‹‹መንገድ ላይ መሰንቆ ይዞ መሄድ ፋሽን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል››

Views: 456

ትውልድን እድገቱ አዲስ አበባ ነው። ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ከሆነው ማሲንቆ ጋር የሚገርም መግባባት አላቸው። የማሲንቆን አቅም በሚገባ እንደተረዳ ያስታውቃል፤ ያሻውን ሙዚቃ፤ የአገር ቤቱን ምት ይሁን የባህር ማዶ ዘመናዊ መሣሪያ የሠራውን ዜማ በማሲንቆው መጫወት ያውቅበታል። ሀዲስ ዓለማየሁ ይባላል፤ በቅጽል ሥሙ ሀዲንቆ። ከጓደኞቹ ጋር ባቋቋሙት መሶብ የባህል ቡድን በኩል በተለያዩ የጥበብ መድረኮች፣ የግጥም ምሽቶች፣ የመጽፍት ምርቃት እንዲሁም እንደ ‹በጎ ሰው› ባሉ የሽልማት ክዋኔዎች ላይ ማሲንቆውን አሰምቷል። በቅርቡም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማትን በተቀበሉበት መድረክ ከሙያ አጋሮቹ ጋር ሥራውን አቅርቧል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጠቅለል ባሉ የማሲንቆና የሙዚቃ ጉዳዮች እንዲሁም በጎንደር ቡርቧቅስ ስለነበረው ቆይታ በማንሳት ከሀዲስ ዓለማየሁ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በሥምህ እንጀምር። ሀዲስ ዓለማየሁ፤ አጋጣሚ የወጣ ሥም ነው ወይስ ሆነ ተብሎ?

ሥሜን ያወጡልኝ ጎረቤቴ ናቸው፤ መጽሐፍ ማንበብ ይወዱ ነበር። የአባቴ ሥም ዓለማየሁ መሆኑን ሲያውቁ እኔ ነኝ ሥሙን የማወጣው ብለው ሐዲስ አሉኝ። ከዛ ቤተሰብም ተስማማና በዛው ጸና።

በተለያዩ ቃለመጠይቆች ቡርቧቅስ ሄደህ እንደነበር ተናግረሃል፤ ቆይታህ እንዴት ነበር?

የቡርቧቅስ ቆይታዬ ጎብኘት አድርጎ መመለስ፣ እዛ ያለውን ሁኔታውን ማየት ነበር። አብዛኛውን ጎንደር ከተማ ላይ ነው የቆየሁት። ጎንደር ከተማ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫ የሚመጡ መሰንቆ ተጫዋቾች አገኝ ስለነበር፣ አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው እዛ ነበር።

ቡርቧቅስ ትንሽ ከተማ ነው። ግን አብዛኛው መሰንቆ ተጫዋች የሚገኝበት፤ እረኛውም መሰንቆ ይዞ እረኝነት የሚሄድበት፤ ብቻ ከመሰንቆ ጋር ትልቅ ቁርኝነት ያላቸው ናቸው። ፈረንጆቹ ጋር ጊታርና ፒያኖ በየቤቱ እንደሚገኝ፣ ቡርቧቅስ በየቤቱ መሰንቆ አይጠፋም። የዛን ያህል ከሕይወታቸው ጋር ቁርኝት አለው። ጎንደርም ከብዙ አቅጣጫ የሚመጡ ሰዎች አሉና እንደውም ማኅበር አላቸው፤ የመሰንቆ ተጫዋቾች ማኅበር። መሰንቆ ያስተምራሉ፣ ያሠለጥናሉ፣ ይሸጣሉ።

አሁን ምን ላይ እንደደረሱ ባላውቅም፣ ‹ዛትኛ› የሚባል ቋንቋ ፈጥረዋል። በዚህ ያወሩበታል። የአዝማሪዎች ቋንቋ ነው፤ ለማስፋፋት እያሰቡ ነበር። 2007 አካባቢ ነበር እኔም የሄድኩት።

መሰንቆን ከአገር ፍቅርና ስሜት ጋር እንዲህ ያገናኘው ምንድን ነው ትላለህ?

ለእኔ ዋናው ነጥብ ታሪካዊና ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ እድሜም ያስቆጠረ መሆኑ ላይ ነው። ለምሳሌ እስከ ‹አሁን እንዴት ቆየ? ከየት መጣ?› የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ ከአክሱማይት ዘመን ጀምሮ የነበረ ወዘተ እየተባለ ይነገራል፤ ይተረካል። ይህን ታሪክ ለማወቅ በር ይከፍታል። ጊታር ይዤ ቢሆን ግን የጊታር አመጣጥን ስጠይቅ የሌላ አገር ታሪክ ነው የማጠናው።

ከዛ በተረፈ መሰንቆ ከታሪክ ጋር በተያያዘ በጣልያን ወረራ ጊዜ አዝማሪዎች ሲደርስባቸው የነበረ በደል አለ። አልፎም ለፈረሶች ደርሷል። የፈረስ ጭራ እየተቆረጠ ነበር። ጭራ አይኖርም ማለት አዝማሪ አይኖርም፤ አዝማሪ ከሌለ ቀስቃሽ አይኖርም። ጣልያኖች በኢትዮጵያውያን አርበኝነት ላይ አዝማሪ ትልቅ ሚና እንደነበረው ገብቷቸዋል።

እንዲሁም በመጠየቅ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አሉ። እነዛ ሰዎች የሚመክሩትና የሚያቀብሉት ሐሳብ፣ አንብብ የሚሉትና የሚጠቁሙት መጽሐፍ ይኖራል፤ እገሌን ብታገኝም ይላሉ። ያንን ተከትለሽ ስትሄጂ ታሪክና መሰል ባወቅሽ ቁጥር ትወጂዋለሽ። በታወቀ ቁጥር እየተወደደ ይሄዳል።

ከዚህ በኋላም የበለጠ እንዳውቅ ነው የሚጠይቀኝ። ገና ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች አሉ። ከሙዚቃ መሸሽ አይቻልም፤ በላይ በመንፈሳዊ ይሁን ወይም በዓለም ሙዚቃ በር ነው፤ ከሙዚቃውም የባህሉ ከዛም የባህል ሙዚቃ መሣሪያ፤ ከዛም መሰንቆ ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንጻር ብዙ ይገናኛል ብዬ አስባለሁ።

መሰንቆ ተጫዋቾች ግጥሞቻቸው ላይ ሳይቀር ጠንቃቃ ናቸው። በተለይ ከከተማ ወጣ ያሉ አካባቢዎች የሚገኙት። ከየት ያመጡት ወይም ያገኙት ይመስልሃል?

በታሪክ ‹አዝማሪ ምን አለ› እየተባለ ይጠየቃል። ባለሥልጣናትም ይህን ይጠይቁና መረጃ ይወስዱባቸው የነበረ ቋት ናቸው፤ አዝማሪዎች። አዝማሪዎችም ለመረጃ ቅርብ የሆኑና ከማኅበረሰቡ ጋር የተግባቡ፤ ግጥምን ጆሮ ገብ በሆነ ዜማና ቋንቋ ለሰሚ የሚያደርሱ ጥበበኞች ናቸው። እንግዲህ ከፈጣሪም ነው የሚሆነው፤ የራስ ጥረትም አለበት። በጥቅሉ ግን ራሱን የቻለ ትልቅ ጥበብ ነው።

በአዝማሪ መልዕክት ይነገራል። ነገሥታት አብዛኛውን አካሄዳቸውን ሊያስተካክሉና ረጅም እድሜ ሥልጣን ላይ ሊቆዩ የቻሉት አንድም ከአዝማሪ በሚያገኙት መረጃ ነው። እንደሚታወቀው የጥበብ ሰዎች ከማኅበረሰቡ ቀደም ያሉ፣ ከነገሥታትም ቀደም ያለ እውቀት ያላቸውና መንጋውን ወደ መልካም ሊወስዱ፤ ወደ ገደልም ሊከትቱ የሚችሉበት አቅም ያላቸው ናቸው።

እኔ ራሴን በዛ ማስቀመጥ ይከብደኛል፤ አሁን ባለሁበት ሁኔታ። ብዙ ይቀረኛል። ስለአገር የማላውቀው ነገር አለ። የድሮዎቹ ብዙ እውቀትና አቅም አላቸው።

ጎንደር ላይ ያለው የመሰንቆና የአዝማሪ አገልግሎት ከቀደመው ጊዜ ጋር የሚመሳሰልበት አጋጣሚ አለ?

አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ይታወቃል። ባለሥልጣናት መልዕክተኛ ልከው ምን ተባለ አይሉም። ጎንደር አካባቢ ሻል ያለ ሙዚቃ ይሰማል። የነ ይርጋ ዱባለ፣ የነ ባህሩ ቃኜ አዚያዜም መንገድ አለ። ገንዘብ ለማግኘትና ለመሸንገል አይጠቀሙበትም። ለጥበብ ብቻ ነው የሚሠሩት፤ እሱን አይቻለሁ። አልፎ አልፎ ደግሞ ለኑሮ መሸፈኛ እና በልቶ ለማደር ሲያስቡ የሚጠቀሙት መንገድ አለ፤ እንደ አዲስ አበባዎቹ ግን አይደሉም። የአዲስ አበባዎቹ ከመስመር ይወጣሉ። ከወግ፣ ባህል እንዲሁም ስርዓት ወጣ ይላሉ፤ ከተማ ላይ።

ገጠር ላይ ቅኔና ዜማ ይበዛል። ሰው በትክክል አዝማሪ ቤት ቤተሰቡን ይዞ ገብቶ ሊዝናና ይችላል። አዲስ አበባ ግን አይችልም፤ እርግጠኛ ነኝ። አዲስ አበባ ላይ ልጄ ባህል እይ ብሎ መውሰድ የለም። እዛ ግን ያንን አይቻለሁ።

እኔም እየሄድኩ እቀዳ ነበር። ሥራዬ ብዬ እየቀዳሁ እዛ ያገኘኋቸው ግጥምና ዜማዎች አሉ። እንደውም የቤቲ ጂ ‹ገርዬ› የተሰኘ ሙዚቃ ላይ ያለችው ማስመቻ ከጎንደር ያመጠኋት ናት፤ ትንሽ ቀመም አደረኩት እንጂ። ከዛ ከመጣሁ በኋላ የዛ ተፅዕኖም ነበረብኝ።

መሶብ የባህል ቡድን ሲጀመር በጋራም በተናጠልም ሕልም አላችሁና ያ ምን ይመስል ነበር?

የመሶብ መሥራቹና የሐሳብ ጠንሳሽ ጣሰው ወንድም (ዋሽንት ተጫዋቹ) ይባላል። ሐሳቡ ሲመጣ የዛሬ 8 እና 7 ዓመት ገደማ ነው። ባንድ /የሙዚቃ ቡድን/ እንመሥርት ሲባል ደስ አለን፤ በሞራል ተነሳን። ሲያወራንም ትልቁን ስዕል አሳየን። ሥም አወጣን፤ እሱም መሶብ የሚል አምጥቶ ነበርና እሱን አብራርቶልን፤ የሰበዙን ነገር አስረዳንና ሥያሜውን ወደድነው።

አሁን ኹለተኛ አልበማችንን እያዘጋጀን ነው። የተለያዩ መድረኮች ላይ ሠርተናል። አገር እንዲሁም ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከጀማሪ እስከ ትልልቅና አንጋፋ ባለሞያዎች ጋር ሠርተናል። ግጥም በጃዝ፣ የመጽሐፍት ምርቃት፣ ደም ልገሳ ፕሮግራምና ማኅበራዊ ክዋኔዎች ላይ፣ በጎ አድራጎቶች ላይም ሠርተናል። ሐሳብ ሲመጣልን አይተን በጣም በቅናሽ ዋጋ አንዳንዴም በነጻ እንሠራለን። ተገቢውን ዋጋም እንጠይቃለን፤ የሠርግ ሥራዎችም ጭምር ሠርተናል።

ትልቁ መሶብ ውስጥ ያለው አቅምና ችሎታ ሐሳብ ነው። ቀድሞ ካየሁት ላይ ያለው አስተሳሰብ መሥራትና መሥራት ከዛ ደሞዝ መቀበል፤ ደሞዝ ሲያልቅ አሁንም መሥራት ነው። ለውጥ የሚፈጥር ሐሳብ አምጥቶ ‹ለምን እንዲህ አናደርግም?› የሚል ሐሳብ ያላቸው ልጆች አብዛኛውን ጊዜ አላገኘሁም። መሶብ ጋር ግን ሐሳብ የሚያመጣ አለ። አሁን አሠራር የመቀየር ሥራ ነው የሠራነው።

ከሆነ ጊዜ በኋላ በትክክልም ተቀይሯል። አሁን ግጥም በጃዝ ሲባል ያለ ባህላዊ መሣሪያ አይሠራም።

ሌላው ናይት ክለብ ላይ ሙዚቀኛ እና ታዳሚ እንዳይገናኝ ይከለከላል። ለሙዚቀኛ ወርዶ ታዳሚውን ሰላም ማለት እንኳ አይፈቀድም። ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ግን በሙዚቀኛውና በታዳሚው በኹለቱ መካከል አለቃ አለ። ስለዚህ እሱ በመሃል ሆኖ ሰው ሐሳቡን እንዳይቀያየር፣ እንዳይገናኝ፣ እንዳይደናነቅ ያደርጋል።

ያንን የማፍረስ ሥራ መሠራት አለበት የሚል ሐሳብ ይዘን፤ ኹለቱ [ሙዚቀኛ እና ታዳሚ] ቀጥታ መገናኘት የሚችልበት ስርዓት መዘርጋት አለበት ብለን የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ። በዚህም በአብዛኛው ሙዚቀኞች ላይ ተጽእኖ መፍጠር ተችሏል። በእነርሱ ሙያ ሌላው መጠቀም እንደሌለበት፣ ተከብረን ሠርተን እኛም ሥራችንን አክብረን በትክክል ደንበኞች ጋር ካደረስን፤ ሰው ተገቢውን ክብር ይሰጣል፤ ማድነቁም፣ ድጋፍና ሐሳብ ይገኛል።

ሰው በሐሳብ፣ በእውቅት፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጊዜ ያለውን ይሰጣል። ጊዜ መስጠትና መገኘት ቀላል አይደለም። ሰው ጊዜውን ሲሰጥ ትልቅ ነገር ነውና ያንን የመረዳጃ ስርዓት በር ይከፍታል። ይህ ሙዚቀኛ ከአድማጩ ወይም ደንበኛው ጋር በቅርብ እንዲገናኝና ሙዚቃ እንዲያቀርብለት፣ በሙዚቃ ሕክምና እንዲሰጠው፣ ማኅበራዊ ሕይወቱ ላይ በመገኘት እንዲደግፈው ያስችላል። አሁን ያንን ስርዓት ጀምረናል፤ አሁን የባህል ምሽት ባለቤቶች ተገቢውን ክፍያ ለባለሙያው የመክፈል ነገር አለ፤ እየተቀየረም ነው።

አንዲር ሙዚቃ ተጫዋቹን እና አድማጭ ተመልካቹን የማገናኛ መንገድ አንድ አካል ነው ማለት ይቻላል?

አንዲር በየወሩ የሚዘጋጅ ክዋኔ ነው፤ አሁን ለጊዜው አልበም ሥራው ላይ ስላተኮርን አቁመነዋል። በየወሩ ነበር የምንሠራው። ሰዉና ሙዚቀኛው የተገናኘበት መድረክ ነው። እንደ አገር በየወሩ መዘጋጀት አለበት በሚል ተነሳን። ታዳሚ ጠጅና መጠጥ እየጠጣ እንዲሁም እየበላ ነው ወይ ሙዚቃን ማዳመጥ ያለበት የሚል ጥያቄ ተፈጠረብን። አይተሽ ከሆነ በአንዲር መድረክ መጠጥና ምግብ የለም፤ ኮሽ የሚል ነገር አይሰማም፤ የሚጠራ ተንቀሳቃሽ ስልክ እንኳ የለም።

ሰዉ ገብቶት ሙዚቃ አዳምጦ፣ ባህላዊ ጭፈራ አይቶና ጨፍሮ፤ እንደ ገጠሩ አዝማሪ ቤት ልጆቹን ይዞ መጥቶ፣ ባህል ላሳይ ብሎ የሚገኝበት ነው። እኛም የመሣሪያዎቻችን አቅም ምን ይመስላል የሚለውን ያየንበት መድረክ ነው። ከአንዳንድ ሚድያዎች ጋር ለመሥራት ሞክረናል። አብዛኞቹ ቀረጻዎች ግን እጃችን ላይ ናቸው። አሁን እየተጠቀምናቸው ነው።

በተለይም ዩ ትዩብ ላይ ለማሳየትና ሥራዎቻችንን ለማስተዋወቅ። እንደ አገር ግን ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል። ሰው የሚወደውን እንዳይሠራ የሚያደርገው አንዱ የኑሮ ነገር ነው፤ ገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህም ሆነ በሌላ አንጻር ምክንያት ሆኖህ ይህን መሰንቆ በተውኩት ብለህ ታውቃለህ? ጎንደር የሄድኩበት ትልቁ ምክንያት ይኸው ነበር። መሰንቆን ልተወው ወይም ሱቅ በደረቴ ጀምሬ ከዛ ተነስቼ ትልቅ ለመሆን ቢዝነስ ውስጥ ልግባ የሚል ነገር ወስኜ ነበር።

ከደሃ ቤተሰብ የወጣሁ ልጅ ነኝ፤ ቤተሰብ መርዳት እኔም መረዳት አለብኝ፤ በዙሪያዬም ብዙ ነገሮች አሉ። ገቢና ወጪው ካልተመጣጠነ ያስወስናል። ግን በመሰንቆ ብዙ ነገር አግኝቻለሁ፣ ደስተኛ ነኝ፤ የምወዳት ነገር ሆናለች። ሰዉም ‹አዝማሪ!› ይለኛል፤ እሱም ተጽእኖ አለው።

ብቻ ልጅ መሆኔ የጠቀመኝ ይመስለኛል። ልጅ ሲባል ግዴለሽ ያደርጋል። አሁን ላይ ቢሆን ላልወስን እችላለሁ። ምክንያቱም አማራጭ አለኝ። ጉልበት ሥራ ሠርቼ እለወጣለሁ፤ ከአገር ወጥቼ እሠራለሁ ሊባል ይችላል። በዛ ጊዜ ግን ማፈር የሚባል ነገር የለም። አዝማሪ መባሉ ተጽእኖ ቢኖረውም፣ ግድ አይሰጠኝም። ቤተሰቦቼም ነጻ እድርገግው ስላሳደጉኝ፣ ችግርና ፈተናን የመፍራት ነገሬ ጠባብ ነበር። ያ ሐሳብ ወደ ጎንደር፤ ያለኝን ሁሉ ጥዬ የማውቀው ሰው በሌለበት እንድሄድና እንድወስን ያደረገኝ እሱ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት ታገለግል እንደነበር ተናግረሃል። አሁንም እያስተማርክ ነው?

በፊት ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በኤስተቲክስ ፊዚካል ኤዱኬሽን ትምህርት ክፍል ነው የተመረቅኩት፤ ዲፕሎማ አለኝ። እዛ የገባሁት ሙዚቃ የሚለው እንደ አንድ ኮርስ ይሰጥ ስለነበር፤ እሱን አይቼ ነው። ከዛ በኋላ በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት አምስተኛና ስድስተኛ ክፍል አስተምር ነበር። ከዛ ገቢና ወጪው ስለማይመጣጠን ወደ ጎንደር ሁሉን ትቼ ሄድኩ፤ እዛ ባገኘሁት እውቀት በትርፍ ጊዜዬ የመሰንቆ ትምህርት ማስተማር ጀመርኩ። ያንን ማስተማሬ ለብዙ ነገር ጠቅሞኛል። ተቀጥሬ ማስተማር ላይ ግን አሁን የለሁም።

የሙዚቃ ሰዎች በባህር ማዶ ፒያኖና ጊታርን የሚጠቀሙበትን መንገድ አይተህ መሰንቆንስ ለምን እንደዛ አንጠቀምም በሚል ሙከራዎችን እንደጀመርክ በተለያየ ጊዜ ገልጸሃል። በዛ መልኩ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን ተጠንተዋል ማለት ይቻላል?

እውነት ለመናገር በዚህ መንገድ አልተጠናም። እነ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ እንዲሁም ሌሎችም የሠሩት በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ያሉ ዶክመንቶች አሉ። የኢትዮጵያ ቅኝት ምንድን ነው ከሚል ጀምሮ መሠረታዊ የሆነ የሙዚቃ ስኬል ላይ የተመሠረተ መረጃ አግኝቻለሁ። የውጪ አገር ሰዎችም ስለ መሰንቆ አጥንተው አይተናል፤ በተለይ ቢቢሲ ያዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም አለ፤ ከጋሽ ባህሩ ቃኜ ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የአዝማሪ ታሪክ አያይዘው የመሰንቆ ባህሪው ምን ይመስላል የሚለውን ለማሳየት ሞክረዋል።

ግን ደፍሮ ‹ይህ ድምጽ እንዲህ ነው፤ ከዚህ ድምጽ ጋር ይህኛው በዚህ መንገድ ሊሠራ ይችላል› ወዘተ የሚል አጥኚና የተጠናም ነገር ይጎድላል። ሊኖር ይችላል፤ ግን አላየሁም። የኔ የመፈለግ እጥረት ነው፤ ወይ ያጠናው በደንብ አላቀረበውም፤ አልያም ጊዜውን እየጠበቀ ይሆናል። የለም ብሎ መደምደም አይቻልም፤ አይጠፋም፤ የት እንዳለ ግን አላውቅም።

ሃዲንቆ የባህላዊ ሙዚቃ ተጫዋች ነው ወይስ የዘመናዊ?

መልሴ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች ነኝ ብቻ ነው። ምክንያቱም ባህልና ዘመናዊ ቃሉ ራሱ ውዥንብር የሚፈጥር ትርጉም ነው ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው። ባህላዊ ሲባል ሰዉ ኋላቀርን ነው የሚያስበው። ዘመናዊ ሲባል ደግሞ አዲስና ፋሽን ነው የሚመስለው። ይህ ቃል መቀየር አለበት። ባህላዊና ዘመናዊ መሣሪያ ወይም በሌላ ዓለም ‹ሞደርን› እና ‹ትራዲሽን› ሲባል እነርሱ ይረዱታል። ትራዲሽናል ሲባል የራሱ ቀለም ያለው፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ፣ ምንጩንና መሠረቱን የጠበቀ ብለው ሊተነትኑት ይችላሉ። እኛ ግን ቀጥታ ከኋላ ቀር ጋር እናገናኘዋለን።

በበኩሌ የባህላዊ ወይም ዘመናዊ ሙዚቃ ተጫዋች ነኝ ከማለት፣ መሰንቆ ተጫዋች ነኝ ማለት ይቀለኛል። ይህ መጥራት አለበት። ይህን ካጠራን፤ በእኔ ቋንቋና አረዳድ ባህላዊ ሙዚቃ ሲባል የራሱ ማንነት፣ የራሱ ታሪክና ውበት አንድን አገር/ማኅበረሰብ ሊወክል የሚችል አቅም ያለው የሙዚቃ ስርዓት ብል ይቀለኛል። በዚህ ቋንቋ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ እንደ ቡፌ ነው። የተለያየ ዓይነት ምግብ ይቀርባል፤ ሁሉም የየራሱ ጣዕም አለው። ሰው አንድ ዓይነት ነገር ስለሚሰለች፣ የተለያየ ዓይነት ነገር ስለሚማርከው፤ ከወደደ ኹለቱን ሊመርጥ ወይም አንዱን ብቻ ሊወድ ይችላል። በስነስርዓት ጣፍጦ ከቀረበ ሁሉም የሚወደድ ይሆናል፤ ሰውም ከሁሉም ይወስዳል።

እንደ እኔ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ ላይ አንደኛ ማኅበረሰቡ አረዳዱን እንዲቀይር ባይ ነኝ። እሱን ለመቀየር በጀመርኩት መንገድ በእኔ እድሜ ያሉ ወጣቶች ላይ መሰንቆ ሲባል ኋላ ቀር የሚለውን ለመስበር ነው ሙከራ ያደረኩት። ዩ ትዩብ ላይ ሰምተሸ ከሆነ የነ ሲሊንዲዮን፣ ኤድ ሼረንና ማይክል ጃክሰንን ሙዚቃ በመሰንቆ እየሠራሁት ነው። ያንን ተጫውቼ ካሳየሁ፤ ‹ስለዚህ የእኛ መሣሪያ የሆነ ምስጢር አለው ማለት ነው› ብሎ ሰው እንዲጠይቅ በር ይከፍታል።

ሰው መውደድ ይጀምራል፤ እያለ እያለ ፋሽን ይሆናል። እና እንደ ፋሽን በየመንገዱ ማሲንቆ ይዞ የሚንቀሳቀስ ትውልድ በቅርቡ ይፈጠራል። ፋሽን የሚሆንበት ዘመን ይመጣል። ያኔ ምን ሊለው ነው፤ ዘመናዊ መሣሪያ ሊለው ነው? በእርግጥ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፤ ግን ኋላ ቀር የሚለውን ትርጉም ያስተካክላል።

የቀደሙ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች በሆነ በሆነ አጋጣሚ ነው ሥማቸው የሚነሳው፤ በአንጻሩ በቋሚነት እንዲታወሱ ምን መደረግ አለበት?

እንደ ባህል እንደ አገር ነው ኃላፊነቱ። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል መሠራት ያለበት ነገር ይኖራል። በቅርቡም አንድ ፕሮግራም ይኖራል። ይህም የጋሽ ይርጋ ዱባለን መሰንቆ ቤተሰቦቹ በክብር አስቀምጠዋልና በክብር ለእኔ ሊያወርሱኝ አስበዋል። ድምጻዊ ኤልያስ ተባበል ተቀብሎ ነው የሚሰጠኝ። ይህንንም መገናኛ ብዙኀን ጠርተው ሊያደርጉት ነው።

እንዲህ ባለ መልኩ እውቅና ኖሯቸው የሚደረጉ ሥራዎች እስከ ዛሬ የሉም/አልነበሩም፡። ምናልባት በመንግሥት ደረጃ ሊዘጋጅ ይገባል፤ አቅም ስለሚፈልግ። ኹለተኛ ለእኚህ ሰው መንገድ ይሰየምላቸዋል፤ ለጋሽ ይርጋ ዱባለ። እንዲህ ባለ መንገድ በማስታወስ የሆነ ወቅት የሚከበር በዓል ቢኖር፤ በሥማቸው ሙዚቃ ትምርህት ቤት ቢከፈት፤ ሐዲስ ዓለማየሁ ትምህርት ቤት እንዳለው ሁሉ፤ ለነዚህም እንደዛው። እኛም እንደ ባለሙያ ለምሳሌ የመጀመሪያው አልበም ላይ አቡነ ጴጥሮስን በተመለከተ ነው የሠራነው።

ርዕሱ የእርሳቸው ነው። ሰው ሲሰማ ማን ናቸው ብሎ እንዲጠይቅና እንዲያስታውስና እንዲያውቅ ማድረግን ነው ያሰብነው። በዚህ መልክ ለመሥራትም ከባለሞያዎች ብዙ ይጠበቅባቸዋል።

በርካታ መድረኮች ላይ ሥራዎችህን በግልህ እንዲሁም በጥምረት አቅርበሃል፤ እስከ አሁን ባለው ከሁሉም የምትወደውና የማትረሳው መድረክ የቱ ነው?

ዞር ዞር ማለትን ገና እየጀማመርኩ ነው፤ ገና ነኝ። ከዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ጌንት ላይ (የቤልጄም ከተማ ናት) አንድ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ ተገኝቼ ነበር፤ የዛሬ ዓመት አካባቢ። እዛ አንድ ሙዚቃ የመጫወት እድልም አግኝቼ ነበር። የሚገርም ነበር፤ የሰዉ ብዛትና ድምጹ ልዩ ነበር። እሱን ጊዜ የማልረሳበት ምክንያት ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመሥራቴ፣ በዛ ላይ ለሙላቱ ያለውን ክብር ሳይ ነው።

እዚህ ከተወሰነ ዓመት በፊት አንድ ፕሮግራም ነበረው፤ ጋሽ ሙላቱ። ግን የዛን ያህል ሰው አልነበረም። እዛ ግን በትንሹ 40 ሺሕ ሰው ነበር። እሱ ይኖራል ስለተባለ ነው። እንዲህ ካለ ሰው ጋር በዛ መድረክ መገኘት ትልቅ ነገር ነው። ተጫውተን እናውቃለን፣ ግን በዛ ትልቅ መድረክ ላይ መጫወቱ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው። ከዚህ በኋላ እንዴት እንደምንሠራና እንደምንገናኝ አላውቅም፤ ይህ ጊዜ ቢደገም ግን ደስ ይለኛል።

የጸጉር ስታይልህን እናንሳ፤ በዚህ ይቀጥላል?

መጨረሻውን ልየው ብዬ ነው። ከዚህ በኋላ አልነካውም እላለሁ፤ ድሬድ ይሆናል፣ ይያያዛል። ጫፉን አነሳዋለሁ፤ እሰነጥቀዋለሁ ድጋሚ ይያያዛል። ግን ለወደፊት ምን እንደማደርገው እስከ አሁን አልታወቀም። በዚህ ነው ሰው የሚያውቀው።

የወደፊት እቅድህ እንዲሁም ህልምህ ምንድን ነው?

እንደ ቡድን አልበሞችን ሠርተን፣ አገርን ወክለን ትልልቅ መድረኮች ላይ መሳተፍ ነው። እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ወክለናል ብለው በፒያኖ ሞክረዋል። ግን ያ ኢትዮጵያን አይገልጽም። በባህላዊ መሣሪያችን፣ ተከብረን ተወደን ተቀብለውን አገራችንን አስተዋውቀን አገራትን ለመዞር እንፈልጋለን። አልበሞችን እየሠራን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን።

በ2050 ዓለም ሁሉ መሰንቆ ሲጫወት የማየት ሕልም አለኝ። በግልም ብዙ ሕልም አለኝ። ብዙ ቦታዎችን ጎብኝቼ፣ በሥሜ ትልልቅ ሥራዎችን ሠርቼና ትምህርት ቤትም ከፍቼ ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ።

ግን ሥምህን አትፈራም ታድያ፤ ሀዲስ ዓለማየሁ ቀድሞ ስለሚታወቅ?

ሀዲንቆም የመጣው ለዛ ነው፣ ሰው ግራ እንዳይጋባ። ሀዲንቆ የሚለው ሥም ቃሉ አዲስ ይመስላል። ግን ሀዲስ እና መሰንቆ ላይ የመጀመሪያና የመጨረሻ ፊደላት ተወስደው፤ ሀዲ እና ንቆ ተዋህደው የተፈጠረ ሥም ነው።

አሁን ላይ ጥቂት የማይባሉ መሰንቆ ተጫዋቾች አሉ። የቀደሙም እንደዛው፤ ምን ይመስልሃል አሁን ባለው ልክ በመሰንቆ የጎላ ሥራ ያልሠሩት?

ምንአልባት የእነርሱ ዘመን ትልቅ ዋጋ ከፍለው አቆይተውልናል/አኑረውልናል። አልተሳካላቸውም ማለት አይቻልም። እንደ እኔ እንደ እኔ ራሴን መካብ አይሁንብኝና ትንንሽ ነገሮች ሳያባክኑ በመጠቀም አምናለሁ፤ ያንንም አደርጋለሁ።

የሥራ ፈጠራን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ወስጃለሁና ለስኬት ጥሬ ግብዓት ነው። ከጊዜው ጋር መሄድ ላይ አለሁበት፣ ዩት ትዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ፌስቡክ ላይ አለሁ፤ ሰው ፈልጎ አያጣኝም። የሌለኝ ዌብሳይት ነው፤ እሱም በቅርቡ ይኖረኛል። በግሌ እጥራለሁ እሞክራለሁ፤ እሱ ሊሆን ይችላል እዚህ ያደረሰኝ። ሌሎች ምንአልባት ራሳቸውን በዛ ልክ አልገፉም ይሆናል።

እውቀት የላቸውም እንዳልል ከእነርሱ በላይ ጥበበኛ የለም። ግን እንደ እኔ ዓይነት ትውልድ ይመጣል ብለው ራሳቸውን እስከሆነ ደረጃ ገድበው የተወሰነ ነገር ላይ ትኩረት አድርገው ሠርተው መሰንቆን እዚህ አድርሰው ይሆናል። እኔም አምናለሁ፤ ከዚህ በኋላ ቴክኖሎጂና እውቀት ተጠቅሞ በደንብ የሚያሻግር ትውልድ ይመጣል። የተሻለ ሐሳብ ይዞ የሚመጣ ሊኖር ይችላል፤ በእርግጠኝነትም ይኖራል። ራሴን ከሌሎች ጋር ማበላለጥ ይከብዳል። የምሞካክራቸው ነገሮች ይሆናሉ።

ከአጓጉል ሱሶች ራሴን ገድቤ ነው ያለሁት። ጊዜዬን ለማንበብና ሰው ለማግኘት፤ ሀይኪንግ እወዳለሁ፤ በዛ በዛ አሳልፋለሁ። እነዚህም እንቅስቃሴዎች ወደ ውስጤ ለማየት ጊዜ ይሰጡኛል። እንዲህ ያለ ነገር የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል።

አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ልጨምር፤ ከቤተሰብ አባላት ወዲህ ወደ መሰንቆ ወይም በጠቅላላው ወደ ሙዚቃው የተጠጋ አለ?

አራት ወንድሞች እና ኹለት እህቶች አሉኝ። ትንሽ ወንድሜ ክራር ይሞክራል፤ ምህንድስና ተማሪ ነው። በትርፍ ጊዜው ለእንጀራም ባይሆን ፍላጎት ስላለው፣ እኔም ቢያንስ መሞከር አለበት ግዴታው ነው ብዬ ኃላፊነት ጭኜበታለሁና ይሞካክራል። እናቴ ጥሩ ገጣሚ ነች፤ ግጥም ታቀብላለች። ቡና ስትወቅጥም በዜማ ነው። እኛ ቤት መድረክ ላይ ያልወጣ ሙያ አለ ማለት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com