ልጁ የኹለተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ ሳለ አብሯት ካደገችው ልጅ ፍቅር ይይዘዋል። በትምህርቱ እጅግ ጎበዝ ከመሆኑ የተነሳ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኹሉንም የትምህርት አይነት ኤ በማምጣት ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ሕክምና ትምህርቱን ጀመረ። ፍቅር ዓይን የለውምና በአብሮ አደጉ ልጅ ፍቅር ተነድፎ ትምህርቱን ከኹለት ዓመት በላይ ሊቀጥልበት አልቻለም። በዚህም ወደትውልድ አገሩ ከዩኒቨርስቲው መልቀቂያ ሞልቶ ተመለሰ።
በዚህ ኹሉ ሒደት ውስጥ፣ የተወደደችው ልጅ የሰፈሯ ልጅ እሷን ወዶ ትምህርቱን ማቋረጡን አታውቅም። በመሀል ለኹለቱም የምትቀርብ የልብ ጓደኛቸው ጉዳዩን በደንብ ስለምታውቅ መፍትሔ መፈለግ እንዳለባት በማሰብ ልጁን ወደትምህርት ገበታው ለመመለስ ቆርጣ ተነሳች። እሱንም ልጅቷንም ለማሳመን ቆረጠች።
ከብዙ ትግል እና እልህ አስጨራሽ የማሳመን ሒደት በኋላ ልጅቷን “እሺ” ታስብላታለች። እዚህ ጋር የተፈቀረችው ጉብል ለልጁ ምንም ዓይነት ስሜት እንደሌላት ልብ ማለት ያሻል፤ ይሁን እንጂ ጓደኛዋ የሚወዳትን ብታገባ ደስተኛ ሒወት እንደምትመራ በመንገር እና ፍቅር በመለማመድ እንደሚመጣ በማሳመን ነው እሺታዋን ያገኘችው። ልጁም የዓይኑን ረሀብ ያሳመነችለትን ባለውለታ ጓደኛ እጅግ አመስግኖ ከተፈቃሪዋ ጋር ግንኙነቱን ጀመረ።
ይሁንና ግንኙነታቸውን በጀመሩ በ 1 ወር ጊዜ ውስጥ፣ ይህ አፍቃሪ፣ ፍቅረኛውን ግንኙነታቸው መቋረጥ እንዳለበት ይነግራታል። ልጅቷ ለዚሁ ልጅ ብላ፣ ከገባበት መከራ ለማውጣት የጀመረችውን ግንኙነት ወደ ፍቅር አሳድጋ እየኖረች ባለችበት ሰዓት እንደዚህ አይነት ዱብ ዕዳ ሲከሰት እጅግ በጣም ልቧ እንደሚሰበር ለመገመት የግድ ጠቢብ መሆን አይጠበቅም። የሆነው ሆኖ፣ ይህችው መከረኛ የኹለቱም ጓደኛ ለምን እንደተዋት በብስጭት ስትጠይቀው፣ የተግባቦት ክፍተት እንዳለባቸው ነገራት።
ለትምህርት ደንታ የሌላት ከመሆኗ የተነሳ 9ነኛ ክፍልን ኹለት ጊዜ ወድቃለች። እሱ ደሞ በተቃራኒው የሕክምና ትምህርት ተማሪ ነው። እዚህ ጋር ነው ክፍተቱ የተፈጠረው። የኹለቱም ጓደኛ፣ ቀጥላ ትጠይቀዋለች ፣“በትምህርት ጎበዝ እንዳልሆነች ቀድመህ ታውቅ የለ? አሁን ምን አዲስ ነገር መጣ?” በዚህ ደረጃ ቋንቋችን የባቢሎንን ግንብ ያህል ይለያያል ብሎ እንዳልገመተ ከይቅርታ ጋር ያስረዳታል።
ቀጥሎም ፣በትምህርት ሰነፍ ብትሆን ችግር የለውም፣ቢያንስ የሥዕል ወይ የሙዚቃ ፣ የሆነ አይነት ክህሎት ባለቤት ብትሆን እንደሚመኝ አስረዳት።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014


