ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ሙሌት ድርድር ጫና ነበረባት?

Views: 370

የ አትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና ልዑካን ቡድኖቻቸው በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንተር ዲሲ ለሦስት ቀናት የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በታዛቢነት በተገኙበት ለሦስት ቀናት ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ረቡዕ ጥር 6 2012 ላይ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በዚህ መግለጫ ሚኒስትሮቹ ባለፉት አራት ስብሰባዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሞላል እና አተገባበር ላይ አጠቃላይ የሆነ፣ ትብብርን የሚያጠናክር፣ ዘላቂነት ያለው እና ሁሉንም ወገን የሚጠቅም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተገኙትን መሻሻሎች አድንቀዋል፡፡ ሁሉም ወገኖች ስብሰባው በጥሩ ውጤት እንደተጠናቀቀም ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ ያወጡት የጋራ መግለጫ ስድስት ዋና ዋና ነጥቦችን የያዘ ሲሆን የግድቡ አሞላል በደረጃዎች እንደሚሆን፣ ይህም የጥቁር አባይን የውሀ ሁኔታ እና የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚኖረውን ውጤት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሙሌቱ በሐምሌ እና ነሐሴ የሚካሔድ መሆኑን እና በአንዳንድ ሁኔታ በመስከረምም ሊቀጥል እንደሚችል ይገልጻል፡፡ በመጀመሪያ የሙሌት ደረጃውም ከባሕር ጠለል በላይ 595 ሜትር ድረስ እንደሚሞላ እና ይህም ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እንደሚያስችል ተጠቅሶ ይህም ግብጽ እና ሱዳን በዚሁ ጊዜ ከፍተኛ ድርቅ ቢደርስባቸው ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ይገልጻል፡፡ ቀጣይ የሙሌት ደረጃዎች እና የረጅም ጊዜ አሠራሩ የሚከናወኑትም ሦስቱ ወገኖች ወደፊት በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ሦስቱን ባለድርሻ አካላት ለማቀናጀት እና ያለመግባባቶችን ለመፍታት የሚሠራ አካል እንደሚቋቋምም ተጠቅሷል፡፡ የቴክኒክ እና ሕጋዊ ውይይቶች እየተደረጉ ከቆዩ በኋላ ሚኒስትሮቹ ከአስራ አንድ ቀን በኋላ ተገናኝተው በሕዳሴው ግድብ አሞላል እና አሠራር ላይ የተዘጋጀን አጠቃላይ ስምምነት ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል፡፡

ይህን መግለጫ ተከትሎ የተለያዩ ቀናም ሆኑ ጥሩ ያልሆኑ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ነገሮች በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ጫና ኢትዮጵያ እንድትቀበል ለማድረግ እንደተሞከረ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ ይህ ጥርጣሬ ክብደት እንዲኖረው የሚያደርጉ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ለዘመናት የቆየው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብን ድምፅ ለማግኘት ግብጽ የሔደችው መንገድ ነው፡፡ የሕዳሴው ግድብ በኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ብቻ እንዲሠራ የሆነው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ከኢትዮጵያ ግንባታ ጋር ለመቆም ልበ ሙሉ ባለመሆኑን ያስተውልዋል፡ ፡ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሳትቀበለው የቆየች ቢሆንም ግብጽ ሦስተኛ ወገን ድርድሩን እንዲቀላቀል ጥሪ ስታደርግ መቆየቷም የልቧ እንደደረሰ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው የቅርብ ጊዜ ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኃይል ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርጎ ከነበረው የመጨረሻው የሦስቱ ወገኖች ውይይት በኋላ ግብጾቹ ላለመስማማት አቅደው የመጡ ይመስሉ ነበር ማለታቸው ነው፡ ፡ ይህም ግብጾቹ ቀጥሎ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ የሚሳተፉበትን ስብሰባ መምረጣቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በዋሽንተን ኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ጫና ሊበዛ እንደሚችል ጥርጣሬው እንዲገለብት አድርጓል፡፡

በዋሽንተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህበራዊ ገፁ ባወጣው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ አቋም “ኢትዮጵያ ትክክለኛና በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እስካላት ድረስ የውይይት ቦታው ተጽእኖ አያሳድርባትም” የሚል ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ የናይል ኤክስፐርት የሆኑት ወንድወሰን ሚጫጎ እንደሚሉት በግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች የሚያደርጓቸው ውይይቶች እንዲህ ተቀራበው አያውቁም፡፡ ባለፈው ሁለት ወራት ለአራት ጊዜ የተደረጉት ስብሰባዎች እና ከ11 ቀናት በኋላ የሚደረገው ሌላ ስብሰባ እውን የሆኑት በአሜሪካ አደራዳሪነት አገሮቹ ከተገናኙ በኋላ ነው፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል ከዚህ በፊት በረጅም ጊዜ ይደረጉ የነበሩት ውይይቶች በፍጥነት መካሔዳቸው አደራዳሪዎቹ ያሳደሩትን ጫና የሚያሳይ ነው፡፡

ወንድወሰን እንደሚሉት መግለጫው ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ውስጥ ጫና መኖሩን በግልጽ የሚጠቁም ነገር ባይኖርም የሚሞላበትን ወራት ገድቦ ማስቀመጡ በጣም በትንሹ ሊጎረብጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው አሉ ወንድወሰን ኢትዮጵያ የራሷን ድምፅ ብቻ የምትሰማ ብትሆን እንኳን የምትሞላው ፍሰቱ በሚጨምርባቸው በተጠቀሱት ወራት መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ፍሰቱ በሚጨምርባቸው ወራት ተብሎ ቢቀመጥ ይሻል ነበር ባይ ናቸው፡፡

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የናይል ተመራማሪ እና ተንታኝ እንደገለፁት ደግሞ ዓባይ ወንዝ የውሃ መጠኑ እንደስሙ ግዝፈት አይደለም፡፡ ለማጠራቀም የሚያስችል የውሃ መጠን የሚገኘው በስምምነቱ ላይ በተጠቀሱት ሦስት ወራት ነው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ወራት መስማማቱ ተገቢ ነው፡፡ በክረምት ወራት የውሃው የአፈር መጠን የሚጨምር በመሆኑ የደለል ችግር ይፈጥር እንደሆነ ለቀረበላቸውም ጥያቄ ግድቡ ይህንን ለመመለስ የተዘጋጀለት መንገድ ስላለው የሚያሳስብ አይደለም ብለዋል፡ ፡

አንዳንድ በጋራ መግለጫው ላይ የተገለጹ ባለሙያ ላልሆኑ ሰዎች ግልጽ ያልሆኑ ገለጻዎችን ሲያብራሩም የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌት የሚባለው ኢትዮጵያ በመጪው ነሐሴ ልትጀምር ያሰበችው የግድብ ሙሌት ሲሆን በዚህም እንደተጠቀሰው ከባሕር ጠለል በላይ 595 ሜትር ድረስ የሚደርስ ውሃ እንደሚሞላ ይጠበቃል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰውም ይህ መጠን ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትን ለማስጀመር በቂ ነው፡፡

መግለጫው የግድቡ ሙሌት ረጅም ደረቅ ዓመታት፣ ድርቅ እና ረጅም ድርቅ በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች መኖሩን ግምት ውስጥ ባስገባ መልክ እንደሚከናወን መግለጹን አስመልክተው ተመራማሪው ይህ አገላለጽ በረሀ በሆኑት በግብጽና ሱዳን ቦታዎች ያለውን መደበኛ ደረቅነት ሳይሆን ህይወት ላይ አደጋ የሚያደርሰውን አይነት የድርቅ አደጋ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለያዕቆብ አርሳኖ (ፕሮፌሰር) ይህ ሦስቱ ወገኖች ያወጡት የጋራ መግለጫ በሒደት ላይ ባለ ነገር ላይ ጠቅለል ያለ መረጃ ነው፡ ፡ እንደ እርሳቸው አባባል ሒደቱ አላለቀም ስለዚህ ጉዳዮቹ በተናጠል አልተበጠሩም፡ ፡ በመሆኑም የሦስተኛ ወገኞች ጫና ይኑር አይኑር ለመጠቆም የሚቻለው ከ11 ቀናት በኋላ ተገናኝተው ስምምነቱን ሲጨርሱት ነው ባይ ናቸው፡፡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በችኮላ ጫና ነበረብን እያሉ እንደሚገኙት የግብጽ የመገናኛ ብዙኋንም የሦስተኛ ወገኖቹ ጫና በአገራቸው ላይ ስለበዛ ተደራዳሪዎቻችን ተዳክመዋል እያሉ እንደሚገኙም ያዕቆብ ጠቁመዋል፡፡

የተደራዳሪዎቹን ብቃት አስመልክተው በሰጡት አስተያየትም ከግድቡ ጥንስስ ጀምሮ ግብጽ መጀመር የለባችሁም ብትልም የኢትዮጵያ ፍላጎት ያለመገታቱ እንዲሁም መጨረሻው እንዳይቀርብ ብትጥርም እስከ አሁን ይህ እንደሚሆን የታየ ነገር ያለመኖሩ የኢትዮጵያን ተደራዳሪዎች ብቃት የሚያሳይ ነው፡፡ የራሴን የውሃ ሃብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ አልጠይቅም ብላ ከተነሳችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ እልህ አስጨራሽ ድርድሮች ተካሒደዋል ያሉት ያዕቆብ በሒደቱ ግን ወደ ኋላ መመለስ ሳይሆን የግብጽ ሁኔታውን መቀበል ነው እየታየ የመጣው ነው ያሉት፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ማየት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት የተለያዩ ሙያዎች ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የግል ሥራቸውን የዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸውን እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊነታቸውን ትተው የአገር ፍቅር አነሳስቷቸው በትጋት የሚሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በማጠቃላያነት ጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶች አስመልክተው ወንድወሰን እንደገለጹት የሚደረገው ስምምነት የጋራ መግባቢያ እንጂ አስገዳጅ ባለመሆኑ ለጋራ ጥቅም፣ መግባባት እና ትብብርን ለማምጣት እንደተደረገ ውይይት ብቻ መወሰድ አለበት፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com