የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ትግበራ ላይ ውይይት ተካሄደ

0
1030

የጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽንን ለመጠቀምና በጋራ ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የሦስት ቀናት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የምክክር መድረኩ ባሳለፍነው ሐሙስ ጥቅምት 25/2014 የተጀመረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የተቀናጀ የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ማዕቀፍ አገራዊ የድርጅት መርሃ-ግብር ትግበራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
በመድረኩ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካይ አንድሬ ኑኩሩማ፣ የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ተወካዮች ተሳትፈውበታል።
የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቱሉ በሻ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ለማኅበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው ከመሆኑም በላይ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አዝማሚያ ያላቸው ተግዳሮቶችን ለመቋቋም፣ ተጽዕኗቸውን ለመቀነስ እንዲሁም ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በመድረኩ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡
ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ምን፣ የት ቦታ፣ መቼ፣ በምን መጠን፣ ለምን እና እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ወሳኝ መረጃ ለውሳኔ ሰጪ፣ ለፖሊሲ አውጪ እና ለተጠቃሚ አካላት መስጠት የሚያስችል ወሳኝ ዲጂታል ገንዘብ ወይንም ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የዓለም አገራት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፈጣን ዕድገት እያሳዩ በመምጣታቸው፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት በእጅጉ እንዲሻሻል እና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረጉ እንደሚገኝም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅት በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን፣ በ1946 ተመሥርቶ በአየር ፎቶግራፍ፣ በቅየሳ፣ በካርታ አነሳስ፣ በሪሞት ሴንሲንግና ጂአይኤስ ዘዴዎች መረጃ የሚሰበሰብ፣ የሚያቀናብርና ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ብሎም ከጂኦግራፊያዊ ማጣቀሻ ጋር የተዛመደ የቦታ መረጃ በመስጠት ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here