የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ግዢ በአንድ ማዕከል ለማድረግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

0
621

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ባቡር ኮርፖሬሽን እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ግዢ በአንድ ማዕከል እና ተቋም ቁጥጥር ሥር ሆኖ እንዲከናወን ለማድረግ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገለፁ።

ረቂቁ በፋይናንስ ሚኒስቴር በሚገኘው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳዳር ኤጀንሲ የተዘጋጀ ሲሆን በመንግሥት ልማት ድርጅቶች በኩል ያለውን የአሰራር ክፍተት በማስቀረት ደረጃ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው በ2001 የወጣው ረቂቅ አዋጅ መሰረት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በቦርድ እና በአስተዳደሩ ውሳኔ በራሳቸው ግዢ መፈፀም ይችላሉ። ይሁን እንጂ፤ ይህ ዓይነቱ አሰራር መንግሥትን ለከፍተኛ ኪሳራ በመዳረጉና ለሙስና በር በመክፈቱ፤ የአዋጁን መስተካከል ግዴታ እንዳደረጉት ተገልጿል።
ሁሉንም የመንግሥት ግዢዎች በአንድ ማዕከል ማድረጉ ሒደቱን ለቁጥጥር ምቹ ከማድረጉም በላይ ለግልፀኝነት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ በአሁኑ ወቅት ውይይት እየተደረገት መሆኑን የገለፁት የኤጀንሲው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሰጠኝ ገላን፤ የአዋጁ አፈጻጸም በቀጣይ በሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች እንደሚወሰን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አሁን በሥራ ላይ አሰራር በተቃራኒ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሰረት የማዕከል ግዢ ስር እንደሚታቀፉ የታወቀ ሲሆን ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ጋር ያሏቸው ተመሳሳይ ፍላጎት ጋር በማጠቃለል የአንዳንድ ዕቃዎች ፍላጎታቸው እንደሚሟላ ታውቋል።

በአዲሱ ረቂቅ ከተካተቱ ዋና ዋና ለውጦች መካከል አገር በቀል ድርጅቶች ዓለም ዐቀፍ ጨረታዎች ላይ በልዩ አግባብ እንዲወዳደሩ የታከለ ዋጋ ምጣኔያቸው (‘ቫልዩ አድሽን’) ከ35 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በተጨማሪም በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ማንኛውም የመንግሥት ግዢ በሚፈፅምበትና ንብረት በሚወገድበት ወቅት ከአባቢያዊ ብክለትነን የማያስከትል መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። በረቂቅ አዋጁ መሰረት የዓለም ዐቀፍ ግልፅ ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።

አሁን ባለው ሕግ መሰረት ለግንባታዎች በዓለም ዐቀፍ ጨረታ ግዢ ሊፈፀም የሚችለው ከ50 ሚሊየን በላይ ሊያወጣ ለሚችሉ ሥራዎች ሲሆን ጣሪያው በረቂቅ አዋጁ ላይ ወደ 150 ሚሊየን ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በተጨማሪም ለምክር አገልግሎት ጣሪያው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር አድጓል። በሌላ በኩል ለዕቃ ግዢዎች ጣሪያው አሁን በሥራ ላይ ካለው በአምስት እጥፍ እንዲያድግ በረቂቅ አዋጁ ተገልጿል።

መንግሥት ለተለያዩ ግዢዎች የአገሪቷን 60 በመቶ በላይ ዓመታዊ በጀት የሚያወጣ ሲሆን ይህም የአገሪቷን አጠቃላይ ምርት 14 በመቶ ይሸፍናል።
በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ይላካል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም በያዝነው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በፓርላማ ወይይት ተደርጎበት ይደነገጋል ተብሎ ታቅዷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here