አቤቱታ የቀለበሳቸው የምርጫ ውጤቶች

0
800

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አጠቃላይ ምርጫውን በአንድ ዙር ማካሄድ ባለመቻሉ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2014 ካካሄደ በኋላ፣ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ባሳለፍነው መስከረም 20/2014 አካሂዷል። ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ዙር ማካሄድ ያልቻለው በጸጥታ ችግር፣ በሕግ የተያዙ ጉዳዮች ዕልባት ባለማግኘታቸው እና የድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ችግር በማጋጠሙ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ኹለተኛው ዙር ምርጫ የተካሄደው በሱማሌ እና ሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ ሲሆን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔና በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ነው። መስከረም 20 በተካሄደው ምርጫ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል። በዚህም ብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ ሆኗል።

ይሁን እንጂ፣ መስከረም 20 በተካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ድምጽ የተሰጠባቸው ምርጫ ክልሎች ላይ በቀረበ አቤቱታ፣ የምርጫ ውጤት ይፋ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

ቦርዱ ድምጽ አሰጣጥ ተከናውኖባቸው፣ ነገር ግን በአቤቱታ ምክንያት ውጤታቸው ይፋ ያልተደረጉ የምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ባለፈው ሰኞ መረጃ አውጥቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሱማሌ፣ በሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ድምጽ አሰጣጥን በመስከረም 20/2014 ማከናወኑን የጠቆመ ሲሆን፣ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የአቤቱታዎች ዝርዝር ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ይፋ ያልተደረጉ የምርጫ ውጤቶች እንደነበሩ አስታውሷል። ቦርዱ የነበሩ አቤቱታዎችን በዝርዝር በማየት በምርጫ ክልሎቹ የተከናውነው የድምጽ አሰጣጥ እና ቆጠራ ላይ ውሳኔዎች ሰጥቷል።

በዚህም ሙሉ ምርጫ በተደረገበት ሱማሌ ክልል፣ ሙሎሙልቄ ምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት) በኹሉም ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመዝገብ ላይ የፈረሙ መራጮች እና በሳጥን ውስጥ በነበሩና ወድቀው በተገኙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች መካከል፣ እንዲሁም ለምርጫ ክልሉ በደረሰው አጠቃላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት እና በድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ እና ከሳጥን ውጪ ካለው ጋር ሲነጻጸር ሊታለፍ የማይችል የቁጥር ልዩነት በመገኘቱ፣ የድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወን መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል።

በምርጫ ክልሉ የተወዳደሩ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች በድጋሚ ቆጠራውን የሚታዘቡ ወኪሎች እንዲልኩ ጥሪ ማድረጉንም ቦርዱ አክሏል። ጅግጅጋ ከተማ የምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት) 26 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለአንድ ፓርቲ ድምጽ እንዲሰጥ ተደርጓል የሚለው እና በ13 የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች መታዘብ አለመቻላቸው በመረጋገጡ ይህም ከውጤቱ ድምር ጋር ሲታይ ውጤት የሚቀይር መሆኑ ስለታመነበት ቦርዱ የድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን መወሰኑን ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ደግሞ በሌሞ 01 የምርጫ ክልል (የተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት) ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል፣ መራጮች ላይ ወከባ እና ማስፈራራት፣ ወኪሎች እንዳይታዘቡ ከጣቢያ ማባረር፣ መስፈርት የማያሟሉ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ማድረግ፣ መራጮች በምርጫ አስፈጻሚዎች ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ፣ የምርጫ ምስጢራዊነትን አለመጠበቅ፣ የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ እነዚህ ጥሰቶች መፈጸማቸው ምስክርነት በመቅረቡ ምርጫው እንዲደገም ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል።

ምስቃን እና ማረቆ 2 ላይ፣ የአካባቢው ሚሊሻ ምርጫ ጣቢያ አካባቢ ማስፈራራት፣ መራጭ እንዳይሳተፍ ማድረግ፣ የመራጭ ቁጥር እና ካርድ የወሰደ ቁጥር አለመጣጣም፣ ሕፃናት እንዲመርጡ ማድረግ፣ የአመራር ቤተሰብ በየጣቢያው ታዛቢና መራጭን ማስፈራራት፣ አመራሮች ደጋግመው መምረጥ፣ ከምርጫ ማግስት ግለሰቦችን ከመንግሥት ሥራ ማገድ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩን ማሰር፣ የፓርቲ አባላትና ታዛቢዎችን ማስፈራራት፣ በምርጫው ቀን ከግማሽ ቀን በኋላ በተፈጠረ ግጭት መራጮች የፈለጉትን መምረጥ አለመቻላቸው፣ ታዛቢዎች ሕይወታቸው ሥጋት ላይ በመውደቁ ምክንያት በፖሊስ ዕርዳታ ጭምር ከምርጫ ጣቢያ መውጣታቸው የቀረቡ አቤቲታዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ አቤቱታዎች አብዛኛዎቹ በምስክር እና በማስረጃ በመረጋገጣቸው፣ በምስቃና ማረቆ 02 ምርጫ ክልል ላይ በምርጫ ቀን በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያ ድምጽ ሰጨዎችን የሚያስገድድ የኃይል ተግባር እንደነበር በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ የድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን ተወስኗል። በምስቃንና ማረቆ 2 የምርጫ ክልል በድጋሚ ምርጫ የተደረገበት ሲሆን፣ ቦርዱ የድጋሚ ምርጫ ሲወስን ይህ ኹለተኛው መሆኑን ጠቁሟል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሠራቻቸው ምርጫ ማለዳ ዘገባዎች፣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ በታዛቢነት የተሳተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምርጫ ትዝብት ግኝቶችን በዘገበችባቸው ዕትሞቿ፣ ቦርዱ ድጋሚ ምርጫ እና ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ ውሳኔ የሰጠባቸውን ምክንያቶች ታዘቢዎቹ እንደ ክፍተት አቅርበዋቸው ነበር።

ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ እስከ ኹለተኛው ዙር ምርጫ ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ታዛቢዎችን አሰማርተው ምርጫውን ከታዘቡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ከቀዳሚዎቹ ይመደባል። ኢሰመጉ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ትዝብቱ፣ በደቡብ እና በሱማሌ ክልል ከታዘባቸው ከፍተቶች መካከል የምርጫ ታዛቢዎችን እንዳይታዘቡ የማድረግ ዝንባሌ መኖሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢሰሙጉ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው ችግሮች መካከል በምስጢራዊ ድምጽ መስጫ ቦታዎች አካባቢ ድጋፍ መስጠትና ከምርጫ አስፈጻሚዎች ውጭ ሒደቱን የሚያስተባብሩና ጣልቃ የሚገቡ አካላት ሕገ-ወጥ ተሳትፎ ዋነኛው ነው ተብሏል። በተለይም የኢሰመጉ ታዛቢዎች በተሠማሩባቸው በጅግጅጋ ከተማ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ሕጋዊ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ አካላትና “በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች” በድምጽ መስጫ ጣቢያ ውስጥ መራጮችን ሰልፍ በማስያዝ፣ መራጮችን ተጽዕኖ ውስጥ በሚከት ሁኔታ በምስጢራዊ ድምጽ መስጫ ቦታዎች ላይ በማስተባበር ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ተጠቁሟል።

በድምጽ አሰጣጡ ሒደት ላይ ከታዩ ጉልህ የሕግ ጥሰቶች መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዕድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሱ ሕፃናት በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በምርጫ ሲሳተፉ ተገኝተዋል ተብሏል። ሕፃናቱ ዕድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሱ መሆናቸውን በቀላሉ በዓይን በማየት ብቻ ግንዛቤ መውሰድ የሚቻል ሲሆን፣ የኢሰመጉ ታዛቢዎች በርከት ያሉ የፎቶግራፍ ማስረጃዎችንም አቅርበዋል።

በድምጽ ቆጠራ ወቅት ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የኢሰመጉ ታዛቢዎች ሒደቱን እንዳይታዘቡ ከምርጫ ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዲወጡ የማድረግ ሙከራዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ታዛቢዎቹ ሒደቱን እንዲከታተሉ ተደርጓል። የኢሰመጉ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የቆጠራ ሒደቱ ወደ ቀጣዩ ቀን እንዲታላለፍ የተደረጉባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ስለመኖራቸው ሪፖርት አድርገዋል ተብሎ ነበር።

ስድስተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ገና ከውጥኑ ጀምሮ የተለያዩ እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደ አጠቃላይ ምርጫነቱ ሳይሆን፣ በተለያየ ጊዜ በዙር የሚደረግ ምርጫ ሆኗል። ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በኮቪድ 19 መካሄድ ባለበት ጊዜ አለመካሄዱን ተከትሎ፣ ለአንድ ዓመት ተራዝሞ ከሰኔ 14/2013 ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ እና መስከረም 20/2014 ከተካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ የቀጠለ ሦስተኛ ዙር ምርጫ ተወልዷል።

በኹለተኛው ዙር ምርጫ ይካተታሉ ተብለው የነበሩ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በኹለተኛው ዙር ምርጫ አልተካተቱም። በዚህም ምርጫው ለሦስተኛ ዙር የተላለፈ ሲሆን፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምርጫን ታህሳስ 21/2014 ለማካሄድ በምርጫ ቦርድ ቀጠሮ ተይዞለታል።

እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች ካልተካተቱት አካባቢዎች መካከል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙት መተከል እና ካማሺ ዞኖች ለሦስተኛ ዙር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ቢወጣላቸውም፣ በሦስተኛውም ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አከባቢዎች አሉ።
በሦስተኛ ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ክልሎች ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአማራ ክልል 10፣ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ሲሆኑ፣ በክልል ደረጃ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን በኦሮሚያ ክልል ሰባት እና በአማራ ክልል ዘጠኝ ናቸው።

በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት በመጀመሪያውም ይሁን በኹለተኛው ዙርም ምርጫ ያልተደረገባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ማጀቴ (ማኮይ) የምርጫ ክልል፣ አርጎባ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ሸዋሮቢት የምርጫ ክልል፣ ኤፌሶን የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ አርማጭሆ የምርጫ ክልል እና ድል ይብዛ የምርጫ ክልል ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰሜን ሽዋ ዞን ችግር የተከሰተባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ባለመካሄዱ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አሁንም በሦስተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ አካባቢዎች ያሉ ሲሆኑ፣ ቤጊ የምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ አያና የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ ገሊላ የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ አሊቦ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ)፣ ጊዳም የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here