በ“ባሕል” ሥም ሴት ሕፃናትን በትምህርት ፈንታ ወደ “ጋብቻ”

0
942

ቤተልሔም ነጋሽ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች ሲወራ የሰነበተውን የ12 ዓመት ታዳጊ የ“ጋብቻ” ፎቶ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ያለ መምህር ያደረሳቸው እና በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ያሉ፣ በቤተሰባቸው ሊዳሩ የተፈረደባቸው ነገር ግን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 7 ተማሪዎችን ዝርዝር መነሻ አድርገው የሚከተለው ትዝብት ያስነብቡናል።

 

 

የሰኞ (27 ጥር 2011) ቀን የፌስቡክ ውሎ ጅምር እንደሌላው የተለመደ ቀን አልነበረም። ጠዋት እንደልማዴ ከሥራ በፊት ፌስቡክና ትዊተር “ምን አሉ?” ብዬ አየት ባደርግ በአንድ የፌስቡክ ወዳጃችን ከአንዲት ወዳጄ ጋር በጋራ ሥሜ ተነስቶ አየሁ። የተመለከትኩት “ኧረ ሴታዊት (ፌሚኒስቶች) ይህቺን ሕፃን አስጥሉ” ከሚል መልዕክት ጋር የተያያዘ ፎቶ ነበር። ወዳጃችን ያጋራን ፎቶ ኋላ የ12 ዓመት ልጅ እንደሆነች የምንረዳት ሕፃን እና የፌስቡክ ገጹ 18 ዓመት እንደሞላው የሚያመለክተው ወጣት በቤተክስርቲያን የተክሊል ጋብቻ ልብስ ለብሰው የተነሱት ፎቶ ነበር። ሁለቱም የጋብቻ ቀለበት አድርገው፣ ካባና ቆብ ደፍተው ይታያሉ። ታዳጊዋን “የሚያገባት” ወጣት ፎቶውን ፌስቡክ ላይ ሲያጋራ በትግርኛ የጻፈው መልዕክት “አስቤው ሳይሆን ተሰጥቶኝ ነው” የሚል ነበር።

ፎቶው ላይ የልጅቷ ሕፃንነት በግልጽ ይታወቅ ስለነበር፥ በሠርግ ልብስ ሆና ስትታይ በጣም የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን አስቀያሚ ነገርም ነበረው። ወዲያው የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን የሚያውቁና ከዚያም አካባቢ የመጡ ጓደኞቻችንን ስንጠራ ጉዳዩ ታውቆ በክልሉ ያሉ የመብት ተሟጋቾችና ታዋቂ ሰዎች እንደያዙት ሰማን። ትክክለኛ ቦታውን ለማወቅም ርብርብ ተደርጎ በመጨረሻ ተገኘ። የክልሉ ሴቶች ጉዳይና ፖሊስ ቆላ ተንቤን ወረዳ ውስጥ “በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሔድ ነበር” የተባለውን ሠርግ ማስቆሙን፣ ወረዳውም ትብብር ማድረጉን የሚገልጸውን የመጨረሻውንና ምሽት ላይ የተበሰረውን ይህንን ዜና እውነት እንደሆነ አረጋግጠን ቀኑን ስንጨርስ ትልቅ እፎይታ ነበር። ዳግም የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛን ጉልበት ያየንበት፣ ለበጎ ሲውል የታዘብንበት ክስተትም ሆኖ አልፏል።

ስለ ትዝብት ከተወራ አይቀር፣ ይህ መረጃ ሲዘዋወር በነበረበት ወቅት ድርጊቱን ካወገዙት ባላነሰ ሊባል በሚችል ደረጃ፥ ለድርጊቱ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አስተያየት ማንበብ ፎቶውን ከማየት ባላነሰ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርና ተስፋ የሚስቆርጥ ገጠመኝ ነበር። በበኩሌ የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ጉዳይ ለብዙዎች የማይዋጥላቸው ነገር መሆኑን ባውቅም፣ በግልጽ ሕፃንነቷ የሚታይ ልጅ ታግባ አታግባ የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ማየት “እንዲህ ሆነን፣ ይህን አመለካከት ይዘን ነው ለውጥ የሚመጣው” የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ለምሳሌ ያህል “ይሄ ምርጥ ሊበረታታ የሚገባው ነው”፣ “ተውት ያሳድግበት፣ በሕግ ለተክሊል የምትሆን ሚስት ማግኘት አይችልም”፣ “ልጁ ዲያቆን ሊሆን ስለሚችል የ18 ዓመት ድንግል ከየት ያገኛል”፣ “…ይህ ዓይነት ሠርግ በተክሊል ተጋቢዎች ዘንድ የተለመደ ነው። እንደ ማሸነፊያ የሚቀርበው አካለመጠን እስክትደርስ ቤተሰብ ኃላፊነት እየወሰደ እንደሚያጋባ ነው”፣ “ሲጀመር እነሱ ያገኙትን ዕድል እግዚአብሔር የመረጣቸው ብቻ ናቸው የሚያገኙት ስለዚህ እግዚአብሔር ትዳራቸውን የአብርሃምና የሳራ ያድርግላቸው።…” የሚሉ ሲገኙበት፣ ትዊተር ላይ ደግሞ “ምን ነክቶአቸው ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ “ምንም አልነካቸው፣ አለማወቅ ነው” ብሎ የሚከራከር አለ። ሌላው “ፌስቡክ የሚጠቀም ወጣት ሕፃን ልጅ ማግባት ወንጀል ብቻ ሳይሆን ትክክል አለመሆኑን አያውቅም?” ሲባል “ቢያውቅ ፌስቡክ ላይ አይለጥፍም” ይላል መልሶ።

ድርጊቱ ክፉኛ ያሳዘናቸው ደግሞ በዚህ ጉዳይ የእምነት ቤቶችም ጭምር ከሕግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደሌለባቸው ሲያሳስቡ ነበር። የአገሪቱ ሕግ የጋብቻ ዕድሜ 18 ዓመት መሆኑን ደንግጎ ሳለ የ12 ዓመት ልጅ ካባ አልብሶ መዳር ትንሽ ሊከብድ ይገባ ነበር። ፈቅጃለሁ እንኳን ብትል ዕድሜዋ 18 ዓመት ያልሆነ ልጅ ማግባት አይደለም የግብረስጋ ግንኙነት ለማድረግ ፈቃድ መስጠት አትችልም።

ከድጋፍና ተቃውሞ አስተያየት ባለፈ አንድ በልጅነቷ ተድራ በጉዳቱ ውስጥ ያለፈች ሴት የጻፈችው ምስክርነት የሚያሳዝን ነገር ነበረው።
“…እኔስ የኔን ቀን አስታወሰኝ። ለመድኃኒያለም ማኅበር ብለው ደግሰው በልጅነቴ ሲድሩኝ። ብዙ ዓመት ዝም ብዬ ነበር። ማሳቀቁ፣ የሚነጥቀው ነገር ብዛቱ፡ የእያንዳንዱ ቀን ሕመም። የዛሬውን ፎቶ ሳይ ወደረሳሁት ወደዛ ጨለማ ጊዜ ተመለስኩ። ዛሬ ልጄን ሳያት 13ኛ ዓመቷን ደፍና፣ ለዛውም ከእኔ ልጅነት ሲተያይ የእሷ ዕድገት የበለጠ ሆኖ ‘በዚህ ዕድሜዬ ነበር ጨክነው የሞሸሩኝ፤ በዚህ ዕድሜዬ ነበር’ እላለሁ። እህቱ ብትሆን ለምን ሰው አየሽ? ብሎ የሚሸልል ሁሉ፥ የጨቅላ ጭን መሐል በባሕል አሳቦ ለመግባት ትንሽ ያዝ አያደርገውም።…”

ጽሑፌን ስደመድም የችግሩን ስፋት በሚመለከት መረጃ በመስጠት በግልጽ ሊታወቅ የሚገባውን የሕፃናት ጋብቻ በልጆቹም፣ በአገርም ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመግለጥ ነው።

የችግሩ ስፋት ምን ያህል ነው?
በተለምዶ ያለዕድሜ ጋብቻ እየተባለ የሚጠራው የሴት ሕፃናት/የልጆች ጋብቻ ማንኛውም ከ18 ዓመት በታች ባለች ሴት ልጅ ላይ የሚፈፀም ጋብቻ ነው። ይህም ልጅቷ በአካልም፣ በሥነ ልቡናም፣ በሰውነትም ልጅ ለመውለድና የትዳርን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ ባልሆነችበት ወቅት የሚፈፀም ነው። የተባበሩት መንግሥታት ሕፃናት አድን ድርጅት መግለጫ እንደሚያስረዳው፥ ይህ ድርጊት የብዙ ሰብኣዊ መብቶችን ጥሰት በውስጡ የያዘ ነው። የማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል ምልክትም ነው።
“ሙሽሮች ሳይሆኑ ልጆች” (Girls not Brides) የሚለው ዓለም ዐቀፍ የልጆች ጋብቻን የማስቀረት ዘመቻ ድረገጽ ዩኒሴፍን ጠቅሶ እንዳስቀመጠው በ2017 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በተደረገ ጥናት የተገኘው መረጃ በኢትዮጵያ ከታዳጊ ሴት ልጆች 14 በመቶ የሚሆኑት 15 ዓመት ሳይሞላቸው ያገቡ ሲሆን፥ 40 በመቶው 18 ዓመት ሳይሞላቸው ያገባሉ። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም አገራችን ሕፃናትን በመዳር 16ኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች። በዚህ መሠረት ከአምስት ሴት ልጆች ኹለቱ፣ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ትዳር ይዘዋል፤ ከአምስቱ አንዷ ደግሞ 15 ሳይሞላት ለትዳር ተሰጥታለች። ሥርጭቱ በየክልሉ የሚለያይ ሲሆን፥ አማራ ክልል ከፍተኛውን ቁጥር በመያዝ 45 በመቶ ሴት ልጆች በልጅነታቸው የሚዳሩበት ክልል ነው።

የሴት ሕፃናት ጋብቻ ለምን ይፈፀማል?
መረጃዎች እንደሚሉት የግዴታ ጋብቻ እና ልጆችን መዳር በብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት “ባሕል” እና “ልማድ” ተደርጎ ተይዟል። በአገራችንም ከላይ የተጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎችን ጨምሮ ብዙዎች “እዚያ አካባቢ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነው። በተክሊል ጋብቻ ይኼ የታወቀ ነው” የሚል አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። የማደጎ ጋብቻም ይሁን ሌላ መቅረት ያለበትና እየቀነሰም የመጣ “ባሕል” ለዚህ ዋና ምክንያት ነው።

ብሔራዊ የልጆች ጋብቻን የማስወገድ ጥምረት በተሰኘው ቡድን አማካኝነት በሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር መሪነትና በዩኒሴፍ ድጋፍ የተደረገ ጥናት ግኝት እንደሚለው ድህነት ልጆችን በለጋነታቸው ለመዳር ዋና ምክንያት አይደለም።

ወላጆች በከፋ ድህነት መኖራቸው ሳይሆን ይልቁንም በማኅበራዊ መደብ ደረጃ ለማሳየት፣ እንዲሁም የሆነ የመደብ ደረጃ ላይ ያሉ ኹለት ቤተሰቦችን የማዛመድና የማቀላቀል ጉዳይም ነው። ይህ በየቦታው የተለያየ መሆኑ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

ዋናው ጉዳይ ግን “ሴት ልጅ አጎጠጎጤ ካወጣች መዳር ነው፣ ትባልጋለች” የሚል ባሕል እና ልማድ ነው። “የተፈጠረችው ልትዳር፣ ልትወልድ ነው፤ በጊዜ ትጠናቀቅ” ብሎ የሚወስን ልማድ። የቤተሰብን ክብር የማስጠበቅ “ንፁህ” ሆኖ የመገኘት ግዴታን የማረጋገጥ ብቸኛ መንገድ በሕፃንነት መዳር ነው ተብሎ ስለሚታሰብም ጭምር ነው ይህ የሚሆነው።

የሕፃናት ጋብቻ ለእናቶች ሞት ዋና ምክንያት ነው!
የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ወር የተከበረውን የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ33 በመቶ በላይ የኅብረተሰቡን ክፍል የሚወክሉት ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ 40 በመቶዎቹ በ18 ዓመታቸው ያገባሉ።

20 በመቶ ያህሉ ደግሞ 18 ዓመት ሳይሞላቸው የሚያረግዙ ሲሆን፣ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭነታቸውም የጎላ ነው። የአፍላ ዕድሜ እርግዝና በአብዛኛው የሚከሰተው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ፣ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ባላቸውና በገጠር አካባቢ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው።
በአብዛኛው እርግዝናው የሚከሰተው በጋብቻ ምክንያት መሆኑን የጠቆመው መረጃው፣ እርግዝናው የሚያስከትላቸውንም ችግሮች አስፍሯል።
የአፍላ እርግዝና፣ ለከፍተኛ ደም ግፊትና ደም ማነስ፣ ቀኑ ያልደረሰ ሕፃን ለመውለድ፣ ንፅሕናውን ላልጠበቀ የፅንስ ማቋረጥና ለተወሳሰበ ምጥና ፊስቱላ ለመጋለጥና ከማኅበራዊ ሕይወት ለመስተጓጎል ምክንያት ነው።

መፍትሔ ወይም ተስፋ አለ?
ከላይ የጠቀስነውን የአመለካከት ችግርና የተግባራዊነቱን ስፋት ስንጠቅስ የመጣ ለውጥ የለም ወይም ተስፋ የለም ለማለት አይደለም። በመንግሥትና በአጋሮች በተለያየ መልኩ የሚደረገው ዘመቻ ውጤት አምጥቷል። በዚህም በቀደሙት ዓመታት 60 በመቶ የነበረው የልጆች ጋብቻ ወደ 40 በመቶ ወርዷል። ይህም በዓለም ከፍተኛ ለውጥ ካስመዘገቡ አገሮች ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል፤ 40 በመቶ ቀላል ቁጥር አለመሆኑ ባይረሳም።
የሚታየው ለውጥ የመጣው ሴት ልጆች ትምህርት ቤት እንዲቆዩ ዘመቻ በማድረግ፣ ወላጆችን በማስተማር፣ መምህራን የለውጡ አስፈፃሚና ተቆርቋሪ እንዲሆኑ በማድረግ በመሆኑ ይህን ማስቀጠል ያስፈልጋል።

ሌላው ዋናው ለሴት ልጅ ቦታ የማይሰጥ ባሕል የሚቀየርበትን ሒደት የማፍጠን ብቻ ሳይሆን ሴት እንደ አምራች ለአገር ዕድገት አስተዋፅዖ ማበርከት የምትችል፣ በራስዋ ሕይወት መወሰን ያለባት፣ ከትዳርና ልጅ መውለድ ውጪ ራዕይ ሊኖራት የሚችል፣ መሆኑን ማስተማርና ማስረፅ፣ ተከታታይ ዘመቻ ማድረግ፣ ልጆች ተድረው ሲገኙ በድርጊቱ ተሳታፊዎችን በወንጀል መጠየቅ ያስፈልጋል።

ዋነኛው የመፍትሔው አካልም በተለይ የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል። አጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የማኅበረሰቡን ግማሽ አካል ሰብኣዊ መብቶች የጣሰ ዕድገት ሊኖር እንደማይችል፣ የሕፃን ልጅ ሕይወት ዳግም እንዳይበራ አድርጎ ለዘላለም የሚያጨልም፣ ከትምህርት ገበታ የሚያስቀር፣ ለጨዋታና ለማደግ ዕድል ያላገኘ ያልጠና አካሏን ለግንኙነትና ለእርግዝና መዳረግ፣ በወሊድ ምክንያት ለሚከሰት ሞት አልያም በአገራችን በስፋት ለሚታየው የፊስቱላ ችግር የሚዳርግ “ባሕል” ተቀባይነት እንደማይኖረው ሊያሳዩ ይገባል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here