ድቅድቁን ጨለማ ብርሃን አሸንፋው ነግቷል። መንጋቱን የሚያመለክቱት የብርሃን ሰበዞች ደግሞ በመስኮቴ ቀዳዳ ሾልከው ገብተው የድል አድራጊነት ፈገግታቸውን በብርሃን መልክ እየለገሱኝ ነው። እኔም ደስ ብሎኛል። ለዓመታት የዘራሁ ዘር ፍሬ አፍርቶ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመመረቅ ኹለት ቀናት ብቻ ነበር የሚቀሩኝ። በመሆኑም ከጓደኞቼ ጋር ተገናኝተን ምሳ ከበላን በኋላ የምርቃት ገዋናችንን ከዩኒቨርስቲው ግቢ ለመውሰድ ተቀጣጥረናል። ምሳ ለመብላት የተቀጣጠርንበት ሬስቶራንት ቀድሜ ነበር የደረስኩት። እናም አራት ወንበር ያለው ጠረጴዛ መርጬ ተቀመጥኩ። የጓደኞቼን በቶሎ መምጣት በመፈለጌ የእጄን ሰዓት በተደጋጋሚ አያለው፤ አርፍደዋል!
በዚህ መሀል ጠይም ዘለግ ያለ ቁመት ያለው ወጣት በድንገት መጥቶ ከፊት ለፊቴ ተቀመጠ። እኔም በውስጤ “ወንበሩ ሰው አለው?” ብሎ ቢጠይቅ ምን አለበት ብዬ አንድም ቃል ሳልተነፍስ አብሰለሰልኩ። ልጁ በመቀመጥ ብቻ ሳያበቃ “ምነው ብቻሽን?” አለኝ። ሰዎች ባሉበትና ራሱ ከጎኔ በተቀመጠበት ሬስቶራንት “ምን የሚሉት ጥያቄ ነው?” በማለት ቃል ሳልተነፍስ ከራሴ ጋር ማውራቴን ቀጠልኩ።
“አይ ሴቶች ተኳኩላችሁ ወጥታችሁ ሲያዋሯችሁ ምንም እንዳልፈለገ ሰው የምትግደረደሩት ነገር እኮ ነው የሚገርመኝ” ብሎ ተናገረ። አሁንስ ዝምታም ልክ አለው ብዬ መመለስ ጀመርኩ።
እኔ: “መኳል ከመቼ ጀምሮ ነው ሴት ለተቃራኒ ጾታ ፍላጎት እንዳላት ማሳያ የሆነው?”
እሱ:”እሱን እንኳን ተይው! ደህና ነገር ከመስራት ስትኳኳሉ የምትውሉት ታዲያ ዝም ብላችሁ ነው?”
እኔ: “አንተ ጺምህን የምትላጨው ለምንድነው?” ጺሙን ሙልጭ አድርጎ መላጨቱን በማስተዋል
እሱ:”ያው ለማማር ነዋ”
እኔ: “ሴቶችም በተመሳሳይ ምክንያት ነው ሜካፕ የሚጠቀሙት። ውበታቸውን ለማጉላትና ለማማር”
እሱ: “ሜካፕ ለመቀባት የምታጠፉትን ጊዜ ብታጠኑበት የት በደረሳችሁ ነበር”
የሆነው ሆኖ ሳያስፈቅደኝ ከመቀመጡና ማውራት አለመፈለጌን አይቶ ዝም ካለማለቱ በላይ ሜካፕ የምትቀባ ሴት መድረስ የሚገባት ቦታ አትደርስም ወይንም ለሌሎች ጉዳዮች ትኩረት አትሰጥም የሚል አንደምታ ያለው ንግግሩ ገረመኝ። በእርግጥ ይህ አመለካከት የዚህ ወንድም ብቻ አይደለም። ብዙ ጊዜ ሴቶችን ለመተቸት ሰዎች ከሚጠቀሙበት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሜክአፕ ጉዳይ ነው።
ሜካፕ የሚቀቡ ሴቶች ከኩልና ከሊፕስቲክ ውጪ የሚጨነቁለት ነገር ያለ የማይመስላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። እውነቱ ግን ከዚህ ይለያል። በወቅቱ ምናልባትም ይህ ወንድም እኔና ከሚመጡት ሦስት ወዳጆቼ መካከል ሁለቱ ሜካፕ የተቀባን ቢሆንም ከኹለት ቀናት በኋላ የማዕረግ ተመራቂ እንደሆንን ቢያውቅ አመለካከቱን ይቀይር ይሆን? ብዬ አስቤም ነበር።
በእኔ እምነት ሜካፕ መቀባትም ሆነ አለመቀባት የግል ምርጫ ነው። ስለዚህ ምርጫን ለመራጭዋ ትተን ሴትን በምትሠራው ሥራ ብቻ ብንመዝናት መልካም ነው። ሜካፕ የምትቀባ ሴት ከሜካፕ ውጩ አታስብም ወይንም እንደዛ የምታደርገው ተቃራኒ ጾታን ለመሳብ ነው ብሎ መፈረጅ ስህተት ነውና!
“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ኪያ አሊ
kiyaali18@gmail.com
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011