የኢሰመጉ የኹለተኛው ዙር ምርጫ ትዝብት

0
832

የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዋና አስተናባሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ባካሂደበት ጊዜ ተቆርጠው በቀሩ ክልሎች ባለፈው መስከረም 20/2014 ኹለተኛውን ዙር ምርጫ አካሂዶ የምርጫ ውጤቱን ይፋ አድርጓል።
መስከረም 20 በተከናወነው ኹለተኛው ዙር ምርጫ በሱማሌ እና በሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ምርጫ ተካሂዷል። በተጨማሪም በቀኑ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዷል።
ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጀምሮ እስከ ኹለተኛው ዙር ምርጫ ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ታዛቢዎችን አሰማርተው ምርጫውን ከታዘቡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ከቀዳሚዎቹ ይመደባል። ኢሰመጉ በኹለተኛው ዙር ምርጫ፣ ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ታዛቢዎችን አሰማርቶ የታዘበውን መልካም እና ደካማ ጎኖች ቀዳሚ ሪፖርት ባሳለፍነው ረቡዕ ይፋ አድርጓል።

ኢሰመጉ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደረግ መቆየቱን የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በቅድመ ምርጫ፣ በድምጽ መስጫ ዕለትና ድኅረ-ምርጫ ወቅቶች ያለውን አጠቃላይ የምርጫ ሒደት መታዘብ፣ የመራጮች ትምህርት እና በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ክትትል ማድረግ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ሰኔ 14/2013 የተካሄደው ምርጫ በተከናወነባቸው በአብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ከአምስት ሺሕ በላይ ታዛቢዎችን በማሠማራት የምርጫ መታዘብ ግኝቱን የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

መስከረም 20/2014 ምርጫ በተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ኢሰመጉ ከ141 በላይ ታዛቢዎችን አሠማርቶ ሂደቱን መታዘቡን ገልጿል። የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ለመራጮች ክፍት እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በሰኔው ምርጫ ወቅት ጥቂት የማይባሉ የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ ያልተከፈቱ ስለመሆናቸው ኢሰመጉ ቀደም ሲል አውጥቶት በነበረው የመርጫ ትዝብት ግኝት ቀዳሚ ዘገባ ማመላከቱ ይታወሳል። ይሁንና፤ መስከረም 20 ምርጫ ከተደረገባቸውና የኢሰመጉ ታዛቢዎች ከተሰማሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች አብዛኛዎቹ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ ለመራጮች ክፍት ተደርገዋል ተብሏል።
ምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲያከናውኑ የሚጠበቅባቸውን የምጽ መስጫ ቁሳቁች መሟላታቸውን ማረጋገጥ፣ የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ባዶ መሆናቸው ማረጋገጥና በቅርብ ዕይታ እና ግልጥ በሆነ ስፍራ እንዲቀመጡ ማድረግ፣ የድምጽ አሰጣጡ ሒደት ስለመጀመሩ ቃለ ጉባኤ መያዝ፣ የመሳሰሉትን የምርጫ ጣቢያ አከፋፈት ሥነ ስርቶች በአብዛኛው የተከተሉ ስለመሆናቸው የአሰመጉ ታዛቢዎች መታዘባቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የኢሰመጉ የምርጫ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው በአብዛባዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምር ለመራጮች ክፍት የሆኑ ሲሆ፣ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ባሉ ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መጠነኛ አለመግባባቶች ቢያጋጥሙም ወዲያውኑ ተፈትተው ሒደቱ መጠናቀቁን የኢሰመጎ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ስርዓት መጓደሎችን ታዝበዋል።

የኢሰሙጉ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው ችግሮች መካከል በምስጢራዊ ድምጽ መስጫ ቦታዎች አካባቢ ድጋፍ መስጠትና ከምርጫ አስፈጻሚዎች ውጭ ሒደቱን የሚያስተባብሩና ጣልቃ የሚገቡ አካላት ሕገ-ወጥ ተሳትፎ ዋነኛው ነው ተብሏል። በተለይም የኢሰመጉ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው በጅግጅጋ ከተማ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ሕጋዊ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ አካላትና “በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች” በድምጽ መስጫ ጣቢያ ውስጥ መራጮችን ሰልፍ በማስያዝ፣ መራጮችን ተጽዕኖ ውስጥ በሚከት ሁኔታ በምስጢራዊ ድምጽ መስጫ ቦታዎች ላይ በማስተባበር ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ተጠቁሟል።

በድምጽ አሰጣጡ ሒደት ላይ ከታዩ ጉልህ የሕግ ጥሰቶች መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዕድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሱ ሕፃናት በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በምርጫ ሲሳተፉ ተገኝተዋል ተብሏል። ሕፃናቱ ዕድሜያያቸው ለመምረጥ ያልደረሱ መሆናቸውን በቀላሉ በዓይን በማየት ብቻ ግንዛቤ መውሰድ የሚቻል ሲሆን፣ የኢሰመጉ ታዛቢዎች በርከት ያሉ የፎቶግራፍ ማስረጃዎችንም አቅርበዋል።

ሕፃናቱ በምርጫ በሚሳተፉበት ውቅት የምርጫ አስፈጻሚዎቹ የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ማኅተም ያረፈበት የምርጫ ካርድ መያዛቸውን እና ስማቸው በምርጫ መዝገቡ ላይ መኖሩን በማረጋገጥ ድምጥ እንዲሰጡ እንደሚያደርግ ኢሰመጉ መታዘቡን ገልጿል። ይህም ከምርጫ ምዝገባ ሒደት ጀምሮ የተዛባ ሥርዓት ለመኖሩ አመላካች ነው ተብሏል።

በድምጽ ቆጠራ ወቅት ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የኢሰመጉ ታዛቢዎች ሒደቱን እንዳይታዘቡ ከምርጫ ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዲወጡ የማድረግ ሙከራዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ታዛቢዎቹ ሒደቱን እንዲከታተሉ ተደርጓል። የኢሰመጉ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የቆጠራ ሒደቱ ወደ ቀጣዩ ቀን እንዲታላለፉ የተደረጉባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ስለመኖራቸው ሪፖርት አድርገዋል።

በኹለተኛው ዙር ምርጫ ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተለየ ነው ተብሎ የተወሰደው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ድምጽ የሚሰጡበት ምርጫ ጣቢያ መቋቋሙ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ተፈናቃዮች የመምረጥ መብት ቢኖራቸውንም በመጀመሪያው ዙር ከፍተት መፈጠሩ ሲገለጽ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሰኔ ወር ከተደረገው ምርጫ ትምህርት በመውሰድ መስከረም 20 በተከናወነው ምርጫ ላይ የአገር ወስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ባሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ መድረጉን ኢሰመጉ ጠቁሟል።
በሱማሌ ክልል ፋፈን ዞን ደንደማ ወረዳ ስር በሚገኙ ኹለት ኮሌጆች የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በተቋቋሙት 41 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች በኩል 22 ሺሕ 468 መራጮች ድምጽ ለመስጠት የተመመዘገቡ መሆኑ ተመላክቷል።

ኢሰመጉ በመጠለያ ጣቢያዎች ውሰጥ እና በዙሪያቸው በተቋቋሙ 41 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ትዝብት እንዲያከናውኑ አምስት የምርጫ ታዛቢ ቡድን አሰማርቻለሁ ብሏል። በትዝብቱ ወቅት የኢሰመጉ ታዛቢዎች አብዛኛዎቹ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ቦታ ለአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና አቅማቸው ለደከመ ሰዎች ምቹ መሆናቸው ታዝበዋል።

ኮሌጅ ውስጥ የአገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ የተቋቋመው በ2008 መሆኑን የጠቆመው ኢሰመጉ፣ በጣቢያዎቹ የሚገኙ ዜጎች በአብዛኛው በወቅቱ በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሱ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ መሆናቸውን ጠቁሟል። መስከረም 20 በጣቢያዎቹ የተደረገው ምርጫ ለፌደራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሱማሌ ክልል ምክር ቤቶች የተደረገ ሲሆን፣ ይህ መሠረታዊ የሕግ ትርጉም የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን ኢሰመጉ አሳስቧል።

ተፈናቃይ ዜጎች ድምጻቸውን ሊሰጡ የሚገባው አስቀድሞ መኖሪያቸው በነበረው አካባቢ ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ወይስ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ በጊዜያዊነት ተጠልለው በሚገኙበት አካባቢ ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ነው የሚለውን ጉዳይ በቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ ትርጉም ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ኢሰመጉ ጠቁሟል።

ባለፈው መስከረም 20 ድምጽ ከተሰጠባቸው ምርጫዎች መካከል በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የሚገኙ የካፋ፣ ሻካ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በጋራ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ላይ የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ አንዱ ነው። ኢሰመጉ ሕዝበ ውሳኔ በሚደረግባቸው በቦንጋ፣ በሚዛንና በተርጫ ከተሞች ስር በተደራጁ የምራጫ ጣቢያዎች የምርጫ ትዝብት እንዲያከናውኑ 15 ታዛቢዎችን ማሰማራቱን አስታውሷል።

በሕዝበ ውሳኔ አማራጭነት ከቀረቡት ኹለት አማራጭ ሐሳቦች መካከል አምስቱ ዞኖችና ልዩ ወረዳው በደቡብ ክልል ስር መቀጠሉን የሚደግፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የምርጫ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አለመታየቱ ኢሰመጉ መታዘቡን ጠቅሷል። በአንጻሩ አምስቱ ዞኖችና ልዩ ወረዳው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የጎዳና ላይ ቅስቀሳዎችን፣ የተያያዙ እጆችን የያዙ የምርጫ ቅሰቀሳ ባነሮችን፣ በራሪ ወረቀቶችን እና ማስታወቂያዎችን የኢሰመጉ የምርጫ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ታዝበዋል ተብሏል።
የኢሰመጉ ታዛቢዎች ከተሰማሩባቸው ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ አከባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ካፋ ዞን፣ ቦንጋ ከተማ የተሰማሩ ስምንት የኢሰመጉ ታዛቢዎች በድምጽ መስጫው ዕለት የሕዝበ ውሳኔው አስተባባሪ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ ‹‹ፈቃድ አልሰጣችሁም፣ መታዘብ አትችሉም›› በማለታቸው ምክንያት ከቀኑ 6፡00-10፡00 ድረስ የምርጫውን ሒደት መታዘብ አልቻሉም ነው የተባለው።

በሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ዕለት ከተስተዋሉ የሕግ ጥሰቶች መካከል የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመራጮች ገለጻ በሚያደርጉበት ወቅት በጥቂቱ የምርጫ ጣቢያዎች የተያያዙ እጆች ላይ ምልክት አድርገው ሲያሳዩ መታየቱ ዋነኛው የትዝብቱ ግኝት ነው። በምርጫ አስፈጻሚነት የተሰማሩት አብዛኛዎቹ የምርጫ አስፈጻሚዎች የአካባቢው ነዋሪዎች በመሆናቸው የአስፈጻሚዎቹን ገለልተኝነት አጠራጣሪ የሚያደርግ መሆኑን ኢሰመጉ መታዘቡን ጠቁሟል።

ኢሰመጉ ያቀረበው የኹለተኛው ዙር ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ ባልድርሻ አካል ከሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከምርጫ ቦርድ ተወካዮች ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ ወቅት ኢሰመጉ በምርጫ ትዝብት ያገኛቸው ከፍተቶች በባለድርሻ አካላት መታረም እንዳለባቸው ተጠቁሟል። በተለይ አሳሰቢ የሚባሉ ግኝቶችን ላይ ትኩት በማድረግ ለሚቀጥሉት ምርጫዎች ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ በውይይቱ ላይ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here