የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ፣ በእግር መጓዝን፣ የብስክሌትና የሕዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀምን ማበረታታት እንዲሁም ስለመንገድ ደኅንነት ግንዛቤ ማስጨበጥ የመተግበሪያው መመሪያ (ማኑዋል) ተቀዳሚ ዓላማ እንደሆነ አመላክቷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ከመቀነስ ባለፈ፣ መንገድ የኹሉም መሆኑን ለነዋሪዎች ግንዛቤ መፍጠር ሌላው ዓላማ እንደሆነም ነው ቢሮው የገለጸው፡፡
የማኑዋሉ መዘጋጀት፣ በመንገድ ለሰው መርሃ ግብር፣ መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነጻ በማድረግ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንዲያካሄዱ በማድረግ ጤናማ ማኅበረስብ መፍጠር ያስችላልም ተብሏል፡፡
መንገድ ለሰው መርሃ ግብር የታለመለትን ዓላማ ማሳካት እንዲቻል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ቢሮው አስረድቷል፡፡
በዚህም ነዋሪው የባለቤትነት ስሜት ኖሮት በራሱ መርሃ ግብሮችን ማከናወን እንዲችል የድጋፍና ክትትል ሥራው መጠናከር አለበት ነው የተባለው፡፡
ከተሽከርካሪ ነጻ መንገዶች ቀን በኢትዮጵያ ከኅዳር 2011 ጀምሮ መከበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ቦታዎቹን ወደ 16 በማሳደግ ከማዘጋጃ ቤት እስከ ቴዎድሮስ አደባባይ በየሳምንቱ እንዲከበር መደረጉም በመረጃው ተነስቷል፡፡
እንዲሁም መርሃ ግብሩን ሕብረተሰቡ ተቀብሎ የራሱ እንዲያደርገው ወደ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ መውረዱም ነው የተጠቆመው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ “መንገድ ለሰው” በመጀመሩ ለሌሎችም የአገሪቱ ትላልቅ የክልል ከተሞች አርዓያ መሆን ተችሏል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የ10 ዓመት ሞተር አልባ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በተለይም በእግረኞች እና ብስክሌቶች ላይ የሚከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነም ጨምሮ አሳውቋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014


