ምርጫ ቦርድ የአመራር አባላቱን ቁጥር ቀነሰ

0
748

የኢፌዲሪ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አምስት ዝቅ ማለቱ ታወቀ። ሥራዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወንና በመንግሥት በኩል የሚወጣውን ተጨማሪ ወጪ ለመቀነስ ታስቦ የቦርድ አባላቱ ቁጥር እንዲቀነስ ሆኗል። የሥራ አመራሩ ቦርድ አባላት ሙሉ ጊዜያቸውን በቦርዱ ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ሲሆን ተሿሚዎቹ ቋሚ ሆነው ከሠሩ አምስቱም አባላት ውጤታማ ሥራ እንደሚሰሩ ታምኖበታል።

የአመራር አባላቱን በእጩነት ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆኑ በአባላት ምልመላ ሒደት ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ለማድረግ ታስቧል። ይህም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ከመፍጠር አንፃር አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት እንደተገለፀው ከዚህ ቀደም በነበረው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆንና ብቃት ማነስ ምክንያት የተካሄዱት አገራዊ ምርጫዎች እጅግ አወዛጋቢ እንደነበሩ ተብራርቷል። ከዚህም በመነሳት መንግሥት የቀየሰውን የለውጥ፣ የዲሞክራሲና የፖለቲካ አንቅስቃሴ ለማረጋገጥ ምርጫ ቦርድን ማቋቋም እንደታመነበት ለመረዳት ተችሏል። የረቂቅ አዋጁ አላማም ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ለማደራጀት እና ምቹ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከሥራ አመራር አባላት ቁጥር በተጨማሪ አሁን ሥራ ላይ ባለው የምርጫ ሕግ ላይ የአባላት የሥራ ዘመን ማስተካከያ ተደርጎበት ወደ ኹለት የምርጫ ዘመን ከፍ እንዲል ተደርጓል። ለዚህም እንደምክንያት የቀረበው ከዚህ በፊት ሁሉም የቦርድ አባላት በተመሳሳይ ጊዜ የሥራ ዘመናቸው እንደሚጠናቀቅና ይህም በቦርዱ ላይ የሚኖረውን ተቋማዊ ትውስታ እንደሚያጠፋና የቦርዱ አባላት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ መሆኑ በቂ ልምድ የሚያስገኝ አለመሆኑ እንደ ችግር ተነስቷል። ከዚህም በተጨማሪ ለተተኪ አባላት ልምድ ማካፈሉ ላይም ክፍተት መታየቱ ዋነኛው ችግር ነው። የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍም የሥራ አመራር ቦርዱ አባላት ሹመት በተለያየ ጊዜ እንዲሆን ተደርጓል።

የአባላት ሹመትም የሚፀድቀው ወይም ከኃላፊነታቸው ለማንሳት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 2/3 ድምፅ እንደሚያስፈልግ እና አሳማኝ ምክንያት በሌለበት ደግሞ አባላትን በቀላሉ ማንሳት እንደማይቻል ከረቂቅ አዋጁ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ደግሞ የቦርዱን አባላት ነፃነት ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ተገልጿል።
የኮሚሽን ዓይነት አቋም እንዲኖረው የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ያለበት ይህ ቦርድ በአንድ ዋና ኃላፊና በአንድ ምክትል ዋና ኃላፊ የሚመራ ይሆናል። ተጠሪነታቸውም ዋና ኃላፊው ለሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ ሲሆን የምክትል ዋና ኃላፊው ደግሞ ለዋና ኃላፊው ተጠሪ ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here