በነሐሴ 2010 ተቋርጦ የነበረው 30ኛው ዙር የአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታን ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ንጉስ ተሾመ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት አሁን ላይ ከመንፈቅ በላይ ተቋርጦ የቆየውን የከተማ መሬት ሊዝ ጨረታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው።
በሐምሌ መጨረሻ ሳምንት በጋዜጣ ወጥቶ የነበረውና ለንግድ፣ ለመኖሪያ ቤትና ለቅይጥ አገልግሎት ግንባታ የሚውሉ የ100 ቦታዎች ጨረታ እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል። የከተማው ካቢኔ ጨረታው እንደሰረዝ የወሰነው ከዚህ ቀደም በጨረታ የተላለፉ ቦታዎች ስለመልማታቸው ለማጣራት፣ ያለሙትን ምን ቢሆኑ ይሻላል የሚለው ላይ መፍትሔ ለመፈለግና በቀጣይ የሚተላፉት በምን አግባብ ይሁን የሚለው ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ ንጉስ ተናግረዋል።
ለጨረታ የወጡት ቦታዎች ሰነድ ለኹለት ቀናት ከተሸጠ በኋላ በአስተዳደሩ ትዕዛዝ እንዲሰረዝ የሆነውን 30ኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ተከትሎ የማጥራት ሥራዎች ሲሰሩ መከረሙን ያነሱት ንጉስ በተፈለገው መንገድ እየለሙ ያሉና በአልሚዎች ተደጋጋሚ የውል ማራዘሚያ ጥያቄ ጦማቸውን ሲያድሩ የኖሩ ቦታዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይም የተቋረጠውን የሊዝ ጨረታ ማስጀምር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከወኑ በመሆኑ ካቢኔው እንደወሰነ ጨረታው ‹‹ሩቅ በማይባል ጊዜ ይወጣል›› ብለዋል። እስካሁን ይኼ ነው ተብሎ የተቆረጠ ቀን እንደሌለም አክለዋል። ይሁንና ኅብረተሰቡ ጨረታው እንዲወጣ በተደጋጋሚ እየጠየቀ እንዳሚገኝ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስተዳደሩም ቢሆን ፍላጎቱ እንዳለው አክለዋል።
ለረጅም ዓመታት ሳይለሙ ኖረዋል በሚል በምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ ካደረጋቸው ሰፋፊ ቦታዎች ውስጥ በሊዝ ለጨረታ የሚቀርቡ እንደሚኖሩም ንጉስ ጠቁመዋል። ይሁንና አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በጨረታ ይወጣሉም አይወጡምም ለማለት እንደማያስደፍር በማከል ከተወረሱት ቦታዎች መካከል ማኅበራዊ ፋይዳና ሁለንተናዊ ጥቅማቸው ታሳቢ እየተደረገ በምደባ እንዲለሙ እንደሚደረግ አክለዋል።
አዲስ ማለዳ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሰማችው በተወረሱት ቦታዎቸ ላይ ይተገበራሉ የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሰሞኑን ይፋ ይደረጋሉ።
ከኹለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ በነበረ የመሬት ሊዝ ጨረታ ለአንድ ካሬ 350 ሺሕ ብር መቅረቡና አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ስላለው የመሬት ሊዝ ጨረታ ዋጋ መናርና የመንግሥት አቅጣጫ ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹መንግሥት ጥቂት ቦታዎችን ለጨረታ እያቀረበ ሕዝቡ እንዲራኮት እንደማይፈልግና በሊዝ የሚወጡ ቦታዎችን ሰብሰብ አድርጎ በብዛት እያወጡ ዋጋውን ማረጋጋት›› እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር። አክለውም በአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ላይ ደላሎች እየተሳተፉ ዋጋውን ከፍ በማድረግ ማሸነፍና የተጫረቱበትን ከፍተኛ ዋጋ ሳይከፍሉ በመቆየት ምናልባት የመንግሥት ለውጥ ከመጣ በሽግግር ጊዜ አጭበርብሮ ለመጠቀም በሚል የሚያስቡም እንዳሉ አስረድተው ነበር።
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011