት ቆይተዋል። የተወለዱበት ራያ ግዛትን በተመለከተ፣ እንዲሁም አጠቃላይ አማራን ወክለው በርካታ ተግባራትን ስለማከናወናቸው የሚነገርላቸው እኚህ የምክር ቤት አባል፣ ስለወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይናገራሉ። የአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ስለወቅቱ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲሁም ስለአጠቃላይ ሒደቱ ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ምን ይመስላል?
ስለአካባቢዎቹ የተሟላ ዝርዝር መረጃ ባይኖረኝም፣ በተለያየ መንገድ ከምሰማውና ከማረጋግጠው በመነሳት፣ ከሞላ ጎደል የሰሜን ወሎ ኹሉም ወረዳዎች በአሸባሪው ቡድን ስለተያዙ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍል በአቅራቢያ ወደሚገኘው የደቡብ ወሎ ዞን ከተሞች ተፈናቅሏል። በተለይ ደሴ፣ ኮምቦልቻና ሐይቅ በርካቶች መጥተው ሰፍረዋል። በምዕራብ አቅጣጫ የተፈናቀሉትም በአቅራቢያው ወደሚገኙት ወገል ጤና እንዲሁም አልፈው ሔደው ደቡብ ጎንደርና ባህር ዳር የተጠለሉ የዋግ ኽምራ የላስታ አካባቢ ተፈናቃዮች አሉ።
የተፈናቃዮች ብዛትም ሆነ የተሠራጩበት ሥፋት ከፍተኛ መሆኑን መመልከት ይቻላል። ከዚህ በባሰ ሁኔታ ሰሞኑንም ወገልጤና ስለተለቀቀ እዛ የነበሩ ተፈናቃዮች ከነነዋሪው የተፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ችግሩ አሁን እየሰፋ መምጣቱን መመልከት ይቻላል። ውጫሌ አካባቢም በትህነግ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በመውደቁ፣ እንዲሁም ከሐይቅ በቅርብ ርቀት ላይ ውጊያዎችም ስለነበሩ ነዋሪው አስጠልሎት ከነበረው ተፈናቃይ ጋር አብሮ ለመፈናቀል ተገዷል።

የተፈናቃዩ ቁጥር እያደር እየጨመረ የችግሩ ውስብስብነትም በዛው ልክ ከፍተኛ ሆኖ እየቀጠለ ነው። ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው። እነዚህን ተፈናቃዮች በመንግሥትም በኩል ይሁን በሌሎች በጎ አድራጎት ተቋማት በኩል የዕለት ምግብ እንዲያገኙ ድጋፍ ለማድረግ ተሞክሯል። ሙከራው ችግሩን የሚመጥንና በዘላቂነት የሚፈታ እንዲሁም በቂና አጥጋቢ ነው ባይባልም፣ ቢያንስ የደሴና የኮምቦልቻ ሕዝብ ወገኖቹ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ እንጀራ መብላት አለባቸው ብሎ ተራ እየገባ በየቀጠናው የተቻለውን አድርጓል።
ችግሩ ሠፊ ከመሆኑ አንፃር ሕብረተሰቡ እርስ በርሱ በመተባበር ለመደጋገፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን፣ አሁንም ጦርነቱ እስከቀጠለ ድረስ የችግሩ ሁኔታ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ እንደማይመጣ ግልፅ ነው።

የተፈናቃዩ ቁጥር ከከተማ ከተማ እየቀጠለ ከመብዛቱ አኳያ፣ ማረፊያ አጣን የሚሉና ዩኒቨርስቲዎች ያስገቡን የሚሉ ስሞታዎች ይቀርባሉ። ከዚህ አኳያ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
ብዙ ሰው መፈናቀሉ የጀመረ የሚመስለው ከቆቦ ነው። ነገር ግን ከዛም በፊት የተፈናቀሉ አሉ። እኔ ያለኝ መረጃ ከኮረም እንደጀመረ ነው። ከመሆኒና ራያ ውስጥ ካለ ባላ ከሚባልም አካባቢ ነበር መፈናቀል የተጀመረው። ቀጥሎ ከአላማጣ ከዚያ በኋላ ነው ከቆቦም ሕዝቡ የተፈናቀለው። እየሸሸ የነበረው ተፈናቃይ ያረፈበት ሲለቀቅ መልሶ እየተፈናቀለ ነው በወልድያ አድርጎ አሁን ደሴና ኮምቦልቻ የደረሰው።

ችግሩ አሁን 3 ወር እያለፈው ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ የመጠለያ ዕጦት የነበራቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ። ትንሽ አቅም የነበራቸው ተከራይተው የሚኖሩበት ሁኔታ ነበረ። አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ትምህርት ቤት ነው ያረፉት። ተቋማቱ ትምህርት መጀመር ስላላባቸው በራሱ የሚፈጥረው ችግር አለ። ትምህርት ቤቶቹ እየተጎዱ መቆየታቸው አይቀርም። ለመማር ማስተማር ሒደቱ ምቹ የማይሆኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ያለው። ምክንያቱም፣ አንድ ግቢ ውስጥ ተፈናቃዮች በብዛት ሲከርሙ የሚበላሹ ነገሮች ይኖራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዩኒቨርስቲውን የመጠቀም ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ተቋማቱ ትምህርት መስጠት አለባቸው። የወልዲያና ሌሎች የተዘጉ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ባሉት ተመድበው ገብተው ሊማሩባቸውም ይገባል። ትምህርት ኹሉም ቦታ ሊቋረጥ አይገባም።
ያሉት ችግሮች ተደራራቢ ናቸው። ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ተማሪም ተፈናቅሏል። እንደአማራጭ ለተፈናቃዮቹ የሚሆኑ ሌሎች መጠለያ ጣቢያዎችን በጊዜያዊነት ማቋቋም ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ መንግሥት ምን እያሰበ እንደሆነ የሚያውቁት የመንግሥት ሰዎች ናቸው። የፌደራሉም ሆነ የክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽኖች፣ ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው።

የምግብ አቅርቦትና የዕርዳታ ድጋፍን በተመለከተ የሚበሉት አጡ የሚል ማስረጃ እስካሁን በእጄ አልደረሰኝም። ወደ አካባቢዎቹ ድጋፍም በማስተባበር በተደጋጋሚ ሔጃለሁ። ሌሎችም ጭምር እርዳታ እንዲወስዱ እያደረግን ነው። ከአልባሳት ጀምሮ የተለያዩ ምግቦችን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። ሰሞኑን ተዘጋ እንጂ በአፋር በኩል ዞብል ድረስ እየተጓዙ ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ። ድጋፉ ለፋኖና ለየአካባቢው ታጣቂዎች ጭምር ሲሆን፣ በተቻለ መጠን ኹሉም እንዲደርሳቸው ጥረት የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም ቢሆን ግን እየተደረገ ያለው በቂ ነው ማለት አይደለም። ዕርዳታው የዕለት ምግብ ላይ ያተኮረ እንጂ ዘላቂ የሆነ ድጋፍ የሚደረግበት አይደለም። በየቤታቸው እያሉ ያገኙት የነበረውንም ማሟላት ባይቻልም፣ በተቻለ አቅም እየተደገፉም ከቁጥራቸው መጨመር አኳያ ገና ብዙ ይቀራል።

ዕርዳታው ተጭኖላቸው ሲሄድ ፍትሃዊ ክፍፍል የማይደረግበት ጊዜ አለ። አንዳንዴ ጎረምሳው ቀድሞ የሚሻማበት ጊዜ አለ። አሮጊቶችና አቅመ-ደካሞች ዕርዳታውን ሳያገኙ የሚቀሩበት ጊዜም እንዳለ ቅሬታዎችን እንሰማለን። እዛ አካባቢ ያለ አስተዳደር ይህንን መለየት መቻል አለበት። በተለይ ወጣቱ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተቀምጦ የአረጋውያንንና የሕፃናትን ዕርዳታ መሻማት የለበትም። ከቻለ ወደ ግንባር ሔዶ በጉልበትም ሆነ በኃሳብ ማገዝ መቻል አለበት። በቋሚነትም ወደ መከላከያም ሆነ ወደ ልዩ ኃይሉ ገብቶ መታገል ይጠበቅበታል። ይህ ባይሆን ጠጋ ብሎ ቁስለኛ ማንሳትን የመሳሰለ ድጋፍ ማድረግ አለበት። ትጥቅና ስንቅ ማቀበል ራሱ ትልቅ ሥራ ነው። አካባቢው ነጻ እንዲወጣ ማገዝ አለበት እንጂ፣ ወጣቱ የዕርዳታ እህል እየጠበቀ ከተማ መቀመጥ የለበትም። በከተሞችም አካባቢ ወጣቱን የተመለከቱ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ስለሚሰሙ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል።

አንዳንዶች፣ የደቡብ ወሎ አስተዳደሪዎች አስፈላጊ ከሆኑ ሥራዎች በስተቀር ኹሉንም ዘግተው ኹሉን ትኩረት ወደ ጦርነቱ ማድረግ አለባቸው፣ የመንግሥት ተቋማትንም ለተፈናቃዮች ክፍት ማድረግ አለባቸው የሚሉ አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
የደቡብ ወሎ አስተዳዳሪዎች ከዋናው ሥራቸው በተጨማሪ ተፈናቃዮችን ማስተናገድ አለባቸው። ነዋሪው የሚመራውና የሚያስተዳድረው ማጣት የለበትም። ኹሉ ነገር ወደጦር ግንባር ይሆናል ማለት አይደለም። የዞኑ አስተዳደር የክተት ዐዋጅ አውጥቷል። ሥራቸው ይህን ማስተባበር ነው። ሌላው የወታደርና የወታደራዊ መኮንኖች ሥራ ነው የሚሆነው። የደቡብ ወሎ አስተዳዳሪ ጦር ግንባር ሔዶ ቢቀመጥ ምን ይሠራል። ያለሥራው ሊሄድ አይገባም። የእሱ ሥራ ከሕዝብ ጋር በተገናኘ ድጋፍ እንዲደረግ መቀስቀስና ማነሳሳት ነው። ስለዚህ ቢሮ ተዘግቶ ወደዛ ስለተሄደ መፍትሔ አይሆንም።
የመንግሥት ቢሮዎችንም ለተፈናቃይ መዋያ እንዲሆኑ ማሰብም በራሱ የተሳሳተ ነው። ምን ያህል ሰው ሊይዙ ነው። የማይሆንን ነገር እንደኃሳብ ማንሳቱ ራሱ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው።

ከሠሞኑ የደሴ ባለሥልጣናት በየመንገዱ ባደረጉት ቅስቀሳ ለሰዓታት የተፈጠረ ሥርዓት አልበኝነት ነበር። ይህን የመሰለ ድርጊት እንዳይደገም ከባለሥልጣናቱ ምን ይጠበቃል ይላሉ?
የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ይመቸዋል እንደሚባለው፣ በእንዲህ አይነት ግርግር ወቅት የትህነግ ሰላዮች ሕብረተሰቡ ውስጥ ይሆኑና ሥራ እንዳይሠራ ሥጋትም እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ሱቆች እንዲዘጉ ወይም እንዲዘረፉ ጭምር ሊሠሩ ይችላሉ። ይህን በየግንባሩ ሲያደርጉት የነበረ ነው። ሠራዊቱ ውስጥም በተለያየ መልኩ ገብተው እንዲበተንና አላግባብ እንዲሸሽ መሳሪያም ጥሎ እንዲወጣ አድርገዋል። ስለዚህ ይህ ሲሆን በየደረጃው ያለ አመራር በቅርበት መከታተልና እውነታውን መገንዘብ አለበት። ጉዳት ሳይደርስ ማክሸፍም ይጠበቅበታል።

ማንም ሰው ከጎኑ ያለውን ማወቅ አለበት። ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት አንድ ሠው ጥሩ ነገር ስላወራ ብቻ ሊታመን አይገባም። ይህ የሚጠበቀው ከአስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ከመላው ሕብረተሰብ ነው። ተናቦ መሥራት ይጠይቃል እንጂ፣ የተለየ ፖሊሲም ሆነ ዐዋጅ የሚጠይቅ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ራሱን ባዳነ ቁጥር አካባቢውንና ማኅበረሰቡን ማዳን ይችላል።

ፌስቡክን በተመለከተ አጠቃቀሙ ላይ ያለ ችግርን አስመልክተው የፃፉትን ተመልክተናል። የማኅበረሰብ አንቂዎች እርስ በርስ ከመከራከር ወጥተው፣ ለምሳሌ ድል ነው ሽንፈት መነገር ያለበት ከሚል አይነት አለመግባበት ተላቀው ለጋራ ዓላማ መቆም ይቻላቸዋል?
የሚያሳዝነው ነገር እሱ ነው። አንዳንዴ ማህበራዊ ሚዲያው ጋር የሚታየው ነገር ያሳዝናል። አንደኛ፣ ድሉን መዘገብ ጠቃሚ ነው። በሌላ በኩል አጋኖ ሕዝብን በሚያታልል መልኩ በማስጮህ መዘገብም ተገቢ አይደለም። ይህ ተራ የፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ሊኖረው ቢችልም፣ ጉዳት ይኖረዋል። የተለቀቀን አካባቢ አልተለቀቀም፣ ያልተለቀቀንም ተለቋል እያሉ ወይም ያልተደመሰሰን ተደምስሷል እያሉ የሚያወሩ ሊያዘናጉና ሕብረተሰቡን ሊያሳስቱ ስለሚችሉ ተገቢ አይደለም። ሚዛንን ጠብቆ በትክክለኛ የተገኘን ድል መዘገብ ጠቃሚ ነው። ሽንፈትም ሊያጋጥም ስለሚችል ያም መዘገብ አለበት።

ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አጋነውም ሆነ በሚያሳጣ መልኩ አሳንሰው ማቅረብ አለባቸው ብዬ አላስብም። ሽንፈትም ቢያጋጥም በልኩ የነበረውን ሁኔታ ሕዝብ ማወቅ አለበት። አንዳንዴ የሚያሳዝን ጽሑፍ እንመለከታለን። ለምሳሌ የማውቀው ለአገር ይቆረቆራል የምለው በሁኔታዎች ተናዶ ይመስለኛል የማይሆን ነገር ጽፎ አይቼ ምላሽ ሰጥቼዋለሁ። “ከዚህ በኋላ የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ያድነናል ብሎ ማሰብ የሚቻልበት ሁኔታ ስለሌለ፣ ዶክተር ደብረ ፂዮንን መማጸን ነው” የሚል ጽሁፍ ነው ያሰፈረው። ይህን ስናይ እግዚአብሔርን መማጸን ተገቢ ቢሆንም፣ እንዲህ ብሎ ስለሰው መጻፉ ግን የሽንፈት ሽንፈት ነው። እየጨፈጨፈ ያለ ቡድን መሪን እንዲህ ማለት የሥነ-ልቦና ችግር መኖሩን ያሳያል። ሌላውን ተስፋ የማስቆረጥ ሚና ስለሚኖረው እንዲህ አይነት አገላለጽ ተገቢ አይደለም።

በተደጋጋሚ “ወሎ ቀብድ ተሰጥታለች፤ ሴራ አለ” እያሉ የሚናገሩ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ የወታደሮች ተግባር በአደባባይ መውጣት የለበትም ብለው፣ ጥፋታቸው ምስጢር መያዝ የለበትም ብለው ከሚሟገቱ ጋር ሲከራከሩ ይሰማል። ይህን እንዴት ያዩታል?
ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ማስረጃው ነው። ተጨባጭ ማስረጃ ያለው ሰው ማውጣት ቢችልም መረጃው የሚወጣበትን ጊዜ፣ ኹኔታና የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። እውነት ቢሆንም ችግር በሚፈጥር ወቅት ማውጣቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ዓላማው መታየት አለበት።
ሠራዊቱ ሕይወቱን እየሰዋ ባለበት ወቅት ችግር ብቻ እያዩ ለመዘገብ መጣደፉ ነው እኛ አገር ያለው ትልቁ ችግር። እንደሚባለው ወሎ ቀብድ ተሠጥታ ሴራ ቢኖርና ጦሩ ዝም ብሎ ቢሸሽ አሁን ምን ይሆን ነበር ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል። በጦርነት ሒደት ውስጥ የአመራር ችግር በተናጥልም ቢሆን ሊኖር እንደሚችል ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ እኔ መጀመሪያው ላይ ስህተት ብዬ የተናገርኩት ነበር። ጦሩ ትግራይን ለቆ የወጣበትን የተቸሁበት ነበር። የተናጥል ተኩስ አቁሙ ተገቢ የነበረ ቢሆንም፣ ሠራዊቱ እንዲለቅ የተደረገበት መንገድ ግን ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። አለቃቀቁ በተጠና መልኩ ሰውም ሆነ መሣሪያ ሳይቀር ነበር መሆን የነበረበት።

ኹለተኛ ሙሉ በሙሉ መለቀቅ ነበረበት ብዬ አላስብም። ማይጨው አምባላጌን በመሳሰሉ ቦታዎች የመንግሥት ኃይሎች መቆየት ነበረባቸው። ወሳኝ የሆኑትን ቁልፍ ቦታዎች እያለፉ መጥተው እዚህ ከመስፈር ይልቅ እዛው መቆየት ነበረባቸው። ይህ ቢያንስ አሁን እንደልባቸው ለመሰባሰብ የቻሉበትን አጋጣሚ ይቀንሰው ነበር። ጦርነቱ እዚህ እንዲሆን መደረጉ ባገኙት አጋሚ እየዘረፉ የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል። የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው ስለመጡ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን እንስሳቱና ሰብሉም ለማጥፋት ደንታቸው አይደለም። በዚህ ጉዳይ የስትራቴጂ ጉድለት የለም ማለት አይቻልም።

እነሱ ገድለው ለመሞት ነው የሚመጡት። “እዚህ ከምትሞት ታሪክ ሰርተህ ሙት” እየተባለ ተቀስቅሶ ነው ወጣቱ በጥላቻ አብዶ የሚላከው። በዚህ በኩል ያለው መደበኛ አገርንና ሕዝብ የመከላከል ዓላማ ነው ያለው። ውስጡ ችግር ያለባቸው እንደሚኖሩ ይጠበቃል። ልምድ የሌላቸውና የሚሸሹ ጭምር ሊያጋጥሙ ይችላሉ። አንዱ ሲበረታ የሌላው መሸሽ ይጠበቃል።

“ወሎን በቀብድ” የሚለው አባባል ግራ ነው የሚገባኝ። አመራሩ ወሎ ላይ ተገቢ ትኩረት አልሰጠም፤ ሕዝቡን አስተባብሮ አካባቢውን ነጻ ማድረግ አልቻለም ብሎ መተቸት ይቻላል። ጉድለት ሊኖር ቢችልም ሆን ተብሎ እንደቀብድ አድርጎ መመልት ግን ተገቢ አይደለም። ደቡብ ጎንደር ለደብረ ታቦር 10 ኪሎሜትር ርቀት እስኪቀር ተይዞ ነበር። ያንን ማስለቀቅ ሲቻል ልምዱን በመውሰድ ሰሜን ወሎ ላይ መድገም ይቻል ነበር። የሰሜን ጎንደር በርካታ ወረዳዎች አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ሥር ናቸው። ስለዚህ የዛ አካባቢ ምን ሊባል ነው። ይህ አይነት የተሳሳተ ስሌት ለማንም አይጠቅምም።

በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መንግሥት መፍረክረክ ይታይበታል የሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ አስፍረዋል። ምንን በተመለከተ ነው?
ወገል ጤና ሲለቀቅ ያን ያህል ጠንከር ያለ ውጊያ ተካሂዶ አይደለም። አስቀድመው የመንግሥት ኃይሎች ወጥተው ነበር። ወዴት ነው ሲባሉ፣ “ወደ ጭፍራ” በማለት በመንግሥት ተሸከርካሪዎች ነው ወጥተው እንዲሄዱ የተደረገው። እነሱ ሲሄዱ የቀረው መመከት ባለመቻሉ የመፍረክረክ ምልክቱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ውጫሌም ላይ በተመሳሳይ አይነት ነው የተለቀቀው። የተወሰነ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ተሰምቶ ነው የተለቀቀው። ከባድ ውጊያ የጠነከረ ተኩስ ተከፍቶ መልቀቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ገና ለገና የተኩስ ብልጫ ስላሳዩ ወይም ተከበብን ተብሎ ሐይቅን አልፎ ደሴ ድረስ የሚሄድ ወታደር ነበር። ከቆቦ እስከመርሳ ድረስም በተመሳሳይ ወታደሩ ተመልሷል። ጦሩ ተደናግጦ ግር ብሎ የሚሸሽበት አጋጣሚ ነበር። “ወዴት ትሄዳላችሁ” ብሎ ማኅበረሰቡ ሊያግዳቸው ሲሞክር፣ “ከፊታችን እንዳታስቆሙን” ብለው የማንገራገርና እንተኩስባችኋለን ብለው የማስፈራራትና ወደሠማይ የመተኮስ ነገር ታይቷል። እነዚህ የመፍረክረክ ምልክቶች ናቸው። እኔ እያነጻጸርኩ ነው የገለጽኩት። የዞብልና የወርቄ አካባቢ ሕዝብ ፊት ለፊት ታግሎ ያሸነፋቸውን እያየን ነው። ከባድ መሣሪያ የሌላቸው ይህን ካደረጉ የተደራጀውና በአግባቡ ሠልጥኖ የታጠቀው ሠራዊት ዝም ብሎ መሸሽ አልነበረበትም።

በተመሳሳይ በአሸባሪነት የተፈረጀውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም ብለው የሚተቹ አሉ። በዚህስ ጉዳይ ምን ይላሉ?
በምስራቅ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸማሉ። በተለይ ሸኔ የተባለው ቡድን እየተጠናከረ ከመጣ ወዲህ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተጠናከረ መልኩ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይገድላሉ፣ ሀብት ንብረታቸውን ይዘርፋሉ። አንዳንዴ ጥቃት የሚደርስባቸው ራሳቸውን መከላከል ሲጀምሩ የመንግሥት ኃይል መጥቶ ለምን እንዲህ አደረጋችሁ ብሎ ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጫና ያሳድራል።

የሰሜኑን ያህል ብዙ ኃይል የማይጠይቅ ቢሆንም፣ ቁርጠኝነትን ግን ይፈልጋል። የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ክልሉ ከ30 ጊዜ በላይ አስመርቋል። በአንድ ዙር እስከ 25 ሺህ አሰልጥኖ ወደ ስምሪት አስገብቷል። ክልሉ ሰፊ ቢሆንም፣ ችግሩ የከፋባቸው አካባቢዎች ላይ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ማሰማራትና ግድያውን ማስቆም ይገባል። በአንድ በኩል የክልሉ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት። የፌደራሉ መንግሥትም እየሰማ እየተመለከተ ዝም ማለት የለበትም።

ማጀቴ ላይ የተሰበሰበ የበርካታ አርሶ አደር እህል መቃጠሉ ተሰምቷል። ይህ ከሆነ በኋላ ጥቃቱ የተፈጸመበት ምክንያትም ሆነ ስለአጥፊዎቹ ማንነት ምንም የተባለ ነገር የለም። ይህ መሆኑ ምንን ያመላክታል ይላሉ?
እንደማንኛውም ሰው መቃጠሉን ነው እንጂ የሰማሁት የተለየ ዝርዝር መረጃ የለኝም። መልዕክቱ ግን በማንኛውም ሁኔታ እንዲህ ማጥቃት እንችላለን የሚል ይመስላል። የአካባቢው አስተዳደር ሕብረተሰቡን አንቅቶ ራሱን እንዲከላከልና ሀብትና ንብረቱን እንደጠብቅ ማድረግ ያስፈልገዋል። ድርጊቱ አካባቢው አሁንም ለጉዳት ተጋላጭ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ማን ድርጊቱን ፈፀመ የሚለውን የማጣራቱ ነገር የሚመለከተው የአካባቢው አስተዳደርም ሆነ የደኅንነት አካል ትኩረት ሠጥቶ ሊሠራ ይገባል። ዛሬ ሰብል አቃጥለው ከሆነ ነገ አንድ መንደር የማያቃጥሉበትና ሕይወት እንዳያጠፉ የሚያግዳቸው ነገር ስለማይኖር ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here