የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አተገባበር ጥንቃቄን ይሻል!

0
808

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕግን ተግባራዊ ካደረገች ወዲህ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ አውጃለች። በተለይ አሁን አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው የህወሓት የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ በተደጋጋሚ እየታወጀ ውጤታማ ሳይሆን ቆይቷል። ከዛም ወዲህ እስካሁን ውጤታቸው ተለይቶ ያልታወቀ ዐዋጆች በተለያዩ ቀጠናዎች ታውጀው ነበር።

ጥቅምት 23፣ 2014 በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንስትሮች ምክር ቤት የታወጀውና ተግባራዊ ከሆነበት ቀን በኋላ የጸደቀው ዐዋጅ፣ ከዚህ ቀደም ከወጡት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ልዩ የሚያደርጉት ባህርያትም አሉት። የበፊቶቹ የሕዝብን አመጽ ለመግታትና ዝም አስብሎ ለማስተዳደር የታለሙ እንደነበር ይታመናል። የአሁኑ ግን እየተካሄደ ያለን ጦርነት አቅጣጫ ለመቀየርና ውጤታማ ሥራን ለመሥራት እንደሆነ ተነግሯል።

ሕዝብ የትኛውንም ሕግ ሆነ ዐዋጅ፣ “ስላላወኩ ነው ያጠፋሁት፤ ይቅርታ ይደረግልኝ” ቢል ተቀባይነት አያገኝም። ኹሉም ሰው ሕግን የማወቅ ግዴታ ያለበትን ያህል፣ መንግሥትም የጸደቀውን ዐዋጅም ሆነ ደንብ ለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

ሕዝብን አዲስ ስለወጣ ሕግ ለማሳወቅ እስካሁን የሚሠራበት መንገድ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታተም አድርጎ ሕዝብ ራሱ ገዝቶ እንዲያውቀው ማድረግ ነው። ይህን ሕግ፣ ሚዲያዎች በፈቃዳቸው ሳይገደዱ የመረጡትን ክፍል በዜና መልክ ያቀርባሉ እንጂ፣ ኹሉንም ለኹሉም ለማሳወቅ የሚችሉበት አሠራር እንደሌላቸው ይታወቃል። ይህ የተለመደው መንገድ በከተማ ላሉ ሚዲያን ለሚከታተሉ ብቻ የሚያገለግል እንደመሆኑ፣ በገጠርም ያሉ መገናኛ ብዙኀን የማይደርስባቸውን ዜጎችንም ለማሳወቅ መጣር እንዳለበት የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ተፈፃሚነት እንደስሙ አስቸኳይ በመሆኑና ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት እንደሌሎች ሕጎች ረዘም ያለ የመወያያም ሆነ የማሳወቂያ ጊዜ ስለማይኖረው፣ እያንዳንዱን የዐዋጁን ክፍል ሕዝብ እንዲያውቀው መደረግ አለበት። ሕብረተሰቡ በማወቁ እንዲጠነቀቅና እንዲያግዝ ከማድረጉ ባሻገር፣ በደጋፊም ሆነ በጠላት መታወቁ እንደሚጠቅም ሊታመንበት ይገባል።

የመንግሥት ኃላፊነት ብዙ መሆኑ ቢታወቅም፣ አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ደጋፊው እንዲበዛ፣ ጠላቴ ብሎ የፈረጀው ኃይል ደጋፊዎች እንዲመናመኑ ማድረግ በጦርነት ወቅት የሚጠበቅ የፕሮፓጋዳ ሥራ እንደሆነ ይታመናል። “ተበልጫለሁ” በሚል ከነጭራሹ ዝም ማለት ተገቢ ባለመሆኑ፣ ወጤታማ የሚያደርግ ጠላት የተጠቀመበትንም መንገድ ቢሆን ለአገር ሲባል መጠቀሙ የሚያስኮንንበት መንገድ ሊኖር አይገባም።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዓላማ ለፖለቲከኛውና ለወቅታዊ ኹኔታው ቅርብ ለሆነ ወገን ግልጽ ቢሆንም፣ ዓላማውንና ይዘቱን እየደጋገሙ ለሕዝብ ማስረዳቱ ጥቅም እንዳለው ሊታወቅ ይገባል። ውሸት እንኳን ተደጋግሞ ሲነገር እንደእውነት መስሎ ተቀባይነት እንደሚያገኝና ሕዝብን እንደሚያሳምን ካለፈው ዘመን ታሪካችን መማር ይገባናል። እውነትን ይዣለሁ በሚል መዘናጋትም ሆነ በራስ ተማምኖ ተቀምጦ መጠበቁ ዋጋ እንደሚያስከፍል መረዳት ያስፈልጋል።

ሕዝብ ማወቅ ያለበት ዐዋጁን በተመለከተ ይዘቱን ብቻ ሳይሆን፣ ማን እታች ድረስ እንደሚያስፈጽመው ጭምር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ጥቆማም ሆነ ጥያቄ ካለው በምን መንገድ በአካባቢው የሚኖረውን አካል እንደሚያገኝ ሊያውቅ ይገባል። ይህ አይነት ተግባር ግን ጥንቃቄን የሚሻ ጉዳይ ነው። ሠርጎ በገባም ይሁን ውስጥ ባለ ድብቅ ኃይል ጥቃት እንዳይሰነዘር ምስጢራዊነቱም ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

አንድ ገጠር ያለ ሰው ዐዋጁን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል በማሰብ አገልግሎት ላይ ሊውል ይገባል። የከተማውን ነዋሪ ብቻ ከግምት ያስገባ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ሕዝብ ሳያልቅ በትንሽ መስዋዕትነት ድልን ለማግኘት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ መንግሥት ቢያውቅም፣ ከጎን እንዲሰለፍ የሚጠየቀው ሕዝብም ዓላማውን እንዲረዳው የቅስቀሳና የማሳወቅ ሥራው መቋረጥ እንደሌለበት ግልጽ መሆን ይኖርበታል።

የዐዋጁን ይዘት በተመለከተ፣ ለምሳሌ ከፍተሻ ጋር በተገናኘ ማን ማን ፈታሽ እንደሆነ ሕዝቡ ሊያውቅ ይገባል። ከቀድሞ ሥርዓት ጋር ቁርኝት ያላቸውንም ሆነ ሰንሠለታቸው ያልተበጠሰን ሕዝቡ ራሱ ስለሚያውቅ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የጠቋሚ ማንነት መደበቁ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ውጤታማ እንዳይሆን የሚፈልጉ አካላት ተቀባይነቱን ለማሳጣት አላግባብ ሊሠሩበት እንደሚችሉም ሊታሰብ ይገባል። አብሮ የኖረ ጎረቤት ሊያደርግ የሚችለውን በመስጋት ጥቆማ የሚሰጥ የመኖሩን ያህል፣ ድርጊቱ በሕዝብ መካከል አላስፈላጊ ልዩነትን በዘላቂነት እንዳይፈጥር ይታሰብበት። በሰው መካከል አለመተማመን መኖሩ ሕብረት እንዳይኖርና በአስፈለገ ጊዜ ተባብሮ እንዳይሠራ ሊያደርግ ስለሚችል ከግንዛቤ ማስገባት ግድ ይላል።

የጦር መሣሪያን በተመለከተ ኹሉም በኹለት ቀን እንዲያስመዘግብ መደረጉ ቢታወቅም የመዝጋቢዎቹን ማንነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ የተመዘገበበት ሠነድ የሚያዝበት መንገድም ምስጢራዊ መሆን ይገባዋል። በጠላት እጅ እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘራፊም ሆነ ለአጥቂ በር እንዳይከፍት መደረግ አለበት። የሚመዘገበውን የጦር መሣሪያ ዓይነት በተመለከተም በመግቢያው ትርጓሜ ላይ የተቀመጠው ሊዘረዘር ይገባዋል። በደፈናው ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ሲባል ብዙ የቤት ቁሳቁስን ሊያካትቱ ስለሚችል ቢብራራ መልካም ነው። ጦር፣ ጊሌና ቆንጨራን የመሳሰሉ ባህላዊ መገልገያዎች የት እንደሚመደቡ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

ሰው ከስህተቱ መማር እንዳለበት ይታወቃል። መንግሥትም በራሱ አካላትም ሆነ በሕዝብ ዘንድ የተፈጸመ ስህተት መልሶ እንዳይደገም፣ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰዱ በጦርነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ ወቅትም ይጠበቃል። “ጦርነት ላይ ሆኖ ፈረስ አይቀየርም” የሚል አባባል የተለመደ ቢሆንም፣ የለገመም ሆነ የደከመ ፈረስን በተሻለ መቀየር እንደሚገባ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል። የጦር መሪዎችም ሆኑ መደበኛው አደረጃጀትን የሚመሩ ግለሰቦች ቢያንስ ከተፋላሚው ወገን እኩል መንቀሳቀስ ካልቻሉ አቅሙ ባለው ሊተኩ ይገባል።
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አንዱ ዓላማ ጊዜያዊና ለ6 ወር የሚቆይ የዕዝ ሰንሠለትን መፍጠር እንደመሆኑ ከሕገ-መንግሥቱ አንድ አንቀጽ በስተቀር ሌሎቹን ሊያግድ እንደሚችል ተጠቅሷል። ይህ መንገድ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊም ሆነ የፖለቲካ መብትን ለተወሰነ ጊዜ በማገድ ለጋራ ዓላማ ሲባል ጥቅም ላይ መዋሉን አዲስ ማለዳም ትረዳለች።

ይሁንና በዐዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው ለግል ዓላማቸው ማስፈጸሚያም ሆነ ለሌላ ፍላጎት የሚጠቀሙበት ከተገኙ እንደሚቀጡ ተደንግጓል። ይህ እንዳለ ሁኖ ሕብረተሰቡ በአተገባበሩ ላይ ችግር ካስተዋለ፣ የአስፈጻሚውን አካል ተቀባይነትን በማይቀንስ መልኩ ጥርጣሬውንም ሆነ ጥቆማውን በምስጢር ሳይፈራ ሊያደርስ የሚችልበት መንገድን አስቀድሞ ሊያውቅ ይገባል።

ዐዋጁ ተፈጻሚ የሚሆነው በመላ ኢትዮጵያ እንደሆነ ቢጠቀስም፣ በመምሪያ ዕዙ እንዳስፈላጊነቱ የሚቀነሱም ሆነ የሚያተኮርባቸውን የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመመሪያ ያሳውቃል ተብሏል። ይህ ተገቢ ቢሆንም፣ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖር የሚያደርገው ይህን ዐዋጅ ተፈጻሚነት እንዳይቀንሰው ሊታሰብበትና በጥንቃቄ ሊወጣ እንደሚገባ ግልጽ ነው።

ሕብረተሰቡ ዐዋጁን ለጋራ መጠቀሚያ እንጂ የግል ቂሙን መወጫ እንዲሁም፣ የተማረረበትን ነጋዴ መበቀያ እንዳያደርገው የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ጎን ለጎን መሠራት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ዐዋጁ ማስፈራሪያ ሳይሆን ማስገንዘቢያና ማስጠንቀቂያ እንደመሆኑ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ለተግባራዊነቱ እንዲረባረብ ሊሠራ ይገባል። ከሰው ኃይል ምልመላ ጀምሮ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ችግሩን ለመቅረፍ እኩል እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደሕዝብ ችግራችንን ለማለፍ በአንድንት የምንንቀሳቀስበት ወቅት እንደመሆኑ፣ የውጭ ጣልቃ ገቢዎችንም ሆኑ ሰርጎ ገቦችን ለማጽዳት ቅድሚያ ተሰጥቶ መሠራት አለበት። በጭቃ የተለወሰ ጫማ አድርጎ ቤትን ማጽዳት እንደማይቻለው፣ በቅድሚያ ራሳችንን ካጸዳን በኋላ ወደ አካባቢያችን ማምራት እንደሚኖርብን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here