የጦርነቱ የአንድ ዓመት ጉዞ

0
1156

በህወሓት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከቃላት ጦርነት ወደ ጦር መመዛዝ ከተቀየረ በሚቀጥለው ረቡዕ አንደኛ ዓመቱን ያስቆጥራል፡፡ በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ወደ ጦርነት የተቀየረው ጥቅምት 24/2013 ሲሆን፣ የተራዘመ ጦርነት ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት ከትግራይ ክልል አሁን እስከተስፋፋባቸው አማራ እና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ የሞት፣ የርሀብ እና የመፈናቀል ሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ እስካሁን በአማራ እና በአፋር ክልል ብቻ ከ900 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ጦርነቱ የተስፋፋባባቸው አካባቢዎች ሳይፈናቀሉ የሚገኙ ዜጎች በተለይ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ኽምራ ዞን፣ በሰሜን ጎንደር እና በሌሎችም አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አለመቻሉን የአማራ ክልል መንግሥት ገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ መነሻውን የደረገው ጦርነት ለስምን ወራት በትግራይ ተገድቦ ቢቆይም መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሰኔ 21/2013 ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ፣ ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ጦርነቱ የተራዘመ መሆኑን ወታደራዊ ባለሙዎች ይገልጻሉ፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ጦርነት የአንድ ዓመት ጉዞ እና የጦርነቱ መነሻ ወደ ኋላ ተመልሶ ያሉትን ሁኔታዎች በማስታወስ እና ወታደራዊ ባለሙያ በማነጋገር ሁነቱን የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 2010 ጀምሮ መንግሥታቸውን በአዲስ አደረጃጀት መተካታቸውን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) እና በፌደራል መንግሥት መካከል ልዩነት መፈጠሩ የሚታወስ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አሠራር፣ ኢትዮጵያን በበላይነት ለ27 ዓመት በመራው ህወሓት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣ ቅሬታ መፍጠሩን ተከትሎ፣ በፌደራል መንግሥት እና በወቅቱ የትግራይ ክልል መንግሥት በነበረው በህወሓት መካከል ልዩነቱ በግልጽ ጎልቶ ወደ ጦርነት ከተቀየረ አንድ ዓመት ሊሞላው ሦስት ቀናት ቀርተውታል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት በልዩነት ጎዳና ማቅናት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ልዩነታቸው ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣቱ በቃላት ጦርነት ተወስኖ የነበረው መቃቃር ጥቅምት 24/2013 ወደ ጦር መማዘዝ ተሸጋግሯል። በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከቃላት ጦርነት ወደ ጦር መማዘዝ ማምራቱን ተከትሎ፣ በየጊዜው የሚቀያየሩ ክስተቶች ታይተዋል።

የህወሓት እና የፌደራል መንግሥት የቃላት ጦርነት ወደ ኃይል ጦርነት የተቀየረው፣ ህወሓት መቀመጫውን በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ባደረገው የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር። የህወሓትን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት የተለያዩ ኹነቶችን እያስተናገደ ቆይቷል። በጦርነቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተስተናገዱ ኹነቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት ተገድቦ የነበረው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልል መስፋፋቱ ነው።
ቅድመ ጦርነት

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገ የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ ክስተት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን መምጣት ከጅምሩ የተቀበለዉ ቢመስልም፣ የኋላኋላ ግን እያፈገፈገ መጣ። ቡድኑን እንዲያፈገፍግ ካደረጉት መነሻዎች አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥተዳደር ከተለመደዉ የተለየ አካሄድ መከተሉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በፈጠሩት አዲስ የመነቃቃት ወኔ፣ መላዉ አገሪቷን እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩና አዲስ መንገድ እያስተዋወቁ በነበረበት ጊዜ መቀሌ ላይ ጥሩ የሚባል አቀባበል አግኝተዉ ነበር። ይሁን እንጅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የሚያደርጋቸዉ የተቋማትና የአመራር ለዉጦች በህወሓት በኩል ቅሬታን የፈጠሩ ነበሩ።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተፈጠረዉ የፖለቲካና አስተዳደር ልዩነት ከመሰረቱ ጀምሮ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ መጣ። በኹለቱ ኃይሎች መካከል የታየዉ የልዮነት ጎራ ጉልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ ኹነቶችም ተከሰቱ።
የህወሓት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በልዩነት እየተጓተቱ የመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ ካደረጉ ዋና ዋና ክስተቶች አንዱ፣ ትግራይ ዉስጥ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ማዕከል እንዲንቀሳቀስ የፌደራል መንግሥቱ ፍላጓት ቢኖርም፣ በክልሉ መንግሥት በኩል ጦሩ ከትግራይ እንዳይወጣ ክልከላ ተደርጎበት ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ከነበረባቸው ከተሞች አንዳያልፍ ሲታገድ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

አዲሱ አስተዳደር ተቋማት ላይ የሚያደርገዉ ለዉጥም ህወሓትን ያስኮረፈ ነበር። በተለይ የቀድሞዉ ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ አመራሮች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ መያዛቸዉ፣ ቡድኑ “በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ዉንጀላ ነዉ” በማለት የልዩነት ጎራውን አሰፋው።

የልዩነት ጉራዉ እያደገ በመጣበት ሁኔታ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥተዳደር የኢትዮጽያን ፖለቲካ በቀዳሚነት የሚዘዉሩትን ድርጅቶች አክስሞ ወደ አንድ ለማምጣት ዉጥን በያዘበት ጊዜ ህወሓት ዉህደቱን አልተቀበለም ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ውህድ ፓርቲ የመመስረት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ። ኢህአዴግን ከመሠረቱት እና የአድራጊ ፈጣሪነት ሚናውን ከፊት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሲዘውር የቆየው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ብልጽግና የተባለውን ውህድ ፓርቲ ሳይቀላቀል ቀረ። ከውህድ ፓርቲነት እራሱን ያገለለው ፓርቲ ተቃዋሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ።

ኹለቱ ኃይሎች ወደ አልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ካደረጋቸው ዋና ምክንያቶች አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መክሰም እና የብልጽግና ፓርቲ ውልደት ይገኝበታል።
ኢሕአዴግን አክስሞ አዲስ ፓርቲ መመስረቱ ለሦስቱ ነባር አውራ ፓርቲዎች ማለትም ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ)፣ ለኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) እና ሌሎች ከዛ በፊት አጋር ተብለው አብረው ለሚሠሩ ድርጅቶች ቀላል ቢሆንም፣ በህወሓት በኩል ግን ተቀባይነት አላገኘም።

የኢሕአዴግ ክስመት እና የብልጽግና ውልደት ህወሓትን ከቀደሙት ጊዜያት በላይ ወደ መቀሌ እንዲከትም እና የተናጠል ሐሳብ እንዲያራምድ እንዳደረገው ይታመናል። ለዚህም እንደማሳያነት ኅዳር 11/2012 ከህወሓት ውጪ በተደረገ የያኔው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክር ቤቱ ውህደቱን በሙሉ ድምፅ ያጸደቀ ሲሆን፣ ኅዳር 21 ውህደቱን የተቀበሉት ፓርቲዎች ተፈራርመው ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ። ኅዳር 24 ፓርቲው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ አቅርቦ ቦርዱ ታኅሳስ 15/2012 ለብልጽግና ፓርቲ ዕውቅና መሰጠቱ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ የቀድሞዋ የፌድሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሒም ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው መቀሌ መግባታቸውን ሰኔ 2012 መቀሌ ሆነው በሰጡት መግለጫ ማብሰራቸው የሚታወስ ነው። የኬሪያ ከአፈ-ጉባኤነት ለቀው ወደ መቀሌ መሔድ እና ህወሓት ፌዴራል ላይ የሚገኙ አባሎቹን ሥራ ለቀው ወደ መቀሌ እንዲመጡ መጠየቁ የቡድኑን ወደ መቀሌ የማቅናት ጉዳይ ያጠናከረ ነበር።

ኬሪያ በወቅቱ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ አንደማይችል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ፣ ምርጫውን ለማራዘም በወቅቱ የተቀመጠውን አማራጭ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ይሰጥ ውሳኔ እና ትርጉም ለመሥጠት እየተሄደበት ያለውን መንገድ ባለመደገፋቸው መሆኑን አብራርተው ነበር።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የህወሓት እና የፌዴራል መንግሥቱ ልዩነት ከነበረበት ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ይሄውም ዓለምን ያሸበረው ኮቪድ-19 ሲሆን፣ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ነበር። በዚህም በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጠየቁን ተከትሎ ነበር ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው።

የሕገ-መንግሥት ትርጉምን እና ምርጫ መራዘምን በወቅቱ አምርሮ የተቃወመው ህወሓት፣ የራሱን ክልላዊ የተናጠል አካሄድ መከተል ጀምሮ ነበር። በዚህም ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ኮቪድ-19 እያለም ቢሆን በመደበኛ ጊዜው በክልል ደረጃ አካሂዳለሁ በማለት የክልሉን ምርጫ አስፈጻሚ አዋቅሮ ዝግጅት ጀመረ።

እንዲህ በእንዲህ እያለ የልዩነት ደረጃው እያደገና በሐሳብ ልዩነት ላይ የተመሠረተው ፍትጊያ ወደ ተግባር መቀየር ጀመረ። ህወሓት በፌደራሉ መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው የተባለውን ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 በይፋ በማካሄድ ማሽነፉን አበሰረ። አሸነፍኩ ማለቱን ተከትሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልል መንግሥት ሆኖ እንደሚቆይ በይፋ አወጀ። ከመስከረም 25/2012 በኋላ የፌደራል መንግሥቱ ሕጋዊ ዕውቅናና ውክልና እንደሌለው በመግለጽ ለማዕከላዊው መንግሥት ተገዢ እንደማይሆን አስታወቀ።

በዚህ ሒደት የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ሕገ-ወጥ ምርጫ በማካሄዱ ሕገ-ወጥ ቡድን እንደሆነ በማወጅ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን በጀት በወረዳዎችና በክፍላተ-ከተሞች ደረጃ እንደሚያሰራጭ አስታወቀ። በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እያደገ ሔዶ አንዱ ሌላውን ሕገ-ወጥ ቡድን በሚል ሲካሰሱ ቀናት ተቆጠሩ። ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ለክልሉ ሕገ-ወጥ መዋቅር እንደማይሰጥ ከወሰነበት ቀን ጀምሮ፣ ህወሓት “የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት አንዳወጀ እንቆጥረዋለን” በማለት ከውይይት ይልቅ ወደ ጦርነት የሚያመሩ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ ነበር።

ህወሓት ጳጉሜ 4/2012 ባካሄደው ክልላዊ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጥቅምት 23/2013 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ በደል መፈጸሙን በመግለጽ፣ አሁን ላይ ያለው የመጨረሻ አማራጭ እንደ ሕዝብ መዋጋት መሆኑን በይፋ ተናግረው ነበር። ደብረጽዮን በመግለጫቸው ከመንገዳችን የሚያደናቅፈንን ኃይል ውጊያ እንገጥማለን በማለት የተፈራውን ጦርነት ለመቀስቀስ ጉትጎታ አድርገዋል።

“የምንገጥመው ውጊያ የሕዝብ ውጊያ ነው የሚሆነው። ድሉ የኛ ነው፤ ድሮም የኛ ነበር፤ አሁንም አሽናፊዎች እኛ ነን” ሲሉም የጦርነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ነበር። ፕሬዝዳንቱ አክለውም “የፈለገው መሣሪያ አያሸንፈንም፤ እንደ ትግራይ ተዘጋጅተናል፤ እንገጥማለን” ሲሉ የጦርነት ነጋሪቱን ጎስመዋል።

ይህ በሆነ በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2013 ሌሊት ላይ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው መቀሌ ላይ ያልታሰበ እና መላ ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ ድርጊት ተፈጽሞ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 25/2013 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው አረዱ።

በማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማው ዜና፣ “ህወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል” የሚል ነበር። ህወሓት ያልተፈለገ ጦርነት መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያ በአካባቢው “የሕግ የማስከበር ሥራ” እንዲሠራ ትዕዛዝ መሰጠቱን አሳውቀው ነበር። በቃላት ጦርነት የገነገነው የኹለቱ ኃይሎች ልዩነት ከጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ ወደ ኃይል ፍልሚያ መቀየሩ የሚታወስ ነው።

የጦርነቱ የአንድ ዓመት ጉዞ
ጥቅምት 24/2013 በይፋ የተጀመረው ጦርነት በፌዴራል መንግሥት በኩል “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ መንግሥትም ተገዶ የገባባት ጦርነት መሆኑን ሲገልጽ ነበር። መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል መከላከያ ሠራዊት ማሰማራቱን ተከትሎ የሕግ ማስከበር ዘመቻው በ17 ቀን መጠናቀቁ ቢገልጽም፣ ጦርነቱ ግን ለስምንት ወራት በክልሉ ቆይቷል።

ጦርነቱ ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተወስኖ ቢቆይም፣ መከላከያ ሠራዊት ሰኔ 21/2013 ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሕወሓት በ15 ቀን ልዩነት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልል እስካሁንም ድረስ የቆየ ጥቃት እየፈጸመ ነው።
የተናጠል ተኩስ አቅሙን ተከትሎ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልል የተስፋፋው ጦርነት፣ ለጦርነቱ መራዘም እና የጦርነቱ አውድ እንዲሰፋ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኀበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ፣ ህወሓት ለ27 ዓመታት በብዙ ነገር እራሱን ሲያዘጋጅ የቆየ በመሆኑ ከተናጠል ተኩስ አቁም በኋላ አማራ እና አፋር ክልልን ሊወር መቻሉን ይገልጻሉ።

ለስምንት ወራት የነበረው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በፌደራል መንግሥት በኩል በ17 ቀናት ተጠናቋል ቢባልም፣ እንደ ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ታመነ ህወሓት በወቅቱ በነበረው ውጊያ ሳይጎዳ በስልት አፈግፍጎ እራሱን የማደራጀት ወታደራዊ ስልት መጠቀሙን ይገልጻሉ። እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ህወሓት እራሱን አደራጅቶ ወደ ጦርነት ለመመለስ የተጠቀመው ስልት መከላከያ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ አማራ እና አፋር ክልል ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዕድል አግኝቷል።

“ህወሓት ለ27 ዓመት ሲዘጋጅ በየተራራው እና በየዋሻው መሣሪያ እና ነዳጅ ቀብሯል” የሚሉት ባለሙያው፣ መከላከያ በትግራይ ክልል በቆየባቸው ስምንት ወራት በህወሓት እጅ ያሉ ከባድ መሣሪዎችን የማውደም እና የመቀማት ሥራ ቢሰራም፣ ቡድኑ እስካሁን ድረስ ከባድ መሣሪያ አለው። ይህ ሊሆን የቻለው ቡድኑ ቀድሞ እራሱን በማዘጋጀቱ እና መንግሥት ያልተዘጋጀበትና ያልጠበቀው ሁኔታ በመፈጠሩ መሆኑን ይጠቁሟሉ።

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያሰማራው መከላከያ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሲወጣ፣ ህወሓትን መደምሰሱን እና ይዟቸው የነበሩ ከባድ መሣሪያዎችን ማውደሙንና ማስመለሱን ገልጾ ነበር። በወቅቱ መረጃ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “አሸባሪው ህወሓት በምንም መልኩ ለአገር ሕልውና አስጊ ባለመሆኑ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ተደርጓል፤ የክልሉ ሕዝብም የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ህወሓት ተደምስሷል በሚለው ሐሳብ ወታደራዊ ባለሙያው አይስማሙም፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በወታደራዊ ሙያ ህወሓት ተደምሷል ከተባለ አሁን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ሊያደርስ እንደማይችል በመግለጽ ነው። መከላከያ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ ህቡድኑ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን መቆጣጠሩ የመንግሥት ከፍተት መሆኑን ይገጻሉ።

በጦርነቱ ውስጥ በነበረው ኹኔታ መከላከያ ትግራይ ክልል ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተቆጣጥሮ ከትግራይ ከወጣ በኋላ፣ የአማራ እና የአፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎችን የተቆጣጠረበት ሁኔታ፣ በመንግሥት በኩል በተሰለፈው መከላከያ፣ ወታደራዊ ክፍትት መኖሩን መረዳት እንደሚያስችል ሻለቃው ይናገራሉ።

“ወታደራዊ ክፍተት ነበር፤ ይሄን መካድ አይቻልም” የሚሉት ሻለቃው፣ ህወሓት አሁን እስከደረሰባቸው አካባቢዎች ድረስ ያሉትን ቦታዎች የተቆጣጠረው፣ ከወታደራዊ ክፍተቱ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያሰራጨው የሀሰት መረጃ ሳይዋጋ ሕዝብ እንዲሽሽ ማድረግ በመቻሉ ነው ይላሉ።

መከላከያ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ በ15 ቀናት ልዩነት ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ላይ የከፈተውን ጦርነት፣ መከላከያ ለምን መከላከል አልቻለም የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል። ባለሙያው እንደሚሉት መከላከያ በትጥቅም በመሪም የልተዘጋጀ እና ቀድሞ የነበሩ ከፍተቶች ላይ የሚደረገው ለውጥ ያለመጠናቀቁን እና ህወሓት በሚያሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ ሕዝቡ በመደናገር የተገፋበት ሁኔታ መኖሩን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

ቀደም ብሎ በወጊያ አፈጻጸሙ ላይ ስህተት መፈጠሩን የሚያስታውሱት ወታደራዊ ባለሙያው፣ በወቅቱ የተከሰተው ስህተት ለጦርነቱ መስፋፋት እና መራዘም ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው። መከላከያ ላይ የታየው ከፍተት ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልል ሲገባ የመከላከል ሥራ እንዳይሠራ አድርጓልም ብለዋል።

በሚቀጥለው ረቡዕ አንደኛ ዓመቱን የሚይዘው ጦርነት፣ መነሻውን በትግራይ ክልል ያድርግ እንጂ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል መስፋፈቱን ተከትሎ የዜጎችን ሞት፣ ርሀብ፣ መፈናቀልና እንግልት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አለመሆኑን የሚያነሱት ባለሙያው፣ የተራዘመ ጦርት በአገር ላይ የሚሳድረው ዘረፈ ብዙ ችግር የጠነከረ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በጦርነቱ ከሚከሰተው የዜጎች ሕይወት ማለፍ በተጨማሪ፣ አሁን ላይ በጦርነቱ ከአማራ እና አፋር ክልል ብቻ 900 ሺሕ በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ደግሞ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸው እየተገለጸ ነው።
አንደኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ጦርነት በአጭር ጊዜ እልባት አግኝቶ የዜጎች ሞትና መፈናቀል እንዲቆም መንግሥት ለተጨማሪ ጦርነት የማይዳርግ ዕርምጃ በመውሰድ አሁን ያለውን ቀውስ ማስቆም እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል። በተለይ በመከላከያ አመራር በኩል ጠንከር ያለ አመራር በመስጠት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ገልጸዋል።

መከላከያ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎችና በሚያደርጋቸው ተግባሮች፣ ከባለፈው ስህተቱ በመማር በውስጡ ሆነው ከኋላ የሚከዱ እና ጦርነቱን በሚፈለገው ልክ የማይመሩ አመራሮችን መፈተሸ እና ለይቶ ማውጣት እንደሚገባ አመላክተዋል። “የመሪ እንጅ የተመሪ ቆሻሻ የለም” የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ መከላከያ ዳግመኛ ስህተት እንዳይፈጥር መጠንቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

“በውትድርና መሳሳት ሕይወት መክፈል ነው” የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ መከላከያ ከሚያደርገው ትግል በተጨማሪ በተሳሳተ መረጃ የሚሸበረውን እና የሚሸሸውን ሕዝብ ሥነ ልቦና መጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ጦርነቱ የኃይል ጦርነት ብቻ አለመሆኑን የሚያሳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታዩ ኹነቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እና በተለይ የጦርነቱ መሪ የሚመስሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎችን በቀይ መስመር መገደብ እንደሚገባ ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here