መሱድ ገበየሁ ይባላሉ። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያ ናቸው። ጥቅምት 24፣ 2014 በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት በጋራ ይፋ ስለተደረገው ሪፖርት ከአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ስለ አጠቃላይ የሪፖርቱ ይዘት እንዲሁም ስለዓላማውና ስለሚያስከትለው ውጤት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ያወጡትን ሪፖርት እንዴት ገመገሙት?
እንደሚታወቀው ከዓመት በፊት ጀምሮ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በሰሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ኃይል በፈፀመው ጥቃት መነሻነት የሕግ ማስከበር ጦርነት ተከትሎ ነበረ። አሁን ድረስ በተለያዩ የአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች የተስፋፋውን የህወሓት እንቅስቃሴን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች እንዳሉ ሆነው፣ በመጀመሪያዎቹ ግጭቱ በተቀሰቀሰባቸው ወራት ውስጥ በጣም መጠነ ሠፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው ነበር። የጦር ወንጀልም ሆነ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደተፈጸመ የሚያስረዱ ተግባራት መኖራቸውን በአገር ውስጥና በውጭ አገራትም ያሉ ሚዲያዎች ይዘግቡ ነበር። በተለይ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሰሜኑ አካባቢ የሚሄዱ የሰብዓዊ ድጋፎችን አስተጓጉሏል፤ ረሀብንም እንደጦር መሣሪያ ተጠቅሟል የሚሉ በርካታ ክሶች ነበሩ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ በተደጋጋሚ ማዕከላዊው መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁሙን ከማድረጉ በፊት በተደጋጋሚ የተለያዩ አለም ዓቀፍ ጫናዎችና ማዕቀብን የመሳሰሉ ተግባራት ሲደረጉ እንደነበረ የሚታወቅ ነው።
የዚህ ኹሉ ጫናን አንድ መልክ የሚያሲዘው ተብሎ የተገመተው በዚህ ሒደት ውስጥ ማን ሚና ነበረው የሚለውን ምርመራ ማድረግ ነው። ይህን በሚመለከት የተባበሩት መንግሥታት የሠብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ሆነው ይህንን በተለይ በትግራይና በተወሰኑ የአማራና አፋር አካባቢዎች የሰብዓዊ ክፍተቶችን ምርመራ ለማድረግ የጋራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ፣ ከጥቅምት 24፣ 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም እስካደረገበት ሰኔ 21 2013 ድረስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ሲደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።
እንደአጠቃላይ ይህን የምርመራ ግኝት ስናየው፣ ብዙ አይነት የሰብዓዊ መብት ተጠያቂነትን የሚያመጡ ከባድ የወንጀል ተግባራት እንደተፈጸሙ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ለዛም የኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ኃይል፣ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚሊሻዎችና ፋኖዎችን የመሳሰሉ በአንድም ይሁን በሌላ በሒደቱ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸውና የተጠያቂነት ደረጃቸውም እንደተሳትፏቸው ዝቅ ወይም ከፍ ይላል። በኹሉም ወገን ያሉት በድርጊቱ የተሳተፉት ኹሉ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የሚያስቀምጥ ሠፊ ወደ 165 ገፅ የሆነ ሪፖርት ነው። ስለዚህ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው። ከዚህ ቀደም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ የነበረበት የተለያዩ መነሻዎች ያሉዋቸው ግጭቶች ሲደረጉ እንደነበር የሚታወስ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ገለልተኛ የሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ምርመራ ያድርጉ የሚል ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር። ከዚህ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ኢህአዴግ፣ ፍላጎት ስላልነበረውና ለመብት ጥሰቶችም ብዙ ተቆርቋሪነት አልነበረውም። መንግሥታዊ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ስለነበሩ ከዚህ በፊት በነበረው ሥርዓት የሚፈጸሙት ምርመራ ሳይካሄድባቸው ቆይቷል።
የአሁኑ ምርመራ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ታሪክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ እንዲያደርጉ መንግሥት ጋብዞና ፈቅዶ፣ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ተሳትፎ ካላቸው ጋር በጋራ በመሆን በርካታ የሆኑ ውይይቶችንና ስብሰባዎችን የመሳሰሉትን በማድረግ ነው ይህንን ሪፖርት መጨረሻ ላይ ይፋ ያደረጉት።
በዚህ ሒደት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ በግጭት ውስጥ ተጎጂ የሆኑትን ቤተሰቦች ምስክሮችን፣ የተለያዩ የሠነድና የቁስ ማስረጃዎችን ኹሉ ተጠቅመው ይፋ ያደረጉት ሪፖርት ነው። ሪፖርቱ ለአገራችን የሰብዓዊ መብት መከበር ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ በተለይ በግጭቱ የተሳተፉትን ኹሉንም አካላት የተሳትፏቸው መጠን እንደየሁኔታው የተለያየ ይሁን እንጂ፣ ተጠያቂ ናቸው የሚል ማምጣቱ በራሱ የሪፖርቱን ታአማኒነት ከፍ ያደርገዋል። ከዛ በመለስ ሒደቱ በራሱ መጀመሩ የሚበረታታ ነው። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረገውን ጅማሮ ማመስገን እፈልጋለሁ።
ጅማሮውን በማጠናከር ከሰኔ 21 በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ወደ አማራና አፋር ክልሎች ያሉ የተለያዩ አካባቢዎችን ለመያዝ ህወሓት ያደረገው መስፋፋትን ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ተሰምቷል። ለምሳሌ፣ ከቀናት በፊት ኮምቦልቻ ላይ ከ100 በላይ ንጹኃን ወጣቶችን ህወሓት ስለመጨፍጨፉ ሪፖርት ቀርቧል። እነዚህ አይነት ተግባሮችን በሚገባ ሠንዶ ከአሁኑ ጥናት ባልተናነሰ እንደውም በተሻለ ሁኔታ አሰናድቶ ለሚመለከተው የፍትሕ አካላት በማስረከብ ተጠያቂነት እንዲመጣና ወደፊት እንዲህ አይነት ተግባር እንዳይደገም መደረግ አለበት።
ግጭቶቹ በተቻለ መጠን በቶሎ የሚቋጩበትን ሁኔታ ስለሚያመላክትና ምክረ ሐሳብ ስለሚያቀርብ፣ ዓለም አቀፉም ማህበረሰብ ደግሞ ችግሮቹ መፍትሔ የሚያገኙበትንና ከዛም በበለጠ በዚህኛው ምርመራ የተገኙትን ምክረ ሐሳቦች ወደ ተግባራዊነት የሚመጡበትን ሁኔታ ሪፖርቱ ይጠቁማል። ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ፍትሕ እንዲያገኙ፣ ተጎጂዎች እንዲካሱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ዘላቂነት ያለው ሥርዓት የሠፈነበትና ኹሉም ሰው እንዲህ ዓይነት የደህንነት ስጋት የማይኖርበት ሆኖ እንዲኖር የአሁኑ ሪፖርት አስተማሪ እንደሚሆን አምናለሁ።
ከዚህ በተጨማሪ ይህ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መንግሥትም ይህንን ሪፖርት ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስተያየቱን አውጥቷል። የሪፖርቱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማይስማማበት እንደሚሆን ቢገልጽም፣ እንደአጠቃላይ ሪፖርቱን እንደሚያከብረው፣ ሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ግኝቶችን መንግሥት አስቀድሞ በራሱ መንገድ ሔዶባቸው ለፍረድ ያቀረባቸው እንደሆኑ፣ አንዳንዶቹም ጥፋተኛ ሆነው እየተቀጡ ያሉ እንዳሉ በበጎ መንገድ መሄዱን መግለጹ ይታወሳል።
ትልቁ ነገር መንግሥት መፍቀዱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሪፖርቱም ዕውቅና መስጠቱ ነው። ከሚመለከታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በጋራ የሚነጋገሩትና ግልጽ የሚያደርጉት እንደተጠበቀ ሁኖ፣ ከመንግሥትም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ በተለይ በዚህ ሒደት የተሳተፉትን መንግሥት ተጠያቂ ማድረግ ስላለበት ነው። ለምሳሌ ሪፖርቱ ላይ ለኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥት የተሠጡ ምክረ ሐሳቦች አሉ። ይህ እንግዲህ ለምሳሌ የአማራ ልዩ ኃይሎች ተሳትፈውባቸዋል የተባሉ፣ የትግራይ ልዩ ኃይሎች ሰርተውታል የተባሉትን በተመለከተ በመንግሥት ደረጃ ስለሆነ ሪፖርቱ የሚቀርበው፣ ያጠፉትን ለሕግ ለፍትህ የማቅረብ ግዴታው የመንግሥት ስለሆነ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የሚወስደውም እሱ ስለሆነ በአብዛኛው ሪፖርቱ ለእሱ ነው።
በአገር ውስጥ ባለው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በማንኛውም አካላት የተፈጸሙ ቢሆኑም ወደ ሕግ መቅረብ አለባቸው። በመከላከያም ይሁን በተለያዩ አካላት የተፈጸሙትን እየለዩ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የሕግ ማዕቀፎች አጥፊዎቹን አቅርቦ ተጠያቂ እንዲያደርግ ሪፖርቱ ይጠቅማል። የኤርትራ መንግሥትም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ተከትሎ፣ ሪፖርቱ ላይ በቀረበው ተጠያቂነት ልክ አጥፊዎችን ወይም ተጠርጣሪዎችን ወደሕግ እንዲያቀርብ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ ሒደቱ አጀማመሩ ጥሩ ስለሆነ ሊበረታታ ይገባል። ምክረ ሐሳቦቹም ወደተግባር እንዲመጡ ተጠያቂነቱም ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረጉ በኩል ሲቪል ማኅበራት፣ ሚዲያው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሌሎችም ወዳጅ አገራት በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጥሩ ጅማሮ ወስደው ተጠያቂነትና ታአማኒነት ያለው ሥርዓት እንዲመጣ ፣ እንዲሁም ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልሆነና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ኹሉም እንዲሠሩ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማድረግ እፈልጋለሁ።
መንግሥት ወደሕግ ቀርበዋል ስላላቸው ተጠርጣሪዎች በሪፖርቱ ያልተካተተው ለምንድን ነው?
ሪፖርቱ በጊዜ ደረጃ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ወቅት አንስቶ የተናጥል ተኩስ አቁም እስከታወጀበት ድረስ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ነው የሚያካትተው። የት እንደተፈጸሙ፣ ማን እንደፈጸማቸው፣ የጉዳቶቹ መጠን ምን ያህል እንደሚደርስ በዝርዝር የሚያሳይ ነው። በተቻለ ኹሉንም የያዘ ሲሆን፣ በመሀል ተይዘው ለሕግ የቀረቡ የተፈረደባቸውም አሉ።
ጉዳዩ አንድ ዓመት የሆነውና አሁንም በሒደት ላይ ያለ ስለሆነ አሁንም በሕግ የሚፈለጉ አሉ። በተለይ ወደ አማራና አፋር ክልል ከመስፋፋቱ ጋር በተገናኘ በአሸባሪው ህወሓት በኩል ጥሰቱን እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ስላሉ እነሱን ይዞ ለሕግ ማቅረቡ ቀጣይ የሚቀር ሥራ ነው የሚሆነው።
በአጠቃላይ፣ ሪፖርቱ የመንግሥትን ጅማሮ የሚያበረታታ ሆኖ በሪፖርቱ ላይ በቀረበው ልክ ኹሉም ተጠያቂ እንዲሆን ጥሪ የሚያደርግ ነው። ሪፖርቱ እነዚህ ተከሰዋል እነዚህ ደግሞ አልተከሰሱም ብሎ ማካተት አይጠበቅበትም። መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉት ማንም ይሁኑ እንደተሳትፏቸው ልክ ለፍትሕ ማቅረቡ አንድ ነገር ነው።
አሁን የሚጠበቀው ሪፖርቱ ላይ በተቀመጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት እነዚህን ለሕግ አቅርቤያለሁ፣ እነዚህን ላቀርብ ነው ማለት ነው። አብዛኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚያወጣው ሪፖርት ላይ እንደምናየው፣ መንግሥት በራሱ በፌዴራልም ሆነ በክልል ፖሊሶች እንዲሁም በደኅንነት ተቋማት የተያዙ ማስረጃዎችን ሠንዶ እንደጥፋታቸው ወታደራዊ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ወታደራዊ ፍርድ እንዲያገኙ፣ ሌላው መደበኛ የወንጀል ተግባር በመፈጸሙ የተጠረጠረ ደግሞ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እንዲቀርቡ ማድረግ ነው። ስለዚህ እስካሁን የተሰሩትን አሰናድቶ፣ መስተካከል ያለባቸውንም አሻሽሎ፣ የቀረውንም ለይቶ ለሕዝብና ለጋራ የምርመራ ግብረ ኃይሉ ቢያሳውቅ ቅቡልነቱንም ስለሚያሳድግ ጥሩ ነው የሚሆነው።
አንዳንዶቹ ጥሰቶች ከባድ እንደመሆናቸው፣ ለምሳሌ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል የሚባሉት ዓለም አቀፍ ወንጀል ቢሆኑም በሕጋችን የተካተቱ በመሆኑ ጉዳዩን ለማየት የሕግ ማዕቀፉ አለ። ነገር ግን፣ እነዚህን ከባድ ወንጀሎች ስናይ ከሌሎቹ በተለየ ሥርዓት መሄድ ይጠበቃል። ገለልተኛ የሆነ ታማኝነት ያለው ሥርዓት መኖሩን መንግሥት ቢያረጋግጥ መልካም ነው።
ይህን በተመለከተ የፍትሕ ሚኒስትሩ የሚመሩት ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ የሚያደርግና እስካሁን የተሠሩትን ሥራዎች የሚያይ ግብረ ኃይል እንደተቋቋመ ተነግሯል። ግብረ ኃይሉ ጉዳዩን ተከታትሎ ኹሉንም መልክ መልክ አስይዞ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ እገምታለሁ።
ዘር ማጥፋትን በተመለከተ የሚሰጡ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ። እርሶ ጉዳዩን እንዴት ያዩታል?
የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ማንነት ላይ ያተኮሩ ስልታዊ የሆኑ ግድያዎች እንደነበሩ ሪፖርቱ ላይ ተካቷል። ይህ በሪፖርቱ ላይ የተገለጸ ስለሆነ ተሳታፊ የነበሩ ለሕግ መቅረብ አለባቸው የሚለውን ምክረ ሐሳብ እኛም የምናምንበት ነው። በአጠቃላይ እነዚህ ነገሮች ላይ የተሳተፉትን ለፍትሕ ማቅረብ የሕግ አካላት ኃላፊነት ነው የሚሆነው። ከአገር የወጡና ጎረቤት አገርም ያሉ ስላሉ ኢንተርፖልን ከመሳሰሉ ጋር በመተባበር በተግባሩ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ማናቸውንም አካላት ቢሆን ወደ ሕግ ማቅረብ ይገባል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የኹሉም ሕብረተሰብ ትብብር ያስፈልጋል። ተጠርጣሪዎችን በመጠቆምም ሆነ ማስረጃ ለሚመለታቸው አካላት በማቅረብ ተጠያቂነትን ማምጣት አለባቸው።
ሪፖርቱ በጋራ የተዘጋጀበትና አሁን እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
በሪፖርቱም እንደተመላከተው ከባድ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው እንደነበረ ነው ስንሰማ የቆየነው ። ብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይሄን ሲያሳዩ ነበር። እንደውም አንዳንዶቹ ሪፖርቱ ላይ ያልተካተቱ ተግባራት በመንግሽት ተፈጽመዋል በማለት ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ነበር።
እንዲህ አይነት ጥቆማዎች ሲደርሱ መመርመርና ውጤቱን ይፋ ማድረግ የኮሚሽኑ ኃላፊነት ነው። ብዙዎች ቅሬታ ያቀርቡ ስለነበር መንግሥት እውነቱ የትኛው ነው የሚለውን በእናንተው እና በእኛ ተመርምሮ ለሕዝብ ይፋ ይሁን ብሎ መንግሥት ፈቃደኛ ስለሆነ፣ በዚህ አግባብ ነው የታየው።
ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሥልጣን አለው፤ ሥልጣኑ ግን መንግሥት ሲፈቅድ ብቻ ነው። መንግሥት ፈቅዷል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መንግሥት ፈቀደም አልፈቀደም፣ በራሱ በመቋቋሚያ ዐዋጅ የተሰጠው ሥልጣን ነው።
ከጊዜ አንጻር የሚለው ደግሞ፣ ይህ ሪፖርት የሚሸፍነው ከጥቅምት 2013 እስከ ሰኔ 21/2013 ድረስ ነው። ሰኔ 21 ማለት አሁን ሦስት ወር ሆኖታል። ሪፖርቱ ከተጠናቀቀ ደግሞ ዋናው ቁልፉ ሪፖርቱን መሥራት፣ ዶክመንት ማድረግ ሳይሆን ሪፖርቱን በጊዜ ይፋ ማድረግ፣ ቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። ምክንያቱም፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ተጎጂ የሆኑና የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰዎች ፍትሕን እየጠየቁ ነው። አሁንም ቢሆን አንዱ ምክረ ሐሳብ ተጎጂዎች ሒደቱን በቅርበት የሚከታተሉት፣ የሚያውቁት ግልጽና ተጠያቂ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት እንዲመጣ ይመክራል። ይህ አንዱ እውነቱን የማወቅ መንገድ ስለሆነ ማለት ነው።
ስለዚህ ከጊዜም አንጻር ሪፖርቱ የሚሸፍነው እስከ ሰኔ 21 ስለሆነ፣ ሰኔ 21 እንዳለፈ በአንድና ኹለት ወር ውስጥ የመተንተኑ/የወረቀት ሥራው አልቆ ይፋ የሚደረግበት ነው እንጂ ከሌላ ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ አይደለም።
አሁን በወቅታዊው ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንደመታወጁ፣ ሪፖርቱ ውጤታማ ይሆናል ይላሉ?
ሪፖርቱ የሚያመላክተው በዛ ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ነው። እንዳልኩት መንግሥት ከዚህ በፊት ባለው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ተጠያቂ ያደረጋቸው፣ የያዛቸው፣ ጠርጥሮ እያጣራ ያለ፣ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉ፣ ጥፋተኛ የተባሉ፣ ወደፊት የሚፈለጉም አሉ። ስለዚህ አሁን ካለው የሕግ ማስከበር እና አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ ራሱን ችሎ የሚሄድ ነው። ለዚህም ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም መንግሥት ግልጽ አድርጓል።
በኹለተኛ ደረጃ፣ አሁን ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንደውም የበለጠ በዚህ ሒደት ውስጥ በአንድም በሌላም የተሳተፉ ብዙ ሰዎችን፣ ይህን ጊዜ ተጠቅሞ ለፍርድ ለማቅረብ ይረዳል የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ። ምክንያቱም ጦርነቱ እየተስፋፋ ሄዶ አሁን አብዛኛውን የአማራና አፋር ክልል ለመያዝ ህወሓት፣ በፕሮፓጋንዳም፣ በመሬት ላይ በሥራም ብዙ ጥፋት እየደረሰ ነው። ይህ ጉዳይ የአገር ሕልውናን የሚፈታተን እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያው ሥራ ይህን አጥፊ፣ ወራሪና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በጣም ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ የሚፈጽም ኃይልን ሥርዓት ማስያዝ፣ ይህን መስፋፋቱን መግታትና ይህን የሚመሩና የሚያስተባብሩ ሰዎችን ለፍትሕ ማቅረብ አንድ ሥራ ነው።
እስከ ሰኔ 21 ተፈጸሙ ለተባሉ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች አሁንም በተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢ በመስፋፋት፣ አመራር እየሰጡ ያሉትም ስለሚገኙበት፣ በዚህ መልክ ነው የሚታየወ።
ስለዚህ፣ እኔ አሁን የወጣው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በተለየ ሁኔታ በዚህ ላይ ጫና ይፈጥራል ሳይሆን ሒደቱን በማፋጠን፣ በአንድም በሌላም የሚፈለጉትን በሙሉ ለፍትሕ ለማቅረብ መንግሥት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የሚሠራው ስለሆነ፣ የበለጠ ምክረ ሐሳቦቹን ወደ ተግባር ለማምጣት ዕድል ይሰጣል የሚል ሐሳብ አለኝ።
ይብራሩ የተባሉትስ በቶሎ ተብራርተው ምላሽ የሚያገኙ ይመስልዎታል?
እሱን በሚመለከት መንግሥት የማልቀበላቸው አሉ፤ በአጠቃላይ ደግሞ ጥሩ ጅማሮ ነው፣ በተለይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስራብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀምና የመሳሰሉ ክሶች ይቀርቡ ስለነበር፤ ይህ አለመሆኑ የምናበረታታው ነው እናመሰግናለን ብለዋል። እንዳልኩት ግብረ ኃይል መቋቋሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል። መንግሥት የሚብራሩትን ያብራራል፤ የሚጠየቁትን ይጠይቃል። እስከአሁን የወሰደውን ዕርምጃ ይፋ ያደርጋል።
መንግሥት ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ ብሎ ኮሚሽኑ እንዲያብራራለት የተጠየቀውስ?
ኮሚሽኑም ያብራራል፤ ግዴታቸው ነው። ሪፖርት ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ሪፖርቱ ላይ ግልጽ ያልሆኑ፣ በማስረጃ መደገፍ ያለባቸው ካሉ እሱን በማስረጃ እያስደገፈ ያብራራል። የጋራ ምርመራ ሲሆን ይህ ግዴታ ነው። መንግሥትም ግልጽ ያድርጋቸው የተባሉ ነገሮች ካሉ፣ ግልጽ ያደርጋል። ከመንግሥት ግን በዋናነት ተጠያቂነትን ማምጣት፣ በወንጀል የተሳተፉ ሰዎችን ለፍትሕ ማቅረብ፣ ተጎጂዎችን ካሳ መስጠት የመሳሰሉት ነገሮች ናቸው የሚጠበቁት።
ይህን ግኝት መሠረት አድርጎ የሚቋቋመው ግብረ ኃይል እነዚህን ሥራዎች ነው የሚሠራው፤ እንጂ ኮሚሽኑማ ግዴታም አለበት። አንዱ የስምምነቱ አካል ተባብሮ መሥራት ነው። ትብብር ነው። መንግሥት ትብብር ካላደረገ፣ ፈቃድ ካልሰጠ ውጤታማ የሆነ ምርመራ ማድረግ ስለማይችሉ፣ ግልጽነት የላቸውም፣ መንግሥት ቅሬታ(ሪዘርቬሽን) አለኝ ያለውም ለዛ ነው።
እነዛ ቅሬታዎች ደግሞ የመጡት አንድም ግልጽ ካለመሆን ነው። ኹለተኛ የቀረቡ ማስረጃዎች የተዓማኒነት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መንግሥት እነዚህ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ እፈልጋለሁ ያለውን የጋራ ምርመራ ቡድኑ ለመንግሥት ማብራራት አለበት። መንግሥትም ደግሞ የጋራ የምርመራ ቡድኑ ይህን ያድርግ ብሎ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ማድረጉን ማሳየት አለበት።
መፍቅድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሀብት ወጥቶበት፣ ብዙ ጊዜ ባክኖበት፣ በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈ ምርመራ እንደመሆኑ መጠን፣ ይሄ የተጠያቂነት ሥርዓት ለመንግሥትም፣ መንግሥት እያመጣ ላለው ጠንካራ ተቀባይነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት ግንባታም አንድ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ የሚሰጥ ነው። በዛው ልክም ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚጠብቁትና የሚጠይቁት ጉዳይ እንደመሆኑ፣ በዚህ ላይ መንግሥት ብዙም ችላ ይለዋል፣ ትኩረት አይሰጠውም የሚል ዕምነት የለኝም። በጣም አዎንታዊ የሆነ ዕርምጃ ተወስዶ፣ በአገራችን የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ምንአልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻለ፣ ፍትሃዊነት ያለው ሒደት እንደሚሆን ነው ተስፋ የማደርገው።
ሌሎች ግጭቶችን በተመለከተ፤ የኦነግ ሸኔ ያደረሳቸው ጥፋቶችም አሉ። እነዚህ በሪፖርቱ መካተት አልነበረባቸውም?
ግልጽ ነው። ሪፖርቱ የሚሸፍናቸው ቦታዎች የታወቁ ናቸው፣ የሚሸፍነው ጊዜ የታወቀ ነው። የሚሸፈኑት ጉዳዮች ደግሞ በጋራ የምርመራ ቡድኑ ተፈጥሮአዊ ሥልጣንና ኃላፊነት ውስጥ የወደቁ ናቸው። ስለዚህ ወለጋም በለው በቤኒሻንጉል፣ ሌሎችም አካባቢዎች ያሉት የቡድኑ የጥናት ወሠን (ስኮፕ) ውስጥ የተካተቱ አይደሉም።
እንደውም በወቅቱ እኛም ጥሪ ስናደርግ የነበረው በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስላሉ፣ በምዕራብ ኦሮሚያም፣ በቤኒሻንጉልና ሌሎችም አካባቢዎችም፣ እነዛንም አብሮ በዚህ ተጠቃሎ ምርመራ ቢደረግ ብለን ነው። ሌላው መንግሥት የአንድ ወገን ተኩስ አቁሙን ተከትሎ በተፈጠሩ ሰፋፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም የዚህ የጋራ የምርመራ ቡድን የምርመራ አካል ቢሆኑ ወይም ደግሞ የዚህኛው ጥናት አካል ሁነው ይህንንም የሚሸፍንበት፣ ማለትም እስከ መስከረምና እስከ ቅርብ ጊዜ ያሉትን ሸፍኖ አልያም ኹለተኛ ዙር ምርመራ የሚደረግበትን ዕድል እንዲመጣ ብለን የምንጠይቀው ነው። ስለዚህ ይህ የዛኛው አካል ስላልሆነ በዚህ ሪፖርት እንዲካተት አይጠበቅም።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014