የኢፌዲሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ወደ አገር ውስጥ በማስገባው ስኳር ላይ የተጣለው የ33 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ እንደገና እንዲታይልኝ ሲል ጥያቄ አቀረበ። ኮርፖሬሽኑ እንደሚለው በአሁኑ ሰዓት የስኳር ፍላጎት በአገሪቱ እየጨመረ እንደሄደና የቅንጦት ዕቃ ስላልሆነ የኤክሳይዝ ታክስ ሊመለከተው አይገባም ሲል ጥያቄውን ለገቢዎች ሚኒስቴር አቅርቧል።
ኤክሳይስ ታክስ በተመረጡ ዕቃዎች ላይ በተለይም የቅንጦት ዕቃ ናቸው ተብለው በሚታሰቡት ላይ የሚጣል ቀጥተኛ ያልሆነ የታክስ ዓይነት ሲሆን፤ በቀጥታ ከተጠቃሚ የሚሰበሰብ ታክስ መሆኑ ቀርቶ የታክስ ባለሥልጣኑ ከአምራቹ ወይም ከጅምላ አከፋፋዩ ላይ የሚጥለው የታክስ ዓይነት ሲሆን፤ ይህም በተዘዋዋሪ አምራቾች በሚጨምሩት ዋጋ አማካኝነት ከተጠቃሚው የሚሰበሰብ ታክስ ማለት ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወንድወሰን ወጋየሁ የቀረበውን የኮርፖሬሽኑን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የገቢዎች ሚኒስቴር የ6 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡት ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሻቸውን ሲሰጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኤክሳይስ ታክሱን በትክክል እየተገበረ እንደሆነና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ መሆኑን ተናግረው ስኳርን ሊያካትት አይገባም ስለተባለው ነገር መስሪያ ቤቱ በጀመረው የሕግ ማሻሻያ ላይ እንደገና እናየዋለን ብለዋል።
ቅሬታውን ለገቢዎች ሚኒስቴር ያሰማው ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ 200 ሺሕ ቶን ስኳር ለፋብሪካዎችና ለተጠቃሚዎች በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ሊገዛ እንደሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም የሚስተዋልበት የስኳር ጉዳይ መንግሥት ከ1985 ጀምሮ በውጭ ምንዛሪ ገዝቶ በማምጣት ቢያከፋፍልም የታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ የታወቀ ሲሆን። በአሁኑ ጊዜ እስከ 350 ሺሕ ኩንታል ስኳር በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል። በአገር ውስጥ ካሉት 4 የስኳር ፋብሪካዎችም ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በዓመት የሚመረት ሲሆን ይህም በአገሪቱ ያለውን የስኳር ፍላጎት ግማሽ ያህሉን ማዳረስ እንደማይችል ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የኮርፖሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ጋሻው አይችሉህም የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማርካት ከውጭ አገር በሚገዛ ስኳር ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ የኤክሳይስ ታክስ ተግባራዊ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በመጨረሻም የገቢዎች ሚኒስቴር የግማሽ ዓመት ሪፖርት ለምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት ለመረዳት እንደተቻለው ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች የተጣራ ትርፍ በጥቅል 122 ነጥን 18 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 98.96 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይህ አፈፃፀም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወይም 8 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011